በአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት አዲስ ድረ ገጽ ተሠርቶ በሥራ ላይ ዋለ
ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለተገልጋዩ ማህበረሰብ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠትና አሠራሩም ዘመኑ የሚፈቅደውን ሥራ ለመሥራት ታስቦ ባለ 3 ፎቅ ዘመናዊ ሕንፃ ማሠራቱን ተከትሎ በሀገረ ስብከቱ ሊኖሩ ከሚገባቸው ሥራዎች አንዱ ሀገረ ስብከቱንና በሀገረ ስብከቱ ያሉትን አድባራትና ገዳማት እንዲሁም በየገዳማቱና አድባራቱ ያሉትን ታሪካዊ ቦታዎችን ሊያስተዋውቅ የሚችልበት፤ ምዕመናን ወቅታዊ የሆነ የሀገረ ስብከቱ ሃይማኖታዊም ሆነ ማህበራዊ ጉዳዮችን የሚከታተሉበት ድረ ገጽና የኢንተርኔት አገልግሎት በወቅቱ በነበረው የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ከፍተኛ ጥረት ተደርጐ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን የሀገረ ስብከቱ ድረ ገጽ አየር ላይ ውሎ እንደነበረ ይታወቃል፡፡
በተጨማሪም አዲሱ የሀገረ ስብከቱ ሕንፃ በሚመረቅበት ወቅት ቴክኖሎጂውን ሊያስጠቅሙ የሚችሉ፡-
- ከ15 ያላነሱ ዘመናዊ ኮምፑውተሮች፣
- የተለያዩ ቪዲዮ ካሜራዎችን፣
- ዲጂታል ላይብሬሪ ሊሰጥ የሚችል ዘመናዊ ላይብረሪ፣
- የኢንተርኔት አገልግሎት መስጫና መቆጣጠሪያ ክፍሎች ለአገልግሎት ተዘጋጅተው የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ተስተጓጉሎ ቆይቷል፡፡
ከ2ዐዐ2 ዓ.ም. ጀምሮ እሰከ 2ዐዐ4 ዓ.ም. አጋማሽ ተጀምረው የነበሩትን ጥሩ የሥራ ጅምሮች ግን ማስቀጠል አልተቻለም፡፡ ምንም እንኳን በወቅቱ ድረ ገጹም ይሁን የኢንተርኔት አገልግሎቱ ሥራ ላይ ባይውልም ከሐምሌ 2ዐዐ4 ዓ.ም. ጀምሮ ከ2 ዓመታት በፊት ተጀምሮ የቀረውን በአዲሱ የሀገረ ስብከቱ አመራር ሰጪነት የድረ ገጹም ሆነ የኢንተርኔት አገልግሎት ሥራ እንደገና ሊሠራ ችሏል፡፡ በቀጣይም ብዙ ሊሠሩ የሚችሉ ሥራዎች እንዳሉ ሆነዉ ይህን ሥራ እንዲሠራ ያደረጉ ሁሉም የሀገረ ስብከቱ የአስተዳደር ሠራተኞች ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ በተለይም በሥራው ወቅት ያሳዩት የሥራ ትብብር በቃላት መግለጽ ከሚቻለው በላይ ነው፡፡ ከባለሞያው በተጨማሪ ለዚሁ ሥራ ሌት ተቀን ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደረጉ የኮሚቴ አባላትም ከፍተኛ የሆነ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል፡፡