በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የዘመናችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተግዳሮቶችና የመፍትሔ ሃሳቦች በሚል ርእስ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀረበ

6139

በአዲስ አበባ ሀ/ስብከትና በሰንበት ትምህርት ቤት ማደራጃ መምሪያ በተደረገ የጋራ ዝግጅት የዘመናችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተግዳሮቶችና  የመፍትሔ ሃሳቦች በሚል ርእስ የተጠና ጥናታዊ ጽሑፍ የሃገረ ስብከቱ ሥራ አስክያጅ መ/ር ጎይትኦም ያይኑ፤የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣የየአድባራቱ ሰባክያነ ወንጌል ሐላፊዎች፣ ሊቃነ መናብርትና የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ተወካዮች በተገኙበት በአዲስ አበባ ሃ/ስብከት አዳራሽ ታህሣሥ 14/2010 ዓ.ም ጥናታዊ ጽሑፉ ቀርቧል።ጥናቱ በሁለት ክፍል የቀረበ ሲሆን በተሳታፊዎች በኩል ለውይይት መድረኩ ክፍት ተደርጎ ነበር። በቀረበው ጥናት ላይ ቤተ ክርስቲያናችን በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ያጋጠሟት ተግዳሮቶችና ውጣውረዶች በርካታ ቢሆኑም የመልካም አስተዳደር እጦት፣ አግባባዊ የሆነ የአገልጋይነት ክብር አለመኖር፣ ለትክክለኛ ስራ ትክክለኛ ሰው አለመመደብና የመሳሰሉት መሆናቸው ተገልጾ ዋናውና ወቅታዊ የቤተክርስቲያን ተግዳሮት ግን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አስተምህሮአዊ እንቅስቃሴና የእስላማዊ አክራሪነትና ጽንፈኝነት ናቸው ተብሏል።በጥናታዊ ዳሰሳው ላይ ቤተክርስቲያናችን ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ የተበታተነ፣ ወጥነት የሌሌው፣ብዙ ትግል ጥቂት ውጤት በመሆኑ የችግሩ መስፋትና እልባት አለማግኘት ችግሩን እስካሁን ድረስ እንዲቀጥል አድርጎታል ከዚህም ጋር ተያይዞ ቤተክርስቲያናችን በርካታ ሊቃውንትና መምህራን እንዲሁም የስነ–መለኮት ምሩቃን ያሏት ባለብዙ አንጡራ ሃብት ያላት ብትሆንም የስብከተ ወንጌል መድረኳንና የሰንበት ትምህርት ቤት አዳራሿን የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምህሮ ጠንቅቀው በማያውቁ የመድረክ ሰዎች መወከሏ ሌላኛውና አንገብጋቢው ችግር መሆኑም ነው የተገለጸው። በየትኛውም መዋቅራዊ አደረጃጀት ባለው ተቋም ውስጥ የራሱ የሆነ ስልታዊ መዋቅር፣ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለው አካል፣የሚከናወኑ ክንውኖች፤ የሚሰሩ ስራዎችና በእቅድ የሚመራ የስራ ክንውን ቢኖራቸውም በየጊዜው አፈጻጸሙን የመገምገም፣ የመፈተሽና የማስተካከል እንዲሁም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የመለወጥም ስራ ጭምር ሲደረግ እንመለከታለን። በቤተክርስቲያናችንም ነገሩን በበላይነት የሚመራው አካል አትኩሮት በመስጠት የተደራጀና የሰለጠነ በቂ የሰው ሃይል በየዘርፉ በመመደብ፣ ያገባኛል የሚል የተቆርቃሪነት ስሜት በማስፈን፣ሐዋርያዊ አስተምህሮዋን በመጠበቅ፣ ቀኖናዋንና ሥርዓትዋን ዘመኑንና ትውልዱን በጠበቀ መልኩ በማሻሻልና በማስተካከል ሐዋርያዊ ግዴታዋን  ያለቸልታና ዝምታ   ልትወጣ ይገባታል። የችግሩ አሳሳቢነት በወፍ በረራ አስተምህሮ የሚቀረፍ ባለመሆኑ ቤተክርስቲያኒቱ ያሏትን ሊቃውንት አስተባብራና አጠንክራ መስራት እንዳለባትም በጥናቱ ለመዳሰስ ተሞክረዋል። ቤተክርስቲያኒቱ 10 ሚሊዮን አማንያንን በቀላሉ ለመዘረፍ ዋንኛ ምክንያት የእኛ አለመወያየት፣ አለመነጋገርና በጋራ አለመስራት መሆኑም  ተነስቷል።በታዳሚዎቹ ሰፋ ያለ ወይይት የተደረገ ሲሆን ብዙ አስተያየቶችም ተሰንዝሯል።
በመጨረሻም የአዲስ አበባ ሃገረስብከት ሥራ አስኪያጅ መምህር ጎይትኦም ያይኑ  ከሰንበት ትምህርት ቤት ማደራጃና መምሪያ ሃላፊ መምህር እንቁ ባህሪ ንግግር በመቀጠል ባደረጉት የመደምደምያ ንግግር በቀረበው ጥናት ላይ አያይዘው የቀረበው ጥናት እንደ አንድ የቤክርስቲያን ችግር መሆኑን ቢያወሱም ሌሎች በርካታና አንገብጋቢ  የቤተ ክርስቲያን ችግሮች መኖራቸውንም ሳይናገሩ አላለፉም። ቤተክርስቲያናችን በቂ የሚባል የሰው ኃይል አላት፤ ነገር ግን ሁሉም አካላት ሐላፊነታቸውንና ድርሻቸውን በአግባቡ አልተወጡም።  ይህም የቀረበው ጥናት የት እንዳለንና ደረጃችንን በመጠኑ የሚያሳይ ቢሆንም ሌሎችንም ችግሮች አካትቶ የበለጠ ጥናት ልናደርግ ይገባናል በማለት ሐሳቡን አጠናክረዋል። ቤተክርስቲያኒቷ ከሲኖዶስ ጀምሮ እያንዳንዱ ቤት ድረስ የሚገባ መዋቅር  አላት። በጣም የሚሳዝነው ነገር ቢኖር በመዋቅሩ መሰረት አለመስራት፣ አግልጋዮች የተባበረና የተቀናጀ አንድነት አለመኖር፣ለአባቶች የሚገባውን ክብርንና የአባትነት ስሜት አለመስጠትና የመሳሰሉት ዘርፈ ብዙ ችግሮች መሆናቸውን አስርድተው ወደፊትም ሀገረስብከቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበርና የቅዱስነታቸውን መልካም ፍቃድ በመጠየቅ እንዲሁም  አባታዊ ምክራቸውን በማዳመጥ ለቤተ ክርስቲያን የሚበጀውንና የሚጠቅመውን ሁሉ ከማድረግ ችላ እንደማይል የውይይት መድረኮችም እንደሚቀጥሉ በመናገር ሐሳባቸውን ደምድመዋል።