በአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ከሥራ የተፈናቀሉ የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች በሙሉ ወደ ሥራ እንዲመለሱ ተወሰነ
ከሚዲያ ክፍል
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ዶ/ር ብፁዕ አቡነ አረጋዊ እና ዋና ሥራ አስኪያጁ መ/ር ይቅርባይ እንዳለ ከአድባራትና ከገዳማት አስተዳዳሪዎችና ምክትል ሊቃነ መናብርት ጋር በዛሬው ዕለት ከሥራ የተፈናቀሉትን ሠራተኞች አስመልክቶ ሰፋ ያለ ውይይት አድርገዋል፡፡
የውይይቱ አጀንዳ በዋነኝነት በተለያየ ምክንያት ከሥራ ገበታቸው ተፈናቅለውና ታግደው ያሉትን ሠራተኞች እንዴት አድርገን መፍትሔ እንስጣቸው የሚል ነበር፡፡የሀገረ ስብከቱ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ዶ/ር ብፁዕ አቡነ አረጋዊ በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብዙ ዘመናትን ያሳለፈች፣ ብዙ ተከታይ ያላት፣ የራሷ የሆነ አስተዳደራዊ ሥርዓት የነበራትና ያላት፣ በሰላም አምባሳደርነቷ፣ በይቅርታና በመልካም ሥራዋ የምትታወቅ መሆኗን ገልጸው አሁን ግን በተለያየ ምክንያት በተፈጠረ ችግር ከውስጥ አልፎ አደባባይ ላይ በመውጣቱ ምክንያት መልካም የነበረው ስሟ በደካማ ጎን ተነሥቷል፤ ችግሩ እንደ ችግር በፈጠርም አሁን ግን የከበረ ዝናዋን ክብሯንና ማልካም ስሟን ማስመለስ ስላለብን ለዚህም ደግሞ እናንተ የረጅም ጊዜ ልምድና ችሎታ ያላችሁ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ሊቃነ መናብርት ጋር መወያየቱ እጅግ ጠቃሚ በመሆኑና ለእነዚህ አገልጋዮች መፍትሔ የሚሆን ሓሳብ እንድታግዙን ነው ሲሉ መድረኩን ከፍተዋል፡፡ በመቀጠልም ዋና ሥራ አስኪያጁ መ/ር ይቅርባይ እንዳለ ከሥራ የተፈናቀሉት ሠራተኞ ጉዳይ አሳዛኝ መሆኑን ገልጸው ለእነዚህ አፋጣኝ ምላሽ እንዴት እንስጥ? ለወደፊት እንዲህ ያለ ችግር እንዳይደገም ምን መፍትሔ እንውሰድ በማለት የረዳት ሊቀ ጳጳሱን ሐሳብ አጠናክረዋል፡፡
የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ምክትል ሊቃነ መናብርትም ለቀረበላቸው ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት በየአድባራቱና በየገዳማቱ ባላቸው ክፍት የሥራ ቦታ እንደየሞያቸው ሀገረ ስብከቱ የላከላቸውን እንቀበላለን ሲሉ በአንድ ድምፅ ተስማምተዋል፡፡
ያልተማረ ሰው አይላክብን፣ የአለቆች መታወቂያ ይሰጠን፤ የደላላዎች በር ይዘጋ፣ ሲፈጸም የቆየው ቅጥር ጥራትን ያላገናዘበ ነበር፤ ባለሙያ ከሆኑ ብዙ ሰዎችም ቢሆኑ እንቀበላለን፤ በእድሜ ያረጁ አባቶች ደመወዛቸውን እንደያዙ ይጦሩ፣ በምትካቸው ሊሠራ የሚችል ሰው ይተካ በማለት ሠፋ ያለ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በሌላ መልኩ ድለላና የድለላ ሥራ ለአንዴና ለመጨረሻ ይቁም ሲሉ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ረዳት ሊቀ ጳጳሱ አውግዘዋል፡፡
በመጨረሻም ረዳት ሊቀ ጳጳሱ ለጉባኤው መመሪያ አስተላልፈዋል፡፡ ከመመሪያዎቹ መካከል በአስተዳዳሪዎችና በሠራተኞ መካከል ያለው ክፍተት በአግባቡና በሥርዓቱ መፈታት አለበት፣ ከሀገረ ስብከቱ የሚላኩ ደብዳቤዎች መዋቅርን ጠብቀው መፈጸም አለባቸው፣ ከሕንፃዎችና ከሱቅ ኪራይ ጋር በተያያዘ በጨረታና በውል መከራየት አለባቸው፡፡