በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በሀ/ስብከቱ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ ዋና ክፍል የተዘጋጀ ስብከተ ወንጌልን በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጠ

ዛሬ የካቲት 25/ 2013 ዓ/ም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት የስብከተ ወንጌል ኃላፊዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ስብከተ ወንጌልን በተመለከተ በሊቀ ጠበብት ዶ/ር ዘሪሁን ሙላቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጧል::

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር አካለወልድ ተሰማ መርሐ-ግብሩን አስመልክቶው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን መርሐ-ግብሩን የተዘጋጀ የቤተ ክርስቲያን የጀርባ አጥንት የሆነ ስብከተ ወንጌልን የተጠናከረ እንዲሆን ሰባክያንንና ሊቃውንትን የሚያሳትፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና መሆኑን አውስቷል።

የሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ ዋና ክፍል ኃላፊ ክቡር መ/ሰላም ዳዊት ያሬድም የተዘጋጀው የሥልጠና መርሐ-ግብር ዘመኑን ዋጅተን የቤተ ክርስቲያኑ ዋነኛ አገልግሎት የሆነውን ስብከተ ወንጌል ዘመኑን በዋጀ መልኩ ለማገልገል እንድንችል የተዘጋጀ ሥልጠና መሆኑን ገልጸዋል።

የሥልጠናው ርእስ “የአስተምህሮና የጉባኤ ገጽታዎቻችን” የሚል ሲሆን አሰልጣኙ ከማርቆስ ወንጌል 3:13-15 ያሉት “ወደ ተራራም ወጣ፥ ራሱም የወደዳቸውን ወደ እርሱ ጠራ፥ ወደ እርሱም ሄዱ፥ ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው፥ ድውዮችንም ሊፈውሱ አጋንንትንም ሊያወጡ ሥልጣን ይሆንላቸው ዘንድ አሥራ ሁለት አደረገ” የሚሉት መሠረተ ሐሳብ ለሥልጠናው እንደ መነሻነት ተጠቅመዋል።

የሥልጠናው ዓላማም የስብከተ ወንጌል ኃላፊዎችና ሰባክያነ ወንጌል ለተሻለ አገልግሎት ማዘጋጀትና ከተጠያቂነት ወደ ተከላካይነት ለመሄድ መሆኑን ተገልጿል።

በሥልጠናው ኦርቶዶክሳዊ የዐውደ ምሕረት ገጽታ ምንድ ነው? ስብከተ ወንጌል የተዳከመበት ምክንያት ምንድ ነው? ስብከተ ወንጌል የሙያ ዘርፍ ነው ወይስ ሁሉም የሚካተትበት የትርፍ ጊዜ ሥራ ነው የሚሉ የመወያያ ነጥቦችን ተነስቷል።

ክቡር ሊቀ ጠበብት ዶ/ር ዘሪሁን ሙላቱ በሥልጠናው የተለያዩ የስብከተ ወንጌል ተገዳሮቶች መኖራቸውን በማውሳት በተለይም የእውቀት እጥረትና ሰንሰለቱን ያልጠበቀ ከላይ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጀምሮ እስከ አጥቢያ ያለውን አስተዳዳራዊ ጠልቃ ገብነት መኖራቸውን ሳይጠቁሙ አላለፉም።

በመጨረሻም በመርሐ-ግብሩ የተገኙት መጋቤ ሐዲስ እሸቱ “አገልጋይና የአገልጋይ ሕይወት” በሚል ርእስ አገልግሎትና የአገልጋይ ሕይወት ምን መምሰል እንዳለበት የሚያትት ሰፋ ያለ ሐተታ አቅርበዋል። ጠቅለል ባለ መልኩ አገልጋይና የአገልጋይ ሕይወት ስንል ከፍ ሲል ክርስቶስን ዝቅ ሲል ዮሐንስ መጥምቅን ማየትና መምሰል ነው ብለዋል።

ዮሐንስ መጥምቅ ላመነበት በሕይወት እየኖረ ለሌሎችም ሳይፈራ፥ ሳያፍር፥ ሳይጨምርና ሳይቀንስ እውነቱን በመስበክና በማስተማር ላጠፋት ደግሞ በድፍረት በመገሰጽ የኖረ ለአገልጋይና ለአገልጋይ ሕይወት ምሳሌ የሚሆን ታላቁ አገልጋይ መሆኑን ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡-መ/ር ኪዱ ዜናዊ

ፎቶ በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ