በጉራጌ ሀገረ ስብከት ጽ.ቤት ሲካሄድ የቆየው 17ኛው የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ጉባኤ ባለ14 ነጥብ መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ !!!

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጉራጌ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም የቅዱስ ዜና ማርቆስ ዘምሁር መንፈሳዊ ኮሌጅ መሥራች ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ርእሰ መንበርነት ከህዳር 24-25 ቀን 2014 ዓ.ም
ሲካሄድ የቆየው 17ኛው የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ጉባኤ ተጠናቋል።

የሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ጉባኤ በወልቂጤ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የስብሰባ አዳራሽ ብፁዕነታቸውን ጨምሮ የሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች፣የወረዳ ሊቃነ ካህናት፣የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የሰ/ት/ቤት እና የሰበካ ጉባኤ ተወካዮች በተገኙበት ለሁለት ቀናት የተካሄደ ነው።

የጉባኤው ርእሰ መንበረ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዋና ዓላማ ቤተ ክርስቲያን በዓመቱ የተሠሩ መንፈሳዊ ሥራዎችን የምትፈትሽበት: ለመንፈሳዊ አገልግሎቱ ተግዳሮት የሆኑ ችግሮችን እየነቀሰች የምታወጣበት እንዲሁም ከእግዚአብሔር የተቀበለችውን የወንጌል ተልእኮ እንዴት ማስቀጠል
እንዳለባት የምትመክርበት ወቅት መሆኑን ባደረጉት ንግግር አስታውሰዋል።

አያይዘውም በሀገረ ስብከቱ የተከፈተው መንፈሳዊ ኮሌጅ ለእናንተ ነው፣ልጆቻችሁን ላኩ፣ አስተምሯቸው መንፈሳዊ ኮሌጅ ከፍተን ስናበቃ ያልተማሩ ዲያቆናት ፣ ካህናት እና አስተዳዳሪዎች እንዲሁም ያልሰለጠኑ የሰበካ ጉባኤ አባላትና የሰ/ት/ቤት ወጣቶች ሊኖሩ አይገባምና  በየደረጃው እናስተምራለን ብለዋል።

ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ  የአብያተ ክርስቲያናት አሳበ ነው”(2ቆሮ.11፥28) በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ በቆየው ዞን ዓቀፍ መደበኛ ጉባኤ የአገልጋዮች የትጋት ማነስ እና የጊዜ ተለዋዋጭነት ለቤተ
ክርስቲያን ተልእኮ አለመሳካት ተግዳሮት መሆኑን መጋቤ ሐዲስ አባ ገብረ ኢየሱስ በሰጡት ትምህርተ ወንጌል ገልጸዋል።

የ2013 ዓ.ም የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የሥራ አፈጻጸም ክንውን ሪፖርት በሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሥርዓት ሣህሉ ተሰማ ተደምጦ በጉባኤው ታዳሚዎች ውይይት ተደርጎበታል።

የቤተ ክርስቲያን ዋንኛ ተልእኮ ስለሆነው የወንጌል አገልግሎት እና የሀገርም ሆነ የቤተ ክርስቲያን የነገ ተረካቢ ወጣቶችን የተመለከተ ሁለት ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ሐሳብ ተሰጥቶባቸዋል።

በመጨረሻም የሥራ ብልጫ ያሳዩ የወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ሽልማታቸውን ከአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ  ብፁዕ አቡነ  መልከጼዴቅ በመቀበል ጉባኤው  በብፁዕነታቸው አባታዊ መመሪያና  ቃለ ምዕዳን በጸሎት ተዘግቷል።

በመ/ር ሽፈራው እንደሻው

የመረጃ ምንጭ:- የጉራጌ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤ