በአዲስ አበባ ገዳማት እና አድባራት ለሚገኙ የአብነት ት/ቤት መምህራን ለሁለት ተከታታይ ቀናት የቆየ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጣቸው
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በተገኙበት ሰኔ 18 እና 19 ቀን 2006 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከአድባራት እና ገዳማት ለተውጣጡ ቁጥራቸው ከ300 በላይ ለሚገመት የአብነት ት/ቤት መምህራን ከስድስት ባላነሱ የትምህርት ርዕሶች በተለያዩ ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ተሰጥቷል፡፡ በተሰጡት ትምህርቶች የነባሩ /የቆየው/ እና የዛሬው ትምህርት ቤት ገጽታ ምን እንደሚመስል የኢትዮጵያ የስልጣኔ ምንጭ የአብነት ትምህርት ቤት መሆኑን በአብነት ት/ቤት የሥርዓተ ትምህርት ፖሊሲ አስፈላጊነትን፣ የአሁኑ ዘመን የአብነት መምህራን የምርምር ሥራ መዳከሙን እና የመሳሰሉትን መሠረታዊ ችግሮች እና መፍትሔአቸውን ጭምር ያካተተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት የተሰጠ ሲሆን በመጨረሻም ከተሰበሳቢ መምህራን የሚከተለው የአቋም መግለጫ ቀርቧል፡፡
የአቅም መግለጫ፡- ትኩረት ለአብነት ትምህርት ቤት በሚል ርዕስ ከሰኔ 18-19 ቀን 2006 ለሁለት ተከታታይ ቀናት በተካሔደው ጉባኤ የተሰጠ የአቋም መግለጫ፡-
1. በሁለቱም ተከታታይ ቀናት በተደረገው ጉባኤ የቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ መንፈስን የሚያድስና የሚገነባ ተስፋ የሚሰጥ የሚያተጋ ስለሆነ በመማር ማስተማር ሂደት እንደቀደመው አባታቶቻቸን ጠንክረን እናስተምራለን፡፡
2. ቤተክርስቲያን የምትሰጠንን ግዳጅ በአወንታ ለመፈጸም ተዘጋጅተናል
3. እኛ መምህራን መንፈሳዊ ትምህርቱን ስብከተ ወንጌሉን ቋሚ መደበኛ ሥራችን አድርገን አንዱን ከአንዱ ሳንለይ ሳበላልጥ እኩል በእኩል በተደራጀና በተጠናከረ ስትራቴጅካዊ አካሄድና ልምድ በተሻለ የዘመኑን ትውልድ በራሱ ቋንቋና ፊደል በማቅረብ ግ እዝን ማእከል አድርገን ለማስተማር እንተጋለን፤
4. የትምሀርት ስርጭቱ ፍትሐዊነት ሁሉን አቀፍ በማድረግ መግባባትን በሚፈጥር ዘዴ በተለይም ወጣቱን ማእከል አድርገን ከዘመናዊ ትምህርት ጋር በማጣጣም እናስተምራለን፡፡
5. የወልና የተናጠል የመደበኛ የክረምት ትምህርቶች እንደየመጠኑ አቅሙ በመለየት ክረምትም ሆኖ የመደበኛ አስተምሮአችን ያለ ማቋረጥ እንደየ ሙያ ዘርፋችን እናስተምራለን፡፤
6. ስለ አብነት መምህራን ለቤተክርስቲያንና ለሀገር ላበረከቱት ከፍተኛ አስዋጽኦ ከቤተክህነት እስከ ቤተ መንግሥት እውቀት ስልጣኔ ብልጽግና ሲሰጡ መቆየታቸው የተረጋገጠ ስለሆነ አሁንም ይህን የታሪክ ዳራ አቅማችን በፈቀደ ሁሉ እናስከብራለን፡፡
7. ቅዱሳንና ብፁዓን አባቶቻችን በትምህርተ መንፈስ ቅዱስ የሚወለዷቸው ጉባኤ ቤቶችና የአብነት መምህራን የማስመስከሪያ ጉባኤ ቤቶች የሚመረቁ ምሑራን እንደ 3ቱ ኮሌጆች ማለትም የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ቅድስት ሥላሴ ከሣቴ ብርሃን አባ ሰላማ ምሑራን እንደተመረቁ ወደ ሥራ እንዲመደቡ የቤተክርስቲያን እራስ ለሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ ይህ የአቋም መግለጫችን እንዲቀርብልን እንጠይቃለን፡፡
8. እኛ የአብነት መምህራን በምንኖርበት፣ በምናገለግልበት፣ በምናስተምርበት ቦታ ከአስተዳደሪው ጀምሮ በቢሮ ሠራተኞች የሚደረገው ጫና ግፍ ከሥራ ማገድ ያለ አግባብ ቅጣት መቅጣት እንዲወገድልን መመሪያ እንዲሰጥልን እንጠይቃለን፡፡
9. እኛ የአብነት መምህራት በቃለ ዓዋዲው መሠረት መደበኛ አገልጋይ ከመሆናችን አንጻር በስበካ ጉባኤ ምርጫ እንመርጣለን ተመርጠን በምንሠራበት ጊዜ አንድ አንድ ያልተገቡ ውሳኔዎችን ስንቃወም፣ ሳንበድል፣ ሳንፈቅድ በግፍ ያለ አግባብ ከምንኖርበት አካባቢ ወደ ሩቅ ቦታ እየተዛወርን በሥቃይ ላይ እንገኛለን፤ ይህ እንዲወገድልን ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና ለሚመለከተው ክፍል መመሪያ እንዲሰጥልን እንጠይቃለን፡፡
10. እኛ የአብነት መምህራን መብታችን ከምድብ ሥራችን ጀምሮ በቢሮ ሠራተኞች በንቀት መታየታችን ደመወዛችን ማነሱ ለመማር ማስተማር ተጽኖ እየፈጠረብን በመሆኑ ሕጻናት እኛን እያዩ ትምህርት ለመማር እየተሳቀቁ ስለሚገኙ ተጽእኖ እየፈጠረብን ስለሆነ በጠቅላላው መብታችን እንዲከበርልን እኛም ግዴታችን እንድንወጣ ጥብቅ መመሪያ ለሚመለከተው ክፍል እንዲተላለፍልን እንጠይቃለን፡፡
11. ለቅጥርም ሆነ ለእድገት ትምህርት ክህሎትና የአፈጻጸም ብቃት ብቻ መሠረት ያደረገ እድገትና ሹመት እንዲሰጥ እንጠይቃለን፡፡ 12. ሁሉም አሠራር በአድሎ ሳይሆን እንደ ቤተክርስቲያን መመሪያ ቃለ አዋዲ መስፈርቱ ግልጽና በትምህርት፣ በእውቀት፣ በብቃት፣ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን እንጂ ከብሔር፣ ከጎጥ፣ ከዘመድ አዝማድ ወ.ዘ.ተ ከሁሉም የጸዳ እንዲሆን መምሪያ ለሚመለከተው ክፍል እንዲተላለፍልን አጥብቀን በትህትና እንጠይቃለን፡፡ በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ቤተክርስቲያን አቅሟ በፈቀደው ሁሉ የአብነት መምህራንን መደገፍ እንደሚገባት፤ የቤተክህነት ጽ/ቤት ቢርም ለአብነት መምህራን ክፍት መሆን እንዳለበት እና መምህራኑም ተወካዮቻቸውን እንዲሰይሙ በማሳሳብ የማበረታቻ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
{flike}{plusone}