በዓለ አስተርእዮ

አስተርእዮ፡- ቃሉ ግእዝ ነው አስተርእዮ ማለትም መገለጥ፣ መታየት ማለት ነው፡፡
በግሪክ ቋንቋ ኤጲፋንያ ይባላል ኤጲፋንያ ማለትም መገለጥ፣መታየት፣ማለት ነው አሁን ያለንበት ዘመን ዘመነ አስተርዕዮ ይባላል የመገለጥ፣ የመታየት ዘመን ማለት ነው፡፡
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ስጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው ሆኖ የተገለጠበት ዘመን ስለሆነ እና እንዲሁም በጥምቀቱ አንድነቱን ሦስትነቱን የገለጠበት ዘመን በመሆኑ ዘመነ አስተርእዮ፡- የመገለጥ፣ የመታየት ዘመን ተብሏል፡፡
የሰላም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ተጠመቀ? የተጠመቀበት አምስት ምክንያቶች አሉ እነሱም እንደሚከተለው ተገልጸዋል፡፡
1.አንድነቱን ሦስትነቱን ለመግለጽ ነው፡- /በማቴዎስ ወንጌል ም. 3፡13-17/ እንደተጻፈው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ሲጠመቅ እግዚአብሔር አብ “ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር” (የምወደው ልጄ እርሱ ነው) ሲል ከሰማይ ተናግሯል፡፡
እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በርግብ አምሳል በራሱ ላይ ተቀምጧል፡፡ በዚህም አንድነቱን ሦስትነቱን ገልጧል፡፡
2.የተነገረውን ትንቢት ለመፈጸም ነው፡፡ ከትንቢቶቹ አንዱን ለአብነት ያህል እንጠቅሳለን “ባሕርኒ ርዕየት ወጎየት ወዮርዳኖስኒ ገብአ ድኅሬሁ አድባር አንፈርአዱ ከመ ሐራጊት” (ባሕርም አየች ሸሸችም ዮርዳኖስም ወደኋላው ተመለሰ ተራሮችም እንደ ጊደሮች ዘለሉ)፡፡ (መዝ. 113፡3)
3.የዕዳ ደብዳቤ አችንን ለመቅደድ ነው፡፡  የክፋት እና የተንኮል ምንጭ የሆነው ጠላታችን ዲያብሎስ አዳምና ሔዋንን መከራውን እንዳቀልላችሁ ስመ ግብርናታችሁን ጽፋችሁ ስጡኝ አላቸው፡፡ ይህም ማለት የእኔ አገልጋይ መሆናችሁን የሚገልጽ ጽሑፍ ስጡኝ ማለት ነው እነርሱም በእውነት መከራውን የሚያቀልላቸው መስሏቸው ጽፈው ሰጡት ጽሑፉም “አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስ” የሚል ነው፡፡ ይህም ማለት አዳም የዲያብሎስ አገልጋይ ነው ሔዋን የዲያብሎስ አገልጋይ ናት ማለት ነው፡፡ ይህንንም በሁለት የድንጋይ ሠሌዳ ላይ ጽፈው ሰጡት አንዱን በዮርዳኖስ፣ አንዱን በሲኦል ጣለው በዮርዳኖስ የጣለውን የዕዳ ደብዳቤአችንን ጥር 11 ቀን የሰላም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀቱ ደምስሶልናል አጥፍቶልናል፡፡
በሲኦል የጣለውን ደግሞ በዕለተ አርብ በስቅለቱ በሞቱ ደምስሶልናል አጥፍቶልናል “በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው እርሱንም በመስቀል ጠርቆ አስወግዶታል” (ቆላስ 2፡14)
ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬምም ይህንን መሠረት በማድረግ በደረሰው የእመቤታችን ምስጋና ላይ “ወሠጠጠ መጽሐፈ ዕዳሆሙ ለአዳም ወለሔዋን” የአዳም እና የሔዋንን የዕዳ ደብዳቤ ቀደደ፣ ደመሰሰ፣ አጠፋ፣ ሲል ተናግሯል፡፡
4.ጥምቀትን ለእኛ ለመባረክ ነው፡፡ ለእኛ አብነት ለመሆንና ከአምስቱ አእማደ ምስጢር በአንዱ በምስጢረ ጥምቀት ልጅነትን እንድናገኝ ለማድረግ ነው፡፡
5.ትሕትናን ለእኛ ለማስተማር ነው፡፡ ይህም በአገልጋዩ በቅ/ዮሐንስ እጅ መጠመቁ ነው፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀበት አምስት ምክንያቶች ከላይ ከ1-5 ተራ ቁጥር የተዘረዘሩት ናቸው፡፡
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን በ30 ዘመኑ ተጠመቀ? ቢሉ አዳም በተፈጠረ በ30 ዘመኑ ልጅነቱን አስወስዷል አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም ይህንን ልጅነት ለመመለስ በተመሳሳይ ዘመን በ30 ዘመኑ ተጠምቋል፡፡
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን በውኃ ተጠመቀ? እኛም በውኃ እንድንጠመቅ ለምን አዘዘ?
የሰላም ንጉሥ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በውኃ የተጠመቀበት፣እኛም በውኃ እንድንጠመቅ ያዘዘበት ምክንያት ብዙ ነው፡፡ ለአብነት ያህል ውኃን ድሃውም ሀብታሙም በቀላሉ ያገኘዋል ለድሃውም ለሃብታሙም እኩል ነው በዚህ መሠረት ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁላችንም መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ስለሚፈልግ በውኃ እንድንጠመቅ አዘዘ፡፡ እርሱም በውኃ ተጠመቀ፡፡
ያለ ጥምቀት መዳን የለም “ያመነ የተጠመቀ ይድናል ያላመነ ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል፡፡ (ማር. 16፡16)
“አማን አማን እብለከ ዘኢተወልደ ዳግመ እማይ ወእመንፈስ ቅዱስ ኢይክል  በዊአ ውስተ መንግሥተ እግዚአብሔር” (እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ካልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ይገባ ዘንድ አይችልም) (ዮሐ. 3÷5) ሲል የእውነት አምላክ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ በነገረው መሠረት ያለ ጥምቀት የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ አይቻልም፡፡ ወንዶች በተወለዱ በ40 ቀን ሴቶች በ80 ቀን የሚጠመቁበት ምክንያት፡-
1ኛ አዳም በተፈጠረ በ40 ቀኑ ሔዋን በተፈጠረች በ80 ቀኗ ቅድስት ሥላሴ ብርሃን አልብሰው ብርሃን አጎናጽፈው ገነት አስገብተዋቸዋል ይህን መሠረት በማድረግ ዛሬ ወንዶች በተወለዱ በ40 ቀናቸው ሴቶች በተወለዱ በ80 ቀናቸው ይጠመቃሉ (ኩፋ 4÷9-13)
2ኛ በብሉይ ኪዳን ወንድ ልጅ በተወለደ በ40 ቀኑ ሴት ልጅ በተወለደች በ80 ቀኗ ወደ እግዚአብሔር ቤት ይገቡ ነበር (ዘሌዋ.12÷1-5) ይህን መሠረት በማድረግ ዛሬ ወንዶች በተወለዱ በ40 ቀናቸው ሴቶች በተወለዱ በ80 ቀናቸው ይጠመቃሉ፡፡
በ40፣ በ80 ቀን የምንጠመቅበት ውኃ፡- በግእዝ ማየ ገቦ ይባላል ማይ ውኃ፤ ገቦ ጎን ነው ማየ ገቦ፡- አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ ሲሰቀል ከጎኑ የፈሰሰው ውኃ ነው በቄሱ ጸሎት ውኃው ወደ ማየ ገቦነት ይለወጣል፡፡ በዚህ ተጠምቀን ከሥላሴ ተወልደናል፤ ልጅነትን አግኝተናል፤ክርስቲያንም ተብለናል፤ ክርስቲያን የሚለውን ስም ያገኘነው በጥምቀት ነው፡፡ ክርስቲያን ማለት ትርጉሙ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የተጠመቀ ማለት ነው፡፡ እንዲሁም በክርስቶስ ክርስቲያን ተብለናል፡፡ በዚህ መሠረት የክርስቲያኖችን ሥራ ሠርተን መገኘት አለብን የክርስቲያኖች ሥራ፤ ሕገ እግዚአብሔርን፣ ትእዛዘ እግዚአብሔርን መጠበቅ ነው “ብትወዱኝስ ትእዛዜን ጠብቁ” (ዮሐ. 14፡15) ብሎ አምላካችን በቅዱስ ወንጌል በተናገረው መሠረት ትእዛዙን መጠበቅ አለብን የክርስቲያኖች ሥራ ይህ ነው፡፡ ትእዛዙን ካልጠበቅን ወዳጆቹ አይደለንም ብትወዱኝስ ትእዛዜን ጠብቁ ብሏልና በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ እንድናገኝ ትእዛዙን እንጠብቅ፡፡
ሕጉን ትእዛዙን ጠብቀን በማየ ንስሐ ታጥበን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ተቀብለን በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት እንዲሁም በቅዱሳን አማላጅነት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ልዑል እግዚአብሔር ወሰን በሌለው ቸርነቱ ይርዳን፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር
(ላዕከ ወንጌል በእደ ማርያም ይትባረክ (ቀሲስ)የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የትምህርት ሥርጭት ኃላፊ)