በዓለ ቅድስት ሥላሴ

ሥላሴ የሚለው ቃል ‹‹ሠለሰ›› ሦስት አደረገ ከሚለው የግዕዝ ሥርወ ቃል የተገኝ ሲሆን ይህም ሦስትነት ማለት ነው፡፡ ምሥጢረ ሥላሴ ብለን ስለነገረ ሃይማኖት ስንናነገር ግን አንድም ሦስትም ተብሎ ይተረጎማል፡፡ በዚህም መሠረት እግዚአብሔርን አንድም ሦስትም ብለን ማመናችንን የምንገልፅበት የሃይማኖት ዶግማ ነው፡፡እንደሚታወቀው የሥላሴ አንድነት ስንል በባህርይ በህልውና በፈቃድ…. አንድ አምላክ ማለታችን ሲሆን  ሦስትነት ስንል ደግሞ በስም’ በአካል’ በግብር ነው፡፡
የሥላሴ አንድነት እና ሦስትነትን ከሚገልጹ ማስረጃዎች ለአብነት፡-
‹‹እግዚአብሔርም አለ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር›› ዘፍ.1.26 ‹‹እግዚአብሔርም አለ ብሎ አንድነቱን ‹‹ሰውን በመልካችን እንፍጠር›› ብሎ ሦስትነትን ይገልጻል ፡፡ እንደ ዚሁም እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ ዘፍ.3 .22 ይህ ኃይለ ቃል ‹‹ከእኛ›› የሚለውና ‹እንደ አንዱ› የሚለው የሦስትነት ምሥጢር የሚጠቁም መሆኑን ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡ በዘመነ ኦሪት የሥላሴ ምሥጢር ከተገለጠበት አንዱ ለአብርሃም በመምሬ አድባር  ዛፍ ሥር ነው ፡፡ ዘፍ.18፡ 1-15 በዚህ ምዕራፍ እግዚአብሔር ለአብርሃም እንደ ተገለጠለት ወዲያውም ሦስት ሰዎች እንደ ተመለከተ አብርሃምም ሊቀበላቸው ሲጠጋ በመስገድ ‹‹አቤቱ በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደሆነ›› ብሎ አንድነቱን መግለጹን አያይዞም ደግሞ “ጥቂት ውሃ ይምጣላችሁ” ብሎ በአካል ሦስት መሆናቸውን ተናገረ፡፡ በአጠቃላይ በምዕራፉ የአንድነት እና የሦስትነት ነገር እናስተውልበታለን፡፡
ነቢየ ልዑል ኢሳይያስ ‹‹ቅዱስ’ ቅዱስ’ ቅዱስ እግዚአብሔር …›› ብለው ቅዱሳን መላእክት እንደ ሚያመሰግኑ መመሥከሩ ከሦስት ሳያሳንስ’ እና ሳያስበልጥ መጠቆሙ የሥላሴን ሦስትነት የሚያሰረዳ ነው፡፡ ኢሳ.6.1- 3
የሥላሴ ሦስትነት ስንል-  በስም፡-  አብ፤ ወልድ፤መንፈስ ቅዱስ ማለታችን ነው፡፡ ‹‹ወእንዘ ታጠምቅዎሙ በሉ በስመአብ፤ወወልድ፤ ወመንፈስ ቅድስ›› እንዲል ማቴ. 28.19
በአካል፡- 
ለአብ ፍጹም ገጽ ፍጹም አካል አለው
ለወልድ ፍጹም ገጽ ፍጹም አካል አለው
ለመንፈስ ቅድስ ፍጹም ገጽ ፍጹም አካል አለው
ብለን ማመናችንን ነው ይህም የማይወሰን  የማይለካ ረቂቅ አካልን ነው፡፡ መዝ. 33.15 መዝ. 118. 73 ዘፍ.18
በግብር ሦስትነት ስንል ፡- የአብ ግብሩ መውለድ፤ማሥረጽ፤ የወልድ ግብሩ መወለድ የመንፈስ ቅዱስ ግብሩ መሥረጽ ወይም አብ አባት፣ወልድ ልጅ ፣መንፈስቅዱስ ሠራፂ ማለታችን ነው፡፡ኢሳ.48.12 መዝ.118.16 ዮሐ 16 ÷7-19
በቅዱስ ወንጌል በዮርዳኖስ እና በደብረ ታቦር የሥላሴ ምሥጢር ገሀድ ለመሆኑ ማስረጃ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡  ማቴ. 3.16 ማቴ.17 መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ ‹‹አነ ወአብ አሐዱ ንህነ›› እኔና አብ አንድ ነን ማለቱ እና ‹‹እኔን ያየ አብን  አየ›› ብሎ ማስተማሩ ነገረ ሥላሴን ያስረዳል ዮሐ .10.30 (14÷11) በይበልጥ አብ ወላዲ፣ ወልድ ተወላዲ መንፈስ ቅዱስ ሠራጺ በማለታችን መበላለጥ እንደሌላቸው በሥልጣን በፈቃድ አንድ መሆንን ያስገነዝበናል፡፡ ለዚሀም ነው አባ ሕርያቆስ ‹‹ኢይልህቅ አብ እምወልድ ወልድኒ ኢይንዕስ እመንፈስቅዱስ  ወመንፈስቅዱስኒ ኢይንዕስ እምወልድ ወወለድኒ አይንዕስ እምአቡሁ›› በማለት እንደማይበላለጡ አስረድቶናል፡፡ እንደዚሁም ሦስት አማልክት እያልን ሳይሆን አንድ አምላክ ማለታችን እንደሆነም እሙን ነው፡፡‹‹ወመለኮትሰ አብ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ እንዳለው አባ ሕርያቆስ (ቅዳሴማርያም) በምሳሌም ለመረዳት ፀሐይ ከበብ፡ ብርሃን፡ ሙቀት፡ እሳትም ነበልባል፡ፍሕም፡ሙቀት፡ ሲኖራቸው ሦስት ፀሐይ ሦስት እሳት አይባሉም አንድ ፀሐይ አንድ እሳት እንጂ እንደዚሁ ሥላሴ በስም በአካል በግብር ሦስት ቢባሉም ቅሉ አንድ አምላክ እንጂ ሦስት አማልክት አይባሉም 2ኛ ቆሮ.13.14 ኤፌ. 4÷4
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ምሥጢረ ሥላሴ የሃይማኖት ዶግማ እና የሥርዓተ አምልኮ ሁሉ መግለጫችን ነው፡፡ ጸሎታችን፣ ጥምቀታችን፣ ቡራኬያችን…. ሁሉ በስመ ሥላሴ ነው፡፡
ይህም እንዳለ ሆኖ ነገረ ሥላሴን በበዓል ለመመስከር እና የቸርነቱ፣ የምህረቱ ተካፋይ ለመሆን በዓለ ንግሥም ይከናወናል፡፡ በይበልጥም ሐምሌ 7 ቀን ለአብርሃም በድንኳን ደጃፍ መገለጡን እና ጥር 7 በባቢሎን በሰናዖር የተፈጸመውን ተአምር በማሰብ እናከብራለን፡፡ ዘፍ.18 ዘፍ.11.1-9
በመጽሐፍ ቅዱስ እና በቅዱሳት አዋልድ መጻሕፍት እንደተመዘገበው ከጥፋት ውሃ በኋላ የኖኅ ልጆች ወልደው ተዋልደው ብዙዎች ሆኑ፡፡ በባቢሎን የነበሩት በሰናዖር ሰፊ ሜዳ አግኝተው ‹ሳንሞት ስም ማስጠሪያ ግንብ እንገንባ› ብለው መክረው ታላቅ ግንብ ገነቡ፡፡ አለቃቸው ናምሩድ ይባላል ‹‹ ሞትን የሚያመጡብን ሥላሴ ናቸውና እነርሱን ወግተን ሞትን እናርቅ ›› አላቸው ከዚያም ሆነው ጦር እየሰበቁ ይወረውሩ ጀመር ሰይጣን ከደመና በምትሀት ደም እየቀባ ይልክላቸዋል እነርሱም ደሙን እያዩ ‹‹ አሁን አብን ወጋነው አሁን ወልድን ወጋነው ….›› ይሉ ጀመር ቅድስት ሥላሴ ምንም እንኳ ምህረታቸው የበዛ ቢሆንም በሕዝቡ ላይ ዲያብሎስ ስለሠለጠነባቸው እና ለሌሎች ከሀድያን ትምህርት ይሆን ዘንድ ‹‹ንዑ ንረድ ወንክዐው ነገሮሙ›› በማለት ቋንቋቸውን ለያዩባቸው የማይግባቡ፣ የማይደማመጡ…… ሆነው ተበታትነዋል፡፡ ባለማስተዋል የሠሩትንም ሕንፃ ዓመጻ ነፋስ ጠራርጎ አጥፍቶታል፡፡ ይህን ያደረጉ ሥላሴ በመሆናቸው በዓሉ ጥር 7 ይከበራል፡፡
በአጠቃላይ ሥልጣን ሁሉ የእግዚአብሔር መሆኑን እና በራስ ደካማ አመለካከት በመታበይ በሥላሴ ሥራ መግባት’ መጠራጠር ….. እንደሚጎዳ እንደዚሁም በጽኑ እምነት በመኖር እና በሥላሴ ስም የተጠመቅን ልጅነታችንን በኃጢአት ሳናሳድፍ በንስሐ ታጥበን እና በምግባር ጸንተን መጠበቅ እንደሚገባ የበዓሉ መልእክት ያስገነዝበናል፡፡ የታማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ እንደሚል ፡፡ ኤፌ. 4÷30
             ውስብሐት ለእግዚአብሔር
                                      (መጋቤ አእላፍ ፋሲል ታደሰ (ቀሲስ))

{flike}{plusone}