በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ጠ/ሥራ አስኪያጅ ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ

0170

ቤተ ክርስቲያን በመልካም አስተዳደር ላይ ተመሥርታ ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት ለትውልዱ ተደራሽ መሆን ያስፈልጋታል፡፡
ኆኅተ ጥበብ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ መንፈሳዊ ጋዜጣ ከአዲሱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ከብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ጋር በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ዙሪያ የሚከተለውን  ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡
መልካም ንባብ
ኆኅተ ጥበብ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
ብፁዕ አባታችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ሆነው እንዲሠሩ በቅዱስ ሲኖዶስ መልካም ፈቃድ መመደብዎ ይታወቃል፡፡ ከተመደቡበት ጊዜ ጀምሮ ያከናወኑትን የመልካም አስተዳደርና የልማት እንቅስቃሴ ቢገልፁልን?
ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ
ቅዱስ ሲኖዶስ በምልዓተ ጉባኤ የቤተ ክርስቲያንን የአስተዳደርና የልማት ሥራ እንድሠራ መድቦኛል፡፡ ሆኖም ግን ሥራ የጀመርኩት ሰኔ 3 ቀን 2008 ዓ.ም ነው፡፡ ሥራውንም የጀመርኩት በብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ጸሎትና ቡራኬ ሲሆን የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ከፍተኛ የሆነ አቀባበል አድርገውልኛል፤ቅዱስ አባታችንም ሁሉም ተግባብቶ፣ ተስማምቶና ተደማምጦ ቤተ ክርስቲያንን እንዲአገለግልና አስተዳደራዊ ሥራውን እንዲሠራ አባታዊ መመሪያ፣ ምክርና ቡራኬ ሰጥተዋል፡፡
ስለዚህ ሥራው በቅዱስነታቸው ጸሎትና ቡራኬ ተጀምሯል ማለት ነው፤ በዚህም ላይ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያው ኃላፊዎችና ሠራተኞች ያደረጉልኝ ደማቅ አቀባበል ፍቅራዊ ደስታ የተሞላበት ስለነበር ላደረጉልኝ አቀባበል ከልብ ላመስግን እወዳለሁ፡፡ ገና ወደ ሥራው ገባሁ እንጂ ይህንን ሠርቼአለሁ የምለው ነገር አይኖርም፡፡
ወደፊት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እሠራለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ምንም መሥራት ስለማንችል ነው፤ እግዚአብሔር በረዳንና ባገዘን መጠን ነው ልንሠራ የምንችለው፤ እኛ የእሱ ምልእክተኞች ነን፡፡
ቀጣዩን ሥራ በተመለከተ ከመምሪያ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተናል፤ ሁሉም በየመምሪያው ተግቶ እንዲሠራ የሥራ መመሪያ ሰጥቻለሁ፤ ሁሉም መምሪያዎች የሥራ እቅድ አዘጋጅተው እንዲአቀርቡ፣ የታቀደውንም ዕቅድ ተከታትለው እንዲአስፈጽሙ፣ ከእኛ የሚጠበቀውን ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን ማድረግ እንዳለብን በማስገንዘብ የሥራ መመሪያ ተሰጥቷል፡፡ ከዚህም ጋር የእያንዳንዱን  መምሪያ የቢሮ ይዘቱን አስመልክቶ የጉብኝት ሥራ ሠርቻለሁ፡፡ በስብከተ ወንጌል አዳራሽ ሁሉም ሠራተኛ ተሰብስቦ በድጋሚ ለሁለተኛ ጊዜ አጠቃላይ የሥራ መመሪያ ሰጥቻለሁ፡፡ በቀጣዩም ምን መሥራት እንዳለብን ከሠራተኛው አሳታፊ የሆነና ነፃነት ባለው መንገድ ሠራተኛው ሐሳብ እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡
ምክንያቱም ሥራውን የሚሠራው ሠራተኛው ስለሆነ ምን መሥራት እንዳለበትና ለወደፊትም ለሥራችን ግብአት እንዲሆነን ሰፊ የሆነ ሐሳብ እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡
ስለዚህ ያንን በተግባር ለማዋል ቅድመ ዝግጅት እያደረግን ነው ያለነው፡፡ በልማት ዙሪያ ያለኝ ሐሳብ የቀደሙ አባቶቻችን ቤተ ክርስቲያን እንጡራ ሐብት እንዲኖራት በማሰብ ብዙ ቤቶችንና ሕንጻዎችን አውርሰዋል፤ በዚሁ ላይ ወቅቱን ተከትለን የገቢ ምንጭ የሚሆን ልማት እንሠራለን ብለን እናስባለን፡፡
ምክንያቱም ቤተ ክርስተያኒቱ በኢኮኖሚ እንድታድግ የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን፡፡ ይህም አንዱና መሠረታዊ ሐሳባችን ነው፤ ይህንንም ለመሥራት የኢኮኖሚስት ባለሙያዎችን ለመሰብሰብ እየተንቀሳቀስን ነው፤ ቤተ ክርስቲያናችን ባዕለ ጸጋ እንደመሆንዋ መጠን በውስጥዋ የሌለ ምሁር የለም፤ ሥጋዊ ትምህርትም መንፈሳዊ ትምህርትም የተማሩ ልጆች አሉአት፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ሀብታም እንጂ ድሀ አይደለችም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ጸጋ ተጠቃሚዎች እኛው ነን፡፡ ሌላውም ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ መንቀሰቀስ ይጠበቅብናል፤ እግዚአብሔር ድርሻውን ተመጥቷል፤ እኛም ለቤተ ክርስቲያኒቱ ልናበረክተው የሚገባ ድርሻ አለንና ድርሻችንን እናበረክታለን፤ ከምዕመናን የኢኮኖሚ አማካሪዎች በበጎ ፈቃድ  ሥራውን ሊሠሩልን እንዲችሉ እነሱን ለማሰባሰብ በጉዞ ላይ እንገኛለን፡፡
ሌላው መሠረታዊ ነገር የአሠራር ለውጥ እንዲኖር ማድረግ ሲሆን ቤተ ክርስቲያን ከወቅቱ ጋር ተራማጅ እንድትሆን፣ ሠራተኛው ከወቅቱ ጋር እንዲራመድ ለማድረግ ወቅቱ የወለደውን ዕቅድ ማቀድ ነው፤ ድሮም አባቶቻችን ቤተ ክርስቲያን ዘመን ተሻጋሪ እንድትሆን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ዕቅድ እያቀዱ ለእኛ የሚበጅ ነገር ሠርተውልን አልፈዋል፤ እኛም ደግሞ ከዘመኑ ጋር የሚሄድ አሠራር መሥራት ከቻልን ቤተ ክርስቲያኒቱ ዘመን ተሻጋሪ ልትሆን ትችላለች፤ ይህ ካልሆነ ግን ትውልዱ ትቶን ሊሄድ ይችላል፤ የዘመኑ ትውልድ የዘመኑን ጥያቄ ነው የሚፈልገው፤ የዘመኑ ጥያቄ ደግሞ የልማት ጥያቄና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ፣ የኢኮኖሚ ብልጽግና ጥያቄ፣ በአንድነት የመጓዝ እና የመሳሰሉትን ዘመኑ ይጠይቃል፡፡
ስለዚህ በእነዚህ ጥያቄዎች ዙሪያ በዕቅድ ለመሥራትና ለመጠቀም በተቻለ መጠን እንቅስቃሴ እናደርጋለን፡፡ ይሁን እንጂ ከኛ በፊት ሥራ አልተሠራም ማለት አንችልም፤ ሥራ ተሠርቷል፤ አሁንም ደግሞ በበለጠ ተጠናክሮ እንዲሠራ መልካም አስተዳደርን በማስፈን፣ የአጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅዳችንን በማቀድ በዚህ ተንተርሰን ሥራዎችን ለማከናወን እያሰብን ነው ያለነው፡፡
ኆኅተ ጥበብ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
የወቅቱን የኑሮ ውድነት መነሻ በማድረግ በመንበረ ፓትርያርክ ሥር የሚገኙ ሠራተኞች ቀደም ሲል በነበሩት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ዘመን ጥያቄ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም ጥያቄው ግን ሳይመለስ ቆይቷል፡፡
ይሁን እንጂ ጥያቄው ብፁዕነትዎ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ  በሆኑበት ወቅት ሊመለስ ችሏል፤ ይህም ሠራተኛውን ያስደሰተ መሆኑ ይታወቃል፤ በዚህ የደመወዝ የማስተካከያ ሥራ የብፁዕነትዎ ሚና ምን ነበር?
ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ
በመጀመሪያ ደመወዝ የሚመደበው ለሥራ ነው፤ ሰው የሚቀጠረውም ለሥራ ነው፤ ደመወዝ የሚከፈለውም ለሥራ ነው፤ ለሥራው ደመወዝ ከተመደበ ሥራውን የሚሠራው ሰው ስለሆነ ያ ሰው ደግሞ ተመጣጣኝ ገቢ ማግኘት አለበት፤ “ነፍስ ርህብት ወነፍስ ድህንት እንተጸግበት ተአኩተከ” እንደተባለው ሰው ካልበላ መንቀሳቀስ አይችልም፤ መኖርም አይችልም፤  ሰው ሳይበላ መንቀሳቀስ እንደማይችል እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ሰውን ከመፈጠሩ አስቀድሞ ምግቡን ነው ያዘጋጀለት፤ ይህም ማለት ሰው ከመፈጠሩ በፊት በጀት ተፈጥሯል ማለት ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው በመጨረሻ ላይ ነው፤ አዝርዕቱም፣ አትክልቱም፣ ዕፀዋቱም እንስሳቱም፣ በምድር የሚሽከረከሩ፣ በሰማይ የሚበሩ ሁሉ የተፈጠሩት ከሰው በፊት ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ከተሟሉ በኋላ በመጨረሻ  ሰው ተፈጠረ፡፡
ስለዚህ ሰው ያለበጀት አልተፈጠረም፡፡ በባህላዊ አነጋገር ያርባ ቀን ዕድል የሚባለው የተፈጥሮ በጀት ይመስላል፡፡ ሰው እያገኘ ድርጅቱም እንዲአገኝ ማድረግ አለበት፡፡ በበለጠ ደግሞ በሥራ ላይ የተሠማራ ሰው ከገንዘቡ ይልቅ ሞራሉ ነው የሚአስደስተው፤ ትንሽም ይሁን ብዙ ሞራል ካለና ሞሯሉ ከተጠበቀለት ማንም ሰው ሥራውን ተግቶ ይሠራል፡፡ አሁን የተጨመረው ደመወዝ የሠራተኛውን ችግር ይቀርፋል ማለት ሳይሆን አቅም በፈቀደ    ሠራተኛው  በተስፋና በሞራል እንዲሰራ ታስቦ የተደረገ ጭማሪ ነው፡፡ የደመወዙ መጨመር ለእኔ ደስታን ፈጥሮልኛል፡፡ ከእኔ በፊት የነበሩት ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅም ጥናቱ እንዲጠና አስዝዋል፤ተግባራዊነቱ ግን አልነበረም፡፡
ስለዚህ ያንን ጥናት ነው እኔ ያገኘሁት ጥናቱን ሳገኝ ግን ይህ መሆን አለበት ብዬ የሠራተኛው ኑሮ አነስተኛ መሆኑን በመገንዘቤ ጉዳዩን ጊዜ ወስጄ ላጥና አላልኩም፤ገንዘብ ሥራ ማስኬጂያ እንጂ አምላክ አይደለም፡፡ ሥራችንን ለመሥራት ቤተ ክርስቲያንንም በኢኮኖሚ ለማሳደግ ወደ ልማት ለውጥ ለመሸጋገርም የምንችለው ሠራተኞቻችንን ስናበረታታና ተስፋ እንዲኖራቸው በርቱ አይዞችሁም ስንላቸው ነው፡፡ በዚህ መሠረት ጉዳዩን ለቅዱስነታቸው በመሸኛ ደብዳቤ ያቀረብን ሲሆን ቅዱስ አባታችንም ፈቃደኛና ደስተኛ ሆነው ከቋሚ ሲኖዶስ ጋር በመነጋገር የሠራተኞውን ችግር ሙሉ በሙሉ ይቀርፋል ባይባልም መጠነኛ ጭማሪ ተደርጓል፡፡ የሠራተኞቹ መጠቀም የእኛ መጠቀም ማለት ነውና፡፡  ሥራውን በጀመርኩበት ወቅት ሠራተኛው የደመወዝ ጭማሪ በማግኘቱ ከፍተኛ ደስታ ነው የተሰማው፤ ወደ ፊትም እንደ የግብሩ እና እንዳየ ወቅቱ እያየን ለቅዱስ ሲኖዶስና ለቅዱስ አባታችን እየቀረብን የቤቱንም ችግር እያየን አቅም በፈቀደ የሠራተኛውን ችግር ለመቅረፍ እንቀሳቀሳለን፡፡
ኆኅተ ጥበብ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
እንደሚታወቀው ሁሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቤተ ክርስቲያናችን ዓለም አቀፍ የ24 ሰዓት የቴሌቪዥን ሚድያ እንዲኖራት ተደርጓል፤ በሥራው ሂደት ላይ ግን አንዳንድ ሥጋቶች ይወራሉ ይህም ፕሮግራሙ 24 ሰአት በመሆኑ በቂ ዝግጅት /ግብአት/ አለ ወይ? በቂ የሰለጠነ  የሰው ኃይል  አለ ወይ? የሚል ነው በዚህ ዙሪያ ብፁዕነትዎ ምን ይላሉ?
ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ
በቅድሚያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ምዕመናንና ካህናት እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ፤ ምክንያቱም ወቅቱ የፈቀደው ሥራ በመሥራቱ ነው፤ ቤተ ክርስቲያንዋ ተጣጥራ ከዚህ ደረጃ መድረሷ ራሱ አንድ ትልቅ ደስታ ነው፤ ምን ጊዜም ሥራ ሲጀመር መደነቃቀፉ አይቀርም፡፡ ይህም የሚሆነው የልምድ ማነስ ስለሚኖር ነው፤ ማንኛውም ነገር ሲጀመር ጨለማ መስሎ ነው የሚታየው፡፡ ያዋጣ ይሆን? አያዋጣ ይሆን? እዛለቀው ይሆን? ያሸንፈኝ ይሆን? አሸንፈው ይሆን በሚል ጥርጣሬ ውስጥ በመግባት ነው ሥራው የሚጀመረው ሆኖም ግን እየተገፋ ሲሄድ ሥራውም ሲለምድ፣ ሰሪውም ሲለምድ ጥሩ ውጤት ላይ መድረስ ይችላል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ይህንን ሚድያ ስትከፍት በመጀመሪያ እግዚአብሔርን  በማመን ነው፡፡ የሥራው ባለቤት እግዚአብሔር ስለሆነ፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ማህበረ ምዕመናንን በጀት በማድረግ ነው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሀብት በሀገር ውስጥ ያሉት ምዕመናንዎቿ ብቻ እንጂ የውጭ ፈንድ እርዳታ የምታገኝ ቤተ ክርስቲያን አይደለችም፡፡ ምዕመናን በሚአደርጉት የአሥራት በኩራት  አስተዋፅኦ ነው የምታገኘው፡፡
ስለዚህ ይህንን መሠረት አድርጋ ነው መንፈሳዊ አገልግሎቷን እያከናወነች ያለችው፡፡ እንደ እኛ ሐሳብ ቤተ ክርስቲያኒቱ አቅም አላት፣ ትችላለች ብለን ነው የምናምነው፡፡ ሥርጭቱ 24 ሰአት መሆኑ ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያን ሀብት ብዙ ነው፤ የገዳማቱን፣ የአድባራቱን፣ የሊቃውንቱን፣ የሰንበት ት/ቤቱን ብዛት ስንመለከት 24 ሰዓትም ያንሳታል፡፡ የሚአቀነባብር የሰው ኃይል በየጊዜው እያሳደግን እንሄዳለን፡፡ ሁሉም በየጥቂቱ እያለ ነው ያደገው፤ ልምድ ይዞ የሚወለድ የለም፤ ስለዚህ ሚድያው የተከፈተው እግዚአብሔርን በማመን ስለሆነ ወደ ኋላ የሚባል ነገር የለም፡፡ ሥጋትም አይግባችሁ፡፡
ኆኅተ ጥበብ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአጼዎቹ ዘመን በመነገሥታቱ፣ በመሳፍንቱ፣ በመኳንንቱ በባለሐብቱ፣ መልካም ፈቃድ በርካታ ቤቶችና ሕንጻዎች በስጦታ የተበረከቱላት ቢሆንም እነዚህ የስጦታ ሀብቶቿ በደርግ ዘመን ተወርሰውባት ሲኖሩ በአሁኑ መንግሥት ደግሞ የተወረሱባት በርካታ ቤቶችና ሕንጻዎች ተመልሰውልታል፡፡ ያልተመለሱላትም  እየታመለሱላት ይገኛሉ፤ እነዚህን ቤቶችና ሕንጻዎች እንዲአስተዳድር (እንዲመራ) የተቋቋመው ድርጅት በአስተዳደር ሂደቱ ዙሪያ አንድ አንድ ችግሮች እየተከሠቱ መሆኑ ይነገራል፡፡
በቅርቡ ባንኮድ ሮማ በሚባለው አካባቢ የተነገነባውን ሕንጻ ምክንያት በማድረግ በድርጅቱ በተዘጋጀው መጽሔት ላይ አንድ አንድ አወዛጋቢ ጽሑፎች በመታየታቸው በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በኩል በሚገኙ የመምሪያ ኃላፊዎች የተቃውሞ ጥያቄ እንደተነሳም ይወራል፡፡ በዚህ ጉዳይ ብፁዕነተዎ ምን ይላሉ?
ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ
በዚህ ጉዳይ ሁለት ነገሮችን ለማንሳት እወዳለሁ፡፡ አባቶቻችን ለገዳማቱና ለአድባራቱ፣ ለአብነት ት/ቤቱ፣ አስበው ራሱን የቻለ የገቢ ምንጭ እንዲኖራት ሠርተው በማለፋቸው የቀደሙት አባቶቻችንን አመሰግናለሁ፡፡ በቤቶችና ሕንጻዎች መመለስ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያን ልናመሰግናቸው ይገባናል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ቤቶች የተመለሱት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዘመን ፕትርክና ነው፡፡
ያለፈውን ታሪክ እንቅበር ብንለው ሊቀበር አይችልም፡፡ ታሪክ አይሞትም የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዘመን ብዙ ቤቶች ተመልሰዋል፡፡ በብፁዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ ማትያስም ዘመነ ፕትርክና በመመለስ ላይ ያሉ ቤቶች አሉ፡፡ የተመለሱ ቤቶችም አሉ፡፡ ለቤቶቹ መመለስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው ያለው፡፡
ሌላው ተመስጋኝ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግሥት ነው፡፡ የደርግ መንግሥት የቤተ ክርስቲያንን ሐብትና ንብረት ወሰደ፡፡ የኢሀደግ መንግሥት ሲመጣ ደግሞ የተወሰደውን ሐብትና ንብረት መልሶላታል፡፡
ቤተ ክርስቲያኗ ምንም አይነት ገቢ እንደሌላት መንግሥት አርቆ በማሰብ ንብረቷ እና ሐብቷ ሊመለስላት ይገባል ብሎ በመመለሱ ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግሥት ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡ ለምስጋናችንም ወሰን የለውም፡፡
አስተዳደሩ ላይ ስንሄድ ግን መልካም ነገርም ሊኖር ይችላል፤ መልካም ያልሆነ ነገርም ሊኖር ይችላል፡፡
ምክንያቱም ሁለቱም ጎን ለጎን የሚሄዱ ናቸው፡፡ ደካማ ጎን እና ጠንካራ ጎን አብረው ነው የሚሄዱት፡፡ ሰው መታገል ያለበት ጠንካራ ጎኑን ለማጎልበት ደካማ ጎኑን ለማስወገድ ነው፡፡ ችግሮቹ ሊኖሩ ይችሉ ይሆናል? ነገር ግን በሥራ ሂደት ገብቼ ስላልፈተሸኳቸው ሙሉ በሙሉ ጥፋት አለ ብዬ ለመናገር አያስችለኝም፡፡ ማን ይናገር የነበረ ነውና፡፡ ባላየሁት፣ ባልደረስኩበት፣ ባላጠናሁት፣ ባልመረመርኩት ላይ ገብቼ ይሄ ጠፍቷል ይሄ ለምቷል ለማለት የሚያስችለኝ ነገር አይደለም፡፡ ወደ ፊት ግን ሥራ ስለጀመርኩ ያየነውን እንመሰክረለን የሰማነውን እንናገራለን እንደተባለው ባየሁትና በሰማሁት ነገር ላይ ተጨባጩን ለመናገር እችላለሁ፡፡ አሁን ግን በዚህ ጉዳይ ላይ በማላውቀው ገብቼ መናገር ህሊናዬ አይፈቅድልኝም፡፡ በመምሪያ ኃላፊዎች ላይ የተጻፈውን ጽሑፍ አላየሁትም እኔ ከመምጣቴ በፊት ተደርጎ ከሆነ አላውቅም፡፡ ግን እንደዛም ቢሆን ከታች ያለው ለበላይ፣ ከላይ ያለው ለበታች መነቃቀፉ ለቤተ ክርስቲያን አይጠቅምም፡፡ መነቃቀፉ ግንባታም አይደለም፡፡ ልማትም አይደለም፡፡ ለልማት፣ ለእድገትና ለለውጥ ከሆነ መነቃቀፉ ያስኬዳል ጥሩ ነው፡፡ ዝም ብሎ መነቃቀፍ ከሆነ ግን ምንም ስለማይጠቅም ከእኔ ጀምሮ ማንኛውም ሰው ሰውን መንቀፍ ክርስትናም አይደለም፡፡ ክርስትናም ወንድማማችነት ነው፡፡ ክርስትናም መተሳሰብ ነው፡፡ ክርስትና ደካማውንም ጭምር መሸከም ነው፡፡ ብሎም መጸለይ ነው፡፡ ለውጥ የማያመጣ መነቃቀፍ ግን አግባብነት ይኖረዋል ብዬ አልገምትም፡፡ ይህን የምለው እንደ አስተያየት ነው እንጂ አይቻለሁ ሰምቻለሁ ብዬ አይደለም፡፡
ኆኅተ ጥበብ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
የሚያስተላልፉት መልእክት አለ
ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ
የማስተላልፈው መልእክት በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያናችን የሁሉ እናት ናት፡፡ የስነ ጽሑፍም፣ የስነ ጥበብም፣ የስነ ሕንጻም፣ የፍልስፍናም ባለቤት ናት፡፡ ሁለተናዋ የሚያኮራ ሕይወት ያላት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ሁለተናዋ ውብና ክብር ነው፡፡ ሆኖም ግን ያሁኑ ትውልድ ቴክኖሎጂው እያደገ ስለሆነ ግሎባላይዜሽን የሚባለውን ባህል ተከትሎ የውጭ ባህል ወደ ሀገራችን እየገባ ትውልዱን እየወረረ ስለሚገኝ ጠቃሚውን ባህል ትውልዱ ይዞ እንዲሄድ በስነ ምግባር፣ በመንፈሳዊነት ታንጾ እንዲጓዝ ማድረግ ስለሚጠበቅብን ቤተ ክርስቲያናችን በመልካም አስተዳደር ላይ ተመሥርታ ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት ለትወልዱ ተደራሽ መሆን ያስፈልጋታል፡፡ ለሕፃናቱ፣ ለአዛውንቱ፣ ለወጣቱ ለሁሉም ሕይወት መጠበቅ የቤተ ክርስቲያን ሥራ ነውና፡፡ ተደራሽ እንድትሆን ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት አለባት፡፡ ሁሉም ሰው የወንጌል አገልግሎት እንዲያገኝ መሆን አለበት፡፡ ሰው ወንጌል ከተማረና በእምነት ካለ አይደለም ለመንፈሳዊ መሪዎች ለፖለቲካ መሪዎችም አያስቸግርም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል አስሮ ይይዘዋል፡፡ አጢኃት እንዳይሠራ፣ በደል እንዳይፈጽም፣ ችግር እንዳያደርስ የእግዘአብሔር ቃል ይገስጸዋል፡፡ ሰዎች በሰዎች ላይ ችግር የሚፈጥሩት የእግዚብሔርን ቃል ባለ መገንዘባቸው ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል በስፋት ስላልተዳረሰም ሊሆን ይችላል፡፡ ሀገርን ሰላም ለማድረግ፣ ለራስም በሰላም ለመኖር፣ የተስተካከለ እና የታነጸ ሕይወትን ይዞ ለመጓዝ ስብከተ ወንጌል ያስፈልጋል፡፡ የሚዲያችንም ሆነ የጉዞአችን መቅድም ስብከተ ወንጌል ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ስብከተ ወንጌልን አልሰበከችም ማለት ግን አይደለም፡፡ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማለት ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስብከተ ወንጌልን ያስተማረ የለም፡፡ ሰዎች እንደሚያወሩት አይደለም፡፡ ይህንን ሁሉ ሕዝብ አማኝ ሆኖ እንዲቆይ በስብከተ ወንጌል ይዛ የቆየች ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ አባቶቻችን አስተምረዋል፣ መክረዋልም እኛም ድርሻችንን ልንወጣ ይገባናል፡፡ ስብከተ ወንጌል ነፍስ አድን እና ሕይወተ አድን ስለሆነ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ አጠናክረን መሥራት አለብን፡፡ ስብከተ ወንጌል ፍቅርንና አንድነትን ያመጣል፡፡ መተሳሰብን እና መተዛዘንን ያመጣል፡፡ መረዳዳትንም ያመጣል፡፡ ስብከተ ወንጌልን የተማረ ሰው ለሀገሩ ይቆረቆራል፡፡ ለእህቱ ለወንድሙ ያዝናል፡፡
ስለዚህ በስብከተ ወንጌል ላይ ትኩረት ማድረግ አለብን፡፡ በገንዘብ እና በጉልበት አስተዋፅኦ በማድረግ ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት አለብን፡፡ የቤተ ክርስቲያን ዋና ሥራዋ ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት ነው፡፡ ሌላው ሥራ ግን በትርፍ የሚሠራ ሥራ ነው፡፡ ስብከተ ወንጌል ላይ ትኩረት አድርገን ከሠራን አትራፊ እንሆናለን፡፡ መክሊታችን እንዲበዛ ስብከተ ወንጌልን በጽሑፍም ይሁን በሚዲያ ጭምር ማጠናከር አለብን፡፡
 ኆኅተ ጥበብ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
ብፁዕ አባታችን ስለሰጡን አባታዊ ማብራሪያ ከልብ እናመሰግናለን፤ ቀጣዩ የሥራ ዘመነዎ የስኬት ዘመን እንዲሆንለዎ እንመኛለን፡፡