በእንጠጦ ሐመረ ኖኅ ቅ/ኪዳነ ምሕረት አንድነት ገዳም የተገነቡ ሕንጻዎች በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ተባርከው ተመረቁ

በሐመረ ኖኅ ቅ/ኪዳነ ምሕረት አንድነት ገዳም የተገነቡ ባለ አንድ ወለል (G+1) ተግባረ እድ እና (G+5) ሁለገብ ሕንጻ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ተባርከው ተመርቀዋል
በምርቃቱ መርሐ ግብር ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ በምስራቅ ትግራይ የዓዲ ግራት ሊቀ ጳጳስ፣ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ፣ የመንበረ ፓትርያርክ የመምሪያ ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ የገዳሙ አስተዳዳሪ ጸባቴ አባ ወልደ ማርያም አድማሱ ካሳዬ(ቆሞስ)፣ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የገዳሙ ሊቃውንት፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና በርካታ ምእመናን ተገኝተዋል
የገዳሙ አስተዳዳሪ ፀባቴ አባ ወልደ ማርያም አድማሱ ካሳዬ ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነም አንዳችስ እንኳ ያለ እርሱ አልሆነም በማለት የእርሱን ፈቃድ አስቀድመን ሕንጻው ለመሥራት ተነሣን፤ በዚህ መሠረት ሕንጻው ሕዳር አጋማሽ 2011 ዓ/ም ተጀምሮ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ተጠናቆ በዛሬ ዕለት ለምርቃት እንደበቃ ገልጸዋል። አክለውም በግንባታው ሥራ ላይ የተሳተፉትን በሙሉ አመስግነው ዋጋ ከፋዩ እግዚአብሔር የድካማችሁን ዋጋ ይክፈልልን፣ እድሜና ጤና ያድልልን ብለዋል።
በመጨረሻ ንግግራቸውም የተመረቀ ሁለገብ ሕንጻ የመጠሪያ ስም እንዲሰጠው ለቅዱስነታቸው ጠይቀዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ሕንጻዎቹን ተዘዋውረው የጎብኙ ሲሆኑ ይህንን ሕንጻ እንዲሠራ የፈቀደ እግዚአብሔር ይመስገን ካሉ በኋላ እንኳን ለዚህ አምሮና ደምቆ የሚታየው ሕንጻ ለማየት አበቃችሁ ብለዋል። አያይዘውም በዚህ በተቀደሰ ስፍራ ይህንን የሚመስል በጣም የሚያስደስትና የሚያስደንቅ ልማታዊ ሥራ መሠራቱ ደስ የሚያሰኝ መሆኑን ገልጸው ልማቱ የተሠራው በገዳሙ ሰላምና ፍቅር ስላለ ነው ብለዋል።
ቅዱስነታቸው ገዳሙ ትልቅ በመሆኑ እንዲሁም ሰፊ ቦታው ስላለው በቦታው ሰፋ ያለና ግዙፍ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን እንዲሠራ አባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል። ለዚህም የገዳሙ አስተዳዳሪ ፀባቴ አባ ወልደማርያም አድማሱ ካሳዬ ይሠሩታል ብዬ አምናለሁ ብለዋል።
በመጨረሻም የገዳሙ አስተዳዳሪ የተመረቀው ሁለገብ ሕንጻ ስም እንዲወጣለት ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ቅዱስነታቸው ሕንጻው “ቤተ አብርሃም” ብለው ሰይመውታል።