በአጭር ጊዜ ተሠርቶ የተጠናቀቀው የደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ተባረከ

በአጭር ጊዜ ተሠርቶ የተጠናቀቀው የደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተባርኮ ተመርቋል።

በየካ ደ/ምሕረት ኪዳነ ምሕረት እና መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሲሠራ የቆየ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶ በመጠናቀቁ በዛሬ ዕለት በርካታ ምእመናን በተገኙበት ተመርቋል።

ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ የተሠራበት ቦታ ከፍ ያለ በመሆኑ፣ ከመልክዓ ምድራዊና አቀማመጡ አንጻር ቤተ ክርስቲያኑ ደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ተብሎ ተሰይሟል። ብፁዕነታቸው ስለ ስያሜው ሲያብራሩም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጅ ለማዳን ሲል ከፍ ባለ ቦታ በቀራንዮ ተሰቅሎ ስለ አዳነን መሆኑን ገልጸዋል።

ብፁዕነታቸው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ጸሎት የሚደረግበት፣ የእግዚአብሔርን ሥራ የሚሠራበት እና ሰውና እግዚአብሔርን የሚገናኙበት መሆኑን በመግለጽ ቤተ ክርስቲያኑ እንዲታነጽ በቆራጥነት ለመሩት ለቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ መ/ምሕረት ተክለወልድ የማነወልድ እና የየራሳቸውን ድርሻ ላበረከቱ ለሁሉም ከልብ አመስግነዋል።

በመጨረሻም ብፁዕነታቸው የታነጸው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ውብና አስደናቂ መሆኑን በመግለጽ፡ ሁላችን ንስሐ ገብተን፣ በቤተ ክርስቲያኑ እየተገለገልን ለእግዚአብሔር የምንታዘዝና የምንመች በመሆን፣ መንፈሳዊ ሕይወታችን አስተካክለን በፍቅር፣ በንጽህና፣ በቅድስናና በሰላም እየተመላልስን ለዘለዓለማዊ ሕይወት ተዘጋጅተን ልንኖር ያስፈልጋል ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በነገ ዕለት ደግሞ ቅዳሴ ቤቱ በማኅሌት፣ በቅዳሴና በተለያየ መንፈሳዊ አገልግሎት እንደሚከበር ተገልጿል።

በመምህር ኪደ ዜናዊ