“በዓለ ጥምቀት በኢትዮጵያ”
ከሊቀ ብርሃናት ኢሳይያስ ወንድምአገኘሁ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው ዘጠኝ ዓበይት በዓላት ውስጥ በየዓmቱ ጥር 11 ቀን በመላዋ ኢትዮጵያ በሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በገጠርም በከተማም በታላቅ ድምቀት የሚከበረው በዓለ ጥምቀት አንዱ ነው፡፡ ይህም በዓል ከበዓላቱ ሁሉ በላይ በድምቀት የሚከበር ታላቅ በዓል ነው፡፡
የጥምቀትን በዓል አከባበር ከሁሉም በዓላት ለየት ከሚያደርጉትም ምክንያቶችና ሁኔታዎች ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
1) ጥር 10 ቀን በዋዜማው ከተራ በሚል ስያሜ በሚታወቀው በዚሁ ዕለት ባሕረ ጥምቀት ከተዘጋጀ በኋላ በመላዋ ኢትዮጵያ በከተማም በገጠርም በመሐል አገርና በጠረፍ ጭምር ባሉት አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙት ታቦታት ሁሉ ከመንበራቸው ተነሥተው ወደተዘጋጀው ባሕረ ጥምቀት በመውረድና በተዘጋጀላቸው ድንኳን ውስጥ በማደር በዚያው በአደሩበት ድንኳን ውስጥም ማኅሌቱና ሥርዓተ ቅዳሴው ከተከናወነ በኋላ ባሕረ ጥምቀቱ ተባርኮ ሕዝበ ክርስቲያኑ ሁሉ የበረከቱ ተሳታፊ ከመሆናቸውም በላይ በዓሉ ከዋዜማው (ከከተራው) ቀን ጀምሮ ታቦታቱ ወደየአብያተ ክርስቲያናቱ ተመልሰው በመንበራቸው ላይ እስኪያርፉ ድረስ ሁለት ቀን መሉ በየባሕረ ጥምቀቱና በየመንገዱ ሁሉ በድምቀት የሚከበር በዓል በመሆኑ ነው፡፡ ይህም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለማትን የፈጠረና ሁሉንም ያስገኘ ልዑል አምላክ ሲሆን ለእኛ አርአያና ምሳሌ ይሆን ዘንድ በተዋሐደው ሥጋ ትኅትናን ገንዘብ በማድረግ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሄዶ በአገልጋዩ በዮሐንስ መጥምቅ እጅ የመጠመቁ ምሳሌ መሆኑን ያስረዳል፡፡
2) የጥምቀትን በዓል ካህናቱ በማኅሌትና በመዝሙር፣ በቅዳሴና በልዩ ልዩ ውዳሴ፤ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በተለያዩ መዝሙራትና ሽብሸባዎች ሕዝበ ክርስቲያኑ ደግሞ ወንድ ሴት ሽማግሌና ወጣት ሕፃናትም ሳይቀሩ ሀብት ያለው አዲስ ልብስ ገዝቶ፣ ዓቅም የሌለው ደግሞ በቤት ውስጥ ያለውን አጥቦና አጽድቶ፤ ነጭ በነጭ ለብሶና አሸብርቆ እጅግ በደመቀና ባማረ ሁኔታ ታቦታቱን በማጀብ በዝማሬ፣ በሆታና በእልልታ፣ በከበሮ፣ በበገናና በእምቢልታ በታላቅ ዝግጅትና ሰልፍ በባሕረ ጥምቀቱ አካባቢና ታቦታቱ በሚያልፉባቸው መንገዶች ሁሉ በታላቅ ድምቀት የሚያከብረው በዓል መሆኑ ነው፡፡
“ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” የሚለው ዘይቤም የሚያመለክተው ይህንኑ የጥምቀቱን በዓል ታላቅነት ነው፡፡ ነጭ በነጭ ተለብሶ የሚከበር በዓል መሆኑም በጥምቀት የሚገኘውን አዲስ ልደትና ከሐጢአት ቍራኝነት የመንፃትን ምሥጢር የሚያመለክት ነው፡፡
3)ሕዝበ ክርስቲያኑ ሁሉ በተለይም ወጣቱ ኅብረተሰብ ታቦታቱ በሚያርፉባቸው የባሕረ ጥምቀት ቦታዎች ከካህናቱ ጋር በማደርና ቀንም ታቦታቱ ወደ መንበረ ክብራቸው እንስኪመለሱ ድረስ ታቦታቱን አጅበው በመዋል፣ በልዩ ልዩ ዝማሬ፣ በጨዋታና በታላቅ ደስታ የሚያከብሩት ታላቅ በዓል ነው፡፡ በዓሉ በሁሉም አህጉረ ስብከት እጅግ በደመቀ ሁኔታ የሚከበር መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም በደቡብ ክፍላተ ሀገር የመስቀል በዓል ከሁሉም በዓላት በላይ እንደሚከበር ሁሉ በሰሜኑ ደግሞ የጥምቀት በዓል ከሁሉም በዓላት የበለጠ እንደሚከበር ይታወቃል፡፡ በጸናው ለመናገር እንጂ የመስቀል በዓል በሰሜን፣ የጥምቀት በዓልም በደቡብ አይከበርም ማለት ግን አይደለም፡፡ የአከባበሩ ሁኔታ እንደሀገሩ የሚለያይ መሆኑን ለመግለጥ ያህል እንጂ ሁሉም በዓላት በሁሉም ቦታ እንደሚከበሩ የታወቀ ነውና፡፡በተለይም የጥር ወር በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ሰብል ተሰብስቦ የሚያበቃበትና ምርት የሚታፈስበት ከመሆኑም በላይ ለገበሬው ኅብረተሰብ የዕረፍት ጊዜ ስለሆነ በዚያውም ላይ ምርቱ በጎተራ ስለሚኖር በዓሉ በዘፈን በጨዋታ ብቻ ሳይሆን በመብል በመጠጥ፣ በተድላና በደስታ የሚከበር በዓል በመሆኑ ይህ በዓል በካህናትና በምእመናን ዘንድ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ዘንድ እጅግ ተወዳጅና ተናፋቂ፤ የሁሉንም ቀልብ የሚያስብና የሚማርክ ነው፡፡ በመሆኑም ፆታና ዕድሜ ሳይለይ ሁሉም በታላቅ ስሜትና ፍቅር ያከብረዋል፡፡
የጥምቀት በዓል በተለይም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ያሉ ወጣቶች ሁሉ ከእረኝነትና ከመሳሰሉት አድካሚ ሥራዎች ሁሉ ነፃ ሆነው የሚዝናኑበትና የወጣትነት ስሜታቸውን በዘፈን፣ በጭፈራ በእስክስታና በጨዋታ የሚገልጡበትና የኑሮ ጓደኛ የምትሆናቸውንም ኮረዳ የሚመርጡበትና የሚያጩበት ወቅትና ጊዜ ሆኖ ቆይቶአል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተለይ የከተማው ወጣቶች በዓሉን የሚያከብሩት በእስክስታና በዘፈን በጨዋታ ሳይሆን አብዛኛዎቹ መዝሙር እየዘመሩና እያሸበሸቡ እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑበት በዓል እየሆነ መምጣቱ እጅግ የሚያስደስትና ዓላማውንም የጠበቀ ሆኖአል ማለት ይቻላል፡፡
የበዓሉ ታላቅነት መገለጥ ያለበትም በተድላ በደስታው በዘፈን በጨዋታው ሳይሆን በውስጡ ያለውን ጥልቅና ረቂቅ ምሥጢር በመመርመርና በማስታወስ ሊሆን ይገባል፡፡ ይኸውም፡ –
1. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ፣ በማየ ዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል እግዚአብሔር አብ በደመና ሆኖ “ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ወሎቱ ስምዕዎ” ማለት “በእሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው ቃሉን ስሙት” እያለ ሲናገር በግልጥ ተሰምቶአል፡፡
2. አሁንም ከሦስቱ አካላ አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ (ኢየሱስ ክርስቶስ) በለበሰው (በተዋሐዳው) ሥጋ በማየ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ በግልጥ እየታየ ተጠምቆአል፡፡
3. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላም ሦስተኛው አካል እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ከሰማይ ሲወርድና በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራስ ላይ ሲያርፍ በግልጥ ታይቶአል፡፡ በዚህም ምክንያት የጥምቀት በዓል የሚከበርበት ወቅት ዘመነ አስተርእዮ በመባል ይታወቃል፡፡ አስተርእዮ ማለትም መገለጥ ማለት ነው፡፡
ስለዚህ በዓለ ጥምቀት የቅድስት ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት የታወቀበት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ እውነተኛ አምላክ መሆኑ የተመሰከረበት ዕለት ስለሆነ ይህ ረቂቅ ምሥጢር የበዓሉን ታላቅነት ያረጋግጣል፡፡ (ማቴ. 3÷13-17፤ ማር. 1÷9-11፤ ሉቃ. 3÷21)፡፡
4. በዓለ ጥምቀት “አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ፣ ሄዋን አመቱ ለዲያብሎስ” ተብሎ በዲያብሎስ አስገዳጅነት ተፈርሞ የነበረው የአዳምና ሄዋን የዕዳ ደብዳቤ የተደመሰሰበትና የሰው ልጆች ሁሉ ከሰይጣን ባርነት ነፃ የወጡበት የነፃነት መታሰቢያ በዓል በመሆኑና ክርስቲያኖች ሁሉ በጥምቀት በሚገኝ ዳግም ልደት የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸው የተረጋገጠ ስለሆነ በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም ለተጠመቁ ክርስቲያኖች ሁሉ የዳግም ልደታቸው መታሰቢያ በዓል ነው፡፡ በመሆኑም በዓለ ጥምቀት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ዘንድ በታላቅ ክብርና ከሁሉም በዓላት በላይ በሆነ ድምቀት ሲከበር ኖሮአል ወደፊትም በዚሁ ይቀጥላል፡፡
ማጠቃለያ
እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓትና ትውፊት ባሕረ ጥምቀቱ ተባርኮ ምእመናን በተባረከው ውኃ የሚረጩትና የሚጠመቁት ጥምቀትን ለመድገምና እንደገና መንፈሳዊ ልጅነትን ለማግኘት ወይም ለማደስ ሳይሆን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ጥምቀት በሚታይ ምሳሌ ለመግለጥና በረከት ለማግኘት መሆኑን፤ እንዲሁም ታቦታቱ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ መውረዳቸውና ካህናቱና ሕዝቡም ታቦታተ ሕጉን አክብረው ወደ የባሕረ ጥምቀቱ መውረዳቸው ከላይ እንደተገለጠው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሂዶ በእደ ዮሐንስ በማየ ዮርዳኖስ መጠመቁን የሚያስረዳ ታላቅ ምሳሌና እውነተኛ የመታሰቢያ በዓል መሆኑን ያመለክታልና የበዓሉን ድምቀት ብቻ ሳይሆን ምሥጢሩን በጥልቀት ልንመረምረውና ልብ ልንለው ይገባል፡፡