በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የተለያዩ የሃይማኖት መሪዎች ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን እና የድኅነትን አስከፊነት አስመልክተው ለግማሽ ቀን የቆየ የጋራ ምክክር አደረጉ

0094

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የሃይማኖቶች ጉባኤ የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን የምክክሩን ጉባኤ አስመልክተው የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት የሚከተለውን መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን  ከሩቅም ከቅርብም አሰባስቦ እርሱ የሚከብርበትን ሥራ እንድንሠራ እንደዚህ ተሰብስበን ስለ ሀገራችን ችግር እንድንወያይ ስለፈቀደልን የተመሰገነ ይሁን፡፡
ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን እና የልመናን አስከፊነት ለማስወገድ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ይህንን መርሐ ግብር አዘጋጅቶአል፡፡ በተለይም የሃይማኖት መሪ የሆን የሰዎችን ችግሮች ለማስወገድ እና መፍትሔ ለመስጠት ከፈጣሪ የተሰጠን ተልእኮ ነው፡፡ ይህንን የተሰጠንን ተልእኮ በአግባቡ እንድንወጣ እና እንድንመካከር የተዘጋጀ የምክክር መድረክ ነው የአዲስ አበባ መስተዳድር ያቀደው አጀንዳ የተሻለ አጀንዳ ነው፡፡ ለዜጎችም መፍትሔ ሰጪ ነው፡፡ እኛ ዛሬ በዚህ ጉዳይ ላይ ተወያይተን የምሠራውን ሥራ ተከፋፍለን የምንለያይበት ጉባኤ ነው፡፡
ከዚህ አጀንዳ በፊት አንድ ነገር ለማለት እፈልጋለሁ፡፡ የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት በግራ ተሰባስበን ያቋቋምነው መንፈሳዊ ተቋም በአዲስ አበባ ከተማና በፌዴራል መንግሥት ታውቆ የለና ምክር ቤትም ያለው ሰላሳ አምስት የምክር ቤት አባላት ያሉበት ሰባት ሰዎች የቦርድ አባላት የጽሕፈት ቤት ኃላፊም ያለው ተቋም ነው፡፡ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ እግዚአብሔር የፈቀደለትን ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ሊሠራቸው የሚገባቸውም ብዙ ሥራዎች አሉ፡፡ አሁን ግን ከ2006 ዓ.ም ከዘንድሮ ጀምሮ በአዲስ መልክ በየክፍለ ከተማው በየወረዳው ተቋማትን በማጠናከር በአዲስ መልክ አዋቅረን እና ብቃት ያላቸውን ሰዎች ከየሃይማኖት ተቋማት መድበን በአዲስ አበባም ውስጥ ያሉትን ችግሮች በመፍታት እኛ ከሁሉም በላይ ደግሞ እና የሃይማኖት አባቶች አርአያና ምሳሌ ሆነን የኢትዮጵያውያን መገለጫና የኢትዮጵያውያን ሁሉ መኖሪያ የሆነችውን አዲስ አበባን የበረከት እና የፍቅር ከተማ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ይህንን ለማድረግ ጊዜው አሁን ነው ብዬ እገምታለሁ፡፡ እንደዚህ በዚህ መልክ ተሰባስበን በመነጋገርና በመወያየት የሚከሰት ችግር አይኖርም እንጂ አለመግባባት ቢፈጠር እንኳን ጊዜ ሳይወስድ ችግሮችን መፍታት የሚአስችለን መድረክ ነው የተከፈተልን፡፡ በእጅጉ ደስ ሊለን ይገባል፡፡ ሰው ብቻውን መኖር አይችልም የሚለው የእግዚአብሔር ቃል ለጋብቻ ብቻ ሳይሆን የተለያየ አመለካከት፣ የተለያየ ግምት፣ የተለያየ ዕውቀት፣ የተለያየ ደረጃ፣ ያለው ሀብት ሆኖ ነው፡፡ መኖር የሚቻለው፡፡
ስለዚህ በአዲስ አበባ ከተማ የምንኖር ሰዎች ምሳሌ ሆነን ከተማውን የምቾት ከተማ ማድረግ እንድንችል ፈጣሪአችን ይርዳን፡፡

640

ስለ ሥነ-ምግባር በተመለከተም እናንተ የሃይማኖት መሪዎች የምትነበቡ መልእከቶች እና ጽሑፎች ናችሁ፡፡
ስለሆነም አርአያና ምሳሌ ልንሆን ይገባናል ለራሳችን ምቾት ሳይሆን ለልጆቻችን ምቾት ሲባል መጎዳት ያስፈልጋል፡፡ በፈጣሪ ዘንድ ዋጋ ማግኘት እንድንችል ዋና አጀንዳችን ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ከምንም በላይ እና በሁሉም መጻሕፍት እንደተጠቀሰው ሰዎችን መጎዳት ሰው በሰው ሲጠቃ በተለይም ሕግን ከለላ በማድረግ ሰው ሲጠቃ ከምንም በላይ አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህንን ችግር መፍታት የሚቻለው ተመካክረን እና ተወያይተን ሲሆን ነው፡፡ ሰውን መሸጥ ኃጢአት ነው፡፡ ወንጀልም ነው፡ ይህንን ወንጀል የምንከላከለው በመንግሥት ብቻ ሳይሆን እኛም በማውገዝ ጭምር ነው፡፡ ሥራ በሚሠራበት ወቅት ሕግን የተላለፉ አይመስላቸውም፡፡ ለእነርሱ የሚታያቸው ሰዎችን ሸጠው የሚአገኙት ገንዘብ ነው፡፡ እነርሱም እየተጠቀሙ አይደለም፡፡ ለሰው ልጆች የምናስተምረው ኃጢአት ሰርቼ የማገኘው ገንዘብ ሊአኖረን ይችላል ወይ? በማለት ማስተማር አለብን ይህንን ወንጀል የሚፈጽሙ ሰዎች ወይም የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ወይም የእስልምና እምነት ተከታይ ወደ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ናቸው፡፡ ስለዚህ ሁላችንም በየሃይማኖት ተቋማችን ማስተማር ይኖርብናል ብየ እገምታለሁ፡፡
በዚህ እየተታለሉ ለሚጠቁትም ሰዎች በስደት የምአገኙት ጥቅም አለመኖሩን ማስተማር አለብን፡፡ ሕይወት ማጣት ምቾት ማጣት አንድሚሆን መንገር አለብን፡፡
ሰዎች ከዩኒቨርስቲ ተመርቀው እስኮላር ሺፕ አግኝተው ወደ ውጭ ሀገር ለመሄድ ሲነሱ ቤተሰብ ተሰብስቦ ያለቅሳል እኔ ሕጻን ሆኜ ከገጠር ወደ አደስ አበባ መጥቼ ስመለከት ሰዎች ወደ ውጭ ሀገር ለእስኮላር ሺፕ ሲላኩ ዘመድ ተሰብስቦ ለቅስ ነበር፡፡ አሁን ግን የኢትዮጵያ ባሕል ተለውጦ ስደት በገንዝብ እየተገዛ ነው፡፡
ስለዚህ የቀድሞውን ጠቃሚ ባሕል ትተናል፡፡ ባህል ማለት ለሰው ልጆች የሚጠቅም፣ ለሀገር የሚጠቅም ማለት ነው፡፡ ሌላው እንደባህል የሚታየው ጎጂ ባህል አለ እሱን ማለቴ አይደለም፡፡
ስለዚህ ጠቃሚ ባህሎቻችን እንዲጠበቁ የማስተማሩ ሥራ የእኛ የሃይማኖት መሪዎች ኃላፊነት ነው፡፡ ልማትን አስመልክቶ ስንመለከት ልማት ከሃይማኖት አባቶች ውጭ የሚፈጸም አይደለም፡፡ ሰነፍ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርስም ይላል መጽሐፍ ቅዱስ፡፡ የሚሠራ ሰው ራሱን ችሎ ለሌላም ይተርፋል፡፡ የማይሠራ ሰው ድሀ ነው፡፡ እግዚአብሔርንም ሰውንም ያሳዝናል፡፡ ሠራተኛ ሀሜተኛ አይሆንም ምክንያቱም ገንዘብ ስለሚኖረው አይሠርቅም እንደገናም ለኃጢአት ጊዜ አይኖረውም የእሱ ጊዜ መልካም ጊዜ ነው ሰውን የሚአማበትና  የሚወቅስበት ጊዜ የለውም፡፡
ስለዚህ ልማትን በዚህ መልኩ ካየን ስለህዳሴው ግድብ ትንሽ ለማለት እፈልጋለሁ፡፡ ቀደም ሲል ቃል የገባነውን ድርሻ ወስነን ነበረ አሁን ግን ቀዝቅዟል በአሁኑ ጊዜ በመንፈስ ከእኛ ጋር የሆኑ ነገር ግን በሥጋ የተለዩን ክቡር ጠቅላይ ምንስቴራችን አቶ መለስ ዜናዊ በነበሩበት ወቅት በእጅጉ እና በስፋት ሲሰሩ ነበር፡፡ ከዚያ በኃላ ግን እየቀዘቀዘ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡
እሳቸው ይህን ሥራ የሠሩት ለእኛ እና ለልጆቻችን እንጂ ለራሳቸው አልነበረም ለትውልድ ማሰብ ለሀገር ማሰብ ማለት ነው ለትውልድ የሚቀጥል ልማፍ ሠርቶ ማለት አለብን፡፡ ታሪክን ለማስታወስ ሲባል ለሀውልትም ገንዘብ ይወጣል የሕዳሴው ግድብ ሐውልትም ነው ሐብትም ነው፤ ታሪክም ነው፡፡ ሁሉንም ነገር የሚአድስ የሕዳሴው ግድባችን ስለሆነ ከበፊቱ የበለጠ ሊቀጥል ይገባዋል፣ የሃይማኖት ተቋማት ቃል የገባነውን በመሰብሰብ እና ባለ ሀብቶች ከሆኑትም በመጠየቅ አጠናክረን እንሠራለን፡፡ አዲስ አበባ ለሁሉም ክፍል ምሳሌ መሆን አለባት፡፡ ምክንያቱም አዲስ አበባ የሁሉም መገለጫ እና የሁሉም መኖሪያ ናት፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የውጭ ሀገር ዜጎችም በፈቃድ የሚኖሩባት ናት
ስለዚህ ሁሉንም ለመወሰን እንድንችል አምላካችን እግዚአብሔር በመካከላችን ተገኝቶ ስብሰባችንን ይባርክልን ሀገራችን ኢትዮጵያም በስምምነት እና በአንድነት የምንኖርበት የበረከት እና የምቾት ሀገር ያድርግልን በማለት ሰፋ ያለ የመግቢያ ንግግር አድርገዋል፡፡
በመቀጠልም በተለያዩ ምሁራን ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን እና የድኅነትን አስከፊነት አስመልክተው ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል ከጉባኤው ተሳታፊዎች ለችግሮቹ መፍትሔ የሚሆኑ ሐሰቦችን ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም ከምክክሩ የተገኘውን ውጤት የሚአንጸባርቅ የአቋም መግልጫ ቀርቧል፡፡

ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና የድህነት አስከፊነት
1. እኛ የአዲስ አበባ ከተማ የጋራ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባላት ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ለዜጎቻችን ከፍተኛ አደጋ ስለሆነ በጋራ አደጋውን እና ወንጀሉን ለመከላከልና ለተከታዮቻችን ለማስተማር ቃል እንገባለን፡፡
2.  ልመና አስከፊና የሀገርን ገፅታ የሚያበላሽ ስለሆነ የዜጎችንም ክብር የሚያዋርድ ስለሆነ በሥነ ምግባር የታነፀ ሠራተኛና ዜጋ ለማፍራት የበኩላችንን ድርሻ ለመወጣት ቃል እንገባለን፡፡
3. ሰላም ለሰው ልጅ ሁሉ እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ስለሆነ ተከባብሮ የመኖርን እሴት ለመወጣት የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን፡፡
4.  በመጨረሻም ሀገራችን የጀመረችው ታላቅ የሕዳሴ ግድብ የሁላችንም የጋራ ጉዳይ እና የጋራ ሀብት ስለሆነ በተወሰነለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ በየቤተ እምነቶቻችን ዜጎችን ለማስተማር ቃል እንገባለን፡፡
                 “ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ የአዲስ አበባ ከተማ የጋራ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ”
                       መጋቢት 10 ቀን 2006 ዓ.ም
                          አዲስ አበባ

{flike}{plusone}