በጉራጌ ሀገረ ስብከት በእዣ ወረዳ በአገና ከተማ ውስጥ የሚገኘው የቅዱስ ዑራኤል አዲስ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶ በመጠናቀቁ በብፁአን አባቶች ተባርኮ ተመረቀ

በጉራጌ ሀገረ ስብከት በእዣ ወረዳ በአገና ከተማ ውስጥ የሚገኘው የቅዱስ ዑራኤል አዲስ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶ በመጠናቀቁ በግንቦት 21 ቀን በአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅና በሰሜን አሜሪካ የካሊፎርንያ አከባቢ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ተባርኮ ተመርቋል፡፡

አዲስ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረተ ድንጋዩ ከተጣለ ከ9 ዓመታት በኋላ ተጠናቅቆ በግንቦት 21 ቀን ተባርኮ በማግሥቱ በቀን 22 ብፁአን አበው ሊቀ ጳጳስትና በርካታ ምእመናን በተገኙበት ቅዳሴ ቤቱ ተከብሮ የዋለ ሲሆን ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ቀድሰው ምእመናኑን ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙን አቀብለዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሕዝብ ግኑኝነት ዋና ክፍል ኃላፊ መ/ምሕረት በቃሉ ወርቅነህ ዕለቱን የተመለከተ ትምህርት የተሰጠ ሲሆን በትምህርታቸው በኢሳ 6÷6-7 ያለው ኃይለ ቃል መነሻነት “ሱራፌልም አንዱ እየበረረ ወደ እኔ መጣ፥ በእጁም ከመሠዊያው በጕጠት የወሰደው ፍም ነበረ። አፌንም ዳሰሰበትና። እነሆ፥ ይህ ከንፈሮችህን ነክቶአል፤ በደልህም ከአንተ ተወገደ፥ ኃጢአትህም ተሰረየልህ አለኝ።“ በማለት መላእክት ለሰው ልጆች ያላቸውን ተራዳኢነትና ባለሟልነት ሰፋ አድረገው ማስተማራቸውን ተገልጿል፡፡

በክብረ በዓሉ የተገኙት ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስም ግበሩ ኲሎ ዘይቤለክሙ፣ የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ በሚል መነሻነት ሰዎች ሁሉ የእመቤታችን ምክር ሰምተው ፣የእግዚአብሔርን ቃል፣ ትእዛዝ፣ ብሎም የቤተ ክርስቲያንንና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ትእዛዝ እንዲከብሩ ለምእመናኑ አባታዊ ምክራቸውን አሰተላልፈዋል፡፡

ለካህናቱና ምእመናኑ አባታዊ መልእክትና መመሪያ ያስተላለፉት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ፡ ሕንጻ አብያተ ክርስቲያናት እየተገነቡ ናቸው፣ እኛም በዛው ልክ በሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ተገኝተን ተምረን በሃይማኖትና በምግባር ታንጸን በክርስቲያናዊ ሕይወት በመልካም ልናድግ ይገባል ብለዋል፡፡

ከሕንጻዉ ኮሚቴ ሊቀ መንበር ሪፖርት እንደተደመጠው ሕንጻው ለማስጀመር የነበረውን 70ሺህ ብር ብቻ ይዘው ብረት ለመግዛት ወደ ገበያ ሲሄዱ የብረቱ ዋጋ ከዛ በላይ በመሆኑና ባለሀብቱ/ነጋዴው የተፈለገው ብረት ለቤተ ክርስቲያን መሥሪያ መሆኑን በማወቁ 70ሺህ ብሩና የሚያስፈልጋችሁን ብረት ይዛችሁ ሂዱ ብሎ መተባበሩን ተነግሯል፡፡

ከዚህ በተያያዘም የቤተ ክርስቲያኑ የሕንጻው ዲዛይንና ሙሉ ሞያዊ አቅም በኢንጅነር ቸሩ መሸፈኑን ተገልጿል፡፡

ዘጋቢ መ/ር ኪደ ዜናዊ
ምንጭ ከሀገረ ስብከቱ የሕዝብ ግንኙነት የተገኘ