በዓለ ጥምቀት የሀገር እና የዓለም ሕያው ቅርስ በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው መንፈሳዊ የምሥጋና መርሐ ግብር በጃንሆይሜዳ (ጃንሜዳ) ተደረገ

ታህሳስ 25 ቀን 2013 ዓ/ም የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊና የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፡ የአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ፡ የሶማሌና ምሥራቅ ሀረርጌ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳደር ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነትና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎች፡ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰ/ት/ቤቶች አንድነት መሪዎች እንዲሁም በርካታ የአድባራትና ገዳማት የሰ/ት/ቤት መዘምራን ወጣቶችና ሕዝበ ክርስቲያን በተገኙበት ታሪካዊና ጥንታዊ የጥምቀት ማክበሪያ ቦታ የሆነውን ጃንሜዳን በማጽዳትና ለበዓሉ ዝግጁ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉትንና የደከሙትን የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችንና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ
ኃላፊዎችን ለማመስገን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ ዋና ክፍልና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰ/ት/ቤቶች አንድነት የጋራ አስተባባሪነት “በዓለ ጥምቀት የሀገር እና የዓለም ሕያው ቅርስ” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው መንፈሳዊ የምሥጋና መርሐ ግብር በጃንሆይሜዳ (ጃንሜዳ) ከቀኑ በአሥር ስአት (10:00) ተደርጓል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ አጭር ሪፖርት ያቀረቡት የሰ/ት/ቤቱ አንድነት ተቀዳሚ ምክትል ሰብሳቢ ላእከ ኄራን መንክር ግርማ ” በዓለ ጥምቀት በዚህ ቦታ ለአንድ ክፍለ ዘመን ሲከበር ቆይቷል፡ ዛሬም የተሰባሰብነው ይህንን ታሪክ ለመዘከርና ሥፍራውን ለማጽዳት አስተዋፅኦ ያደረጉ አካላትን ለማመስገን ነው ብለዋል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊና የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ዛሬ በዚህ ቦታ የተገኘነው የሰላም ቃል የሚሰበክበትንና ታቦታቱ የሚከብሩበትን ይህን ቅዱስ ሥፍራ ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ሁሉ ከፍተኛውን አስተዋፅኦ የተወጣችሁትን ወገኖች ለመመረቅ ነው፡ወደፊት በድምቀት ለምናከብረው የአደባባይ በዓልም አብሮነታችሁ እንደማይለየን ተስፋ አደርጋለሁ በማለት ገልጸዋል፡፡
በምክትል ከንቲባ ማእረግ የከተማ አስተዳድሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥረቱ በየነ “የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክያን በሀገራችን ታሪክ ውስጥ እጅግ ጉልህ የታሪክ ድርሻ ያላት ትልቅ ተቋም ናት፡ ባሳለፍነው አስቸጋሪ ወቅት ሁሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከመንግሥት አጠገብ በመሆን ላበረከተችው ከፍተኛ ትብብር አመስግነው፡ ወደፊትም የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክያን ለምታነሳቸው የትኛውም ጥያቄዎች የከተማ አስተዳደሩ በአስቸኳይ እንደሚፈታ አረጋግጠዋል፡፡
በመጨረሻም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ፈታኝ በሆነው ጊዜ መንግሥት ለወሰደው አፋጣኝ ርምጃ እኛም የሰው ሕይወት ይገደናልና ተባባሪዎች በመሆን ክፉን ወቅት በትብብር አልፈናል፡ሆኖም ግን ታሪካዊው ቦታችን የቀደመ መልኩ ተለውጦ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ምቹ ባለመሆኑ የተነሣ ወደነበረበት ማንነት ለመመለስ ብዙ ውይይት አድርገናል፡ ለችግሩም አፋጣኝ መፍትሔ ስላገኘን እነሆ ዛሬ በደስታ ተሰባሰበናል፡ በዚህ መልካም ተግባር የተሳተፋችሁ ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ፡ ምሥጋናችን ይድረሳችሁ ብለዋል፡፡
አያይዘውም በዚህ ቅዱስ ሥፍራ ቅዱሳን ፓትርያርኮቻችን ተገኝተው ሕዝበ ክርስቲያኑን የሚባርኩበት፡ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶችና ጎብኝዎች የሚገኙበት ስለሆነ ልናሳምረውና መልካም ገፅታ ልናጎናፅፈው ይገባል፡ይህንን ኃላፊነት ደግሞ እኛ እንወስዳለን፡ስለሆነም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ስም የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ይሰጠን ሲሉ አባታዊ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፡ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና ፣ክብርት ምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤ ጋር ተገኝተው ታሪካዊ ቦታውን በባረኩበት ወቅትም በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ስም የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ሊሰጠን ይገባል የሚል ጥያቄ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው፡፡
መ/ር ሽፈራው እንደሻው የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ
ፎቶ-በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ