በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በዋና ሥራ አስኪያጅነት የተመደቡት 27ኛው ተሿሚ መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ኃይለ ገብርኤል ነጋሽ በሀገረ ስበከቱ የስብሰባ አዳራሽ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው
የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት በሀገሪቱ ርእሰ መዲና አዲስ አበባ ከተመሠረተ ጀምሮ የበርካታ ሥራ አስኪያጆችን ታሪካዊ አሻራ አስተናግዶ አሁን ደግሞ መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ኃ/ገብርኤል ነገሽን 27ኛው የሀ/ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አድርጎ ሾሟል። ላለፉት 12 ወራት ጽ/ቤቱን በዋና ሥራ አስኪያጅነት ሲመሩት የነበሩት መልአከ ሕይወት አባ ሞገስ ኃ/ማርያም የካቲት 20/2012 ዓ/ም ተሰናብተው በምትካቸው ደግሞ የምስራቀ ፀሐይ ቅዱስ ገብርኤልና ቅድስት አርሴማ ቤ/ክን አስተዳዳሪ የነበሩት መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ኃ/ገብርኤል ነገሽ የሀ/ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆን በቦታው ተተክቷል።
በዋና ሥራ አስኪያጅነት ለተመደቡት አባት በተደረገው ደማቅ አቀባበል ላይ ብፁአን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የሀ/ስብከቱና የክፍላተ ከተሞች ሠራተኞች፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና ሊቃነ መናብርት እንዲሁም በርካት ካህናትና ተጋባዥ እንግዶች የተገኙ ሲሆን በአቀባበል መርሀ ግብሩ ላይም በምስራቀ ፀሐይ ቅዱስ ገብርኤልና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህናትና ሊቃውንት ስብሐት እግዚአብሔር ቀርቦ በዋና ሥራአስኪያጁ መልእክት ተላልፏል። መልእክቱም የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ብዙ ችግሮች እንዳሉበት ቢታወቅም ይህንን መሠረታዊ ችግር ለመፍታት ግን መጮህ መፍትሄ አይሆንም። ይልቁንም ስልታዊ የሆነ መልካም አስተዳደር በመቀየስ፣ ስብከተ ወንጌልን በማጠናከርና የጋራ አንድነታችንን በማጎልበት መሆን ይገበዋል። እኔ የተቀበልኩትን የመሪነት አደራ በሚቻለኝ መጠን ለመተግበር የእናንተ የወንድሞቼና የአባቶቼ ጸሎትና ቀና ምክር ያስፈልገኛልና አብራችሁኝ ተሰለፉ የሚል አባታዊ ጥሪም አስተላልፈዋል።
በሥርዐቱ ላይ ከተገኙት ብፁአን አባቶች መካከል አንዱ የሆኑት ብፁእ አቡነ ሕርያቆስ ተሿሚዎችን መቀበልና መሸኘት በጽ/ቤቱ የተለመደ ቢሆንም ሁሉም ግን የራሳቸውን ታሪካዊ አሻራ አሳርፈው ሄደዋል። እኛ በማይረቡ ነገሮች ስንነታረክ ብዙ የሚረቡና የሚጠቅሙ ነገሮች አምልጠውናል። አሁንም ለሚረባው ነገር ትኩረት ሰጥተን ከአዲሱ ተሻሚ ጋር አብረን እንስራ ሲሉ ብጹእ አቡነ እንጦስ ደግሞ ተጠርተን በፈቃዳችን የተቀበልነው የእረኝነት ሥራ ከፍታኛ ኃላፊነትን የሚጠይቅ በመሆኑ ሁላችንም ቤተክርስቲያን የምታደርግልንን ያክል እኛም ልናደርላት ይገባል። አዲስ አበባ ሀ/ስብከት ብዙ ውስብስብና የማይፈታ የሚመስሉ ችግሮች አሉ በዚህም በሊቃውንት ብዛትና በገንዘብ ብዛት ሞዴል የሆነችውን ያክል በሰላም ጉዳይ ሞዴል እንዳትሆን አድረጓታል። በሀገራዊ ጉዳይ ትልቅ ሥራ ሊሠራ አደራ የተሰጠው ቋሚ ሲኖዶስ የአዲስ ሀ/ስብከትን አቤቱ አቅራቢዎችን ችግር ብቻ በማየት ጊዜውን መጨረሱ በእጅጉ ያሳዝናል።
አዲሱ ተሿሚ ከሌላ ሀ/ስብከት ወይም ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የተላኩ አይደሉም ይልቁንም ከመካከላቹ የተሾሙ ናቸው። ይህም ዕድል ተቀራርባችሁ እንድትሰሩ ይረዳችኋል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ በማለት ጠንከር ያለ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈው የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሁኗል።
የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት መዋቅራዊ አደረጃጀቱን የጠበቀ ስልታዊ አሰራር የሌለው ከመሆኑ አንጻር በበርካታ ችግሮችና እንቅፋቶች ውስጥ ተወጥሮ እንደሚገኝ ይታወቃል። ይህም ልማታዊ እና ትምህርታዊ በሆኑ ዘርፎች ላይ መሥራት ያለበትን ያክል እንዳይሠራ፣ ማልማት ያለበትን እንዳያለማ፣ ስብከተ ወንጌልንም እንዳያጠናክር በጥቅሉ የተቀመጠለትን ግብ እንዳይመታ እንቅፋት ሆኖበታል። በእንዲህ አይነት ተቋም ላይ በመሪነት መሾም ወይም ኃላፊነት መቀበል ደግሞ ፈተናውን በእጅጉ ከባድ ያደርገዋል። ስለሆነም የባለ ጉዳዮችን ችግር ከመፍታት በዘለለ ለሀ/ስብከቱ ችግር ፈች የሆነ ዘለቄታዊ የአሠራር ሥርዓት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን እንዱዘጋጅ ያደርጉ ዘንድ እያሳሰብን መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንልዎት እንመኛለን።
መ/ር ሽፈራው እንደሻው
የሀ/ስብከቱ ዘጋቢ