በአዲስ አበባ ገዳማት እና አድባራት ልዩ የስብከተ ወንጌል የአንድነት ጉባኤ መርሐ ግብር ተጀመረ
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልዕኮ ዋና ክፍል አስተባባሪነት የተጀመረው የአድባራት እና ገዳማት የአንድነት ጉባዔ የተጀመረው የካቲት 11 ቀን 2006 ዓ.ም በቦሌ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ ሲሆን ጉባዔው እስከ ሰኔ 30 ቀን 2006 ዓ.ም ድረስ የአንደኛው ዙር ጉባዔ ይካሄዳል፡፡ የአንድነት ጉባዔው በምድብ እየተመደበ የሚካሄድ ሲሆን አንድ ምድብ ከሶስት አድባራት እስከ አስር አድባራት የሚያጠቃልል የምድብ ይዘት ነው፡፡
የአንድነት ጉባኤው ቀደም ሲል ሲካሄድ የነበረ ሲሆን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሰባት ክፍላተ ከተሞች መከፈሉን ተከትሎ ለተወሰነ ጊዜ የአንድነት ጉባዔው ተቋርጦ የነበረ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ይሁን እንጂ የሰባቱ ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት አደረጃጀታዊ መዋቅር ከተጠናከረ በኋላ የአንድነት ጉባዔው ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት ምዕመናንን ወደ ንስሐ ለማቅረብና በሃይማኖታቸው ጸንተው እንዲኖሩ ለማድረግ የአንድነቱ ጉባኤ መቀጠል ጠቀሜታው እጅግ የጎላ በመሆኑ የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊዎች እና የሀገረ ስብከቱ ስብከተ ወንጌል ዋና ክፍል ባደረጉት የጋራ ምክክርና ውይይት ቀደም ሲል ተጀምሮ የነበረው የአንድነት ጉባዔ በማህበረ ካህናትም ሆነ በማህበረ ምዕመናን ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የነበረ መሆኑን በማውሳት ለወደፊቱም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል በማለት ስምምነት ላይ የተደረሰ በመሆኑ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም በጉዳዩ ላይ የተስማማ ስለሆነ ለሁሉም አድባራት ባስተላለፈው መመሪያ መሰረት የአድባራት እና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፍያን፣ የሰበካ ጉባዔ ምክትል ሊቃነ መናብርት፣ የቁጥጥር ሠራተኞች፣ ሒሳብ ሹሞች፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ የሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች የጋራ ምክክር በማድረጋቸው የአንድነቱ ጉባዔ የጌታችንን እና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ ጾም ምክንያት በማድረግ ጉባዔው በሰባቱም ክፍላተ ከተሞች ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑን በየአድባራቱ እና በየገዳማቱ ከተደረጉት ጉባዔያት ለመረዳት ተችሏል፡፡ የአንድነቱ ጉባዔ የሚካሄድባቸው ቀናት በየሳምንቱ ቅዳሜ እና እሁድ እየተከተለ ሲሆን በተለይም በርካታ ምዕመናን የሚገኙባቸውን ወርህ በዓላትን እና የዓመት በዓላትን ምክንያት በማድረግ ነው፡፡ ጉባዔው የሚጀምረው እንደ አካባቢው ቢለያይም ዋና መነሻው ከቀኑ አስር ሰዓት ነው፡፡
መጨረሻው ደግሞ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ተኩል ሲሆን ነው፡፡ ለጉባዔውም ክብር ሲባል ተረኛው ደብር ዩኒፎርም የለበሱ ወጣቶች የጉባዔው አስተናባሪ እንዲሆኑ የአንድነቱ መርሐ ግብር ይደነግጋል፡፡ የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱን እንዲሰጡ የሚጋበዙት የወንጌል መምህራን በአድባራት እና ገዳማት ጽ/ቤት ጠያቂነት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ በየአድባራቱ እና ገዳማቱ ተመድበው የሚያገለግሉ ሰባክያነ ወንጌል እና በትሩፋት የሚያገለግሉ የወንጌል አገልጋዮች ናቸው፡፡ የአንድነት ጉባዔውን ታላቅነት በማሳየት መርሐ ግብሩ የሚጀመረው በጸሎተ ወንጌል እና በማዕጠነት ነው፡፡
ሊቃውንት መዘምራንም ጥንግ ድርብ ለብሰው ያሬዳዊ ዜማ ያቀርባሉ፡፡ መነሻውን ከመንበረ ፀበኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ያደረገው ይህ ዐቢይ የአንድነት ጉባኤ በተለያዩ አድባራት እና ገዳማት እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን ከመጋቢት 20 – 21 ቀን 2006 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱስን ማርያም ገዳም ቤተ ክርስቲያን የተካሄደውን ጉባኤ የዝግጅት ክፍላችን ከቦታው ድረስ በመገኘት እጅግ በደመቀ መልኩ የተከናወነ መሆኑን ለመረዳት ችለናል፡፡
የአራዳና ጉለሌ ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ትጉኃን ታጋይ ታደለም በጉባኤው ላይ ተገኝተው የሚከተለውን መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ አበው አባቶቻችን ባቆዩልን መሠረት ከ2000 ዓመት በፊት ጀምሮ ቤተ ክርስቲያናችን ወንጌልን ያስተላለፈችልን መሆኑ ይታወቃል፡፡
የወንጌልን አገልግሎት ያቋረጠችበት ጊዜ የለም ወደፊትም እስከ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምጽአት ድረስ የሚቀጥልና የሚቆይ ነው፡፡ ይህ የወንጌል አገልግሎት የአንድነት ጉባኤ ተብሎ በአዲስ አበባ ከተማ ይጀመር እንጂ ዋና ዓለማው በገጠሪቱ ያለውን መንፈሳዊ አገልግሎት ለማጠናከር ታስቦ ነው የተቋቋመው፡፡ በአሁኑ ሰዓት የገጠሪቱን ቤተ ክርስቲያን በስብከተ ወንጌል መንፈሳዊ ዘርፍ ለማጠናከር ቅዱስ ሲኖዶስ ቤተ ክርስቲያን ባላት ዘርፈ ብዙ አገልሎት ተቀዳሚ ተግባሯ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ነው፡፡ ስለዚህ በምናገኘው ሁሉ አጋጣሚ ይህንን የስብከተ ወንጌልን አገልግሎት ለምዕመናን ወራትን እና ዓመታትን ጠብቆ ወንጌልን ከመስበክ ባሻገር በየቀኑ ወንጌልን በመስበክ ምዕመናን በሃይማኖታቸው እንዲጠናከሩ ማድረግ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከታችን በአራዳና ጉለሌ ክፍላተ ከተማ በአምስት ምድብ የተመደቡ 20 ገዳማት እና አድባራት አሉ፡፡ ሰሜን፣ ምዕራብ፣ ደቡብ እና ምሥራቅ እንዲሁ ማዕከል ተብለው ተደራጅተዋል፡፡ ዛሬ ይህን ጉባኤ ያዘጋጁ የቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳምን ጨምሮ ካቴድራል ቅድሥት ሥላሴ፣ ታዕካ ነገሥት ልደተ ለማርያም፣ መንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል እና የቀበና ምሥራቀ ፀሐይ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን እነዚህ አምስቱ አብያተ ክርስቲያናት በማዕከል ደረጃ የተመደቡ ናቸው፡፡ ሁሉም አድባራት እና ገዳማት በየተራው ጉባኤውን ያካሄዳሉ፡፡ ዓላማችን ወንጌልን ማድረስ ብቻ አይደለም፡፡ ምዕመናን በአንድነት ተሰብስበው ንስሓ እንዲገቡ ማድረግ ነው፡፡ ምዕመናን ወንጌል ከገባቸው ምን እናድርግ ይላሉ፡፡
ስለዚህ ክፍለ ከተማችን ከያዘችው ዕቅዶች መካከል በገጠሪቱ ሀገራችን በመናፈቃን ተወረው የሚገኙት አብያተ ክርስቲያናትን በወንጌል መታደግ መቻል ነው፡፡ በሌላ መልኩ ወንጌልን በአውደ ምሕረት ብቻ ሳይሆን በእስር ቤት ያሉ ታራሚዎችን፣ በአልጋ ቁራኛ የወደቁትን የማፅኛ ሥራ ለመሥራት ታልሞ የተሠራ ነው፡፡ ስለዚህ በቅርብ ጊዜ ከብፁዓን አባቶች ጋር በመመካከር ሥራውን እንጀምራለን፡፡ ድሆችንም በልብስ እና በምግብ ራሳቸውን የሚረዱበት ተግባር ለማድረግ እናስባለን፡፡ ምዕመናንም ይህንን ተግባር እንዲደግፉት ይገባል በማለት ሊቀ ትጉኅን ታጋይ ታደለ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በመጨረሻም የቀጣዩ መርሐ ግብር ወደ ቀበና ምሥራቀ ፀሐይ መድኃኔዓለም የተላለፈ መሆኑን የሚያሳይ የርክክብ ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል፡፡
{flike}{plusone}