በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ስለ ቤተክርስቲያን ወቅታዊ ሁኔታ የጋራ ውይይት ተደረገ
የጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በጋራ ባዘጋጁት የምክክርና የውይይት መድረክ በሁለት ብፁዓን አባቶች የሚመራና የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ኃላፊዎችና ሠራተኞች፤ የክፍላተ ከተሞች ሃላፊዎችና ሠራተኞች እንዲሁም የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አስተዳደሪዎችና ሰባክያነ ወንጌል በተገኙበት በቀረቡ ሁለት ዳሰሳዊ ፅሁፎች መነሻነት የጋራ የምክክር መድረክ ተካሄደ፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ላይ እየደረሱ ባሉት ወቅታዊ ችግሮችንና ተግዳሮቶችን አስመልክቶ ሁለት ዳሰሳዊ ፅሁፎች የቀረቡ ሲሆን የመጀመሪያውን የመነሻ ዳሰሳዊ ፅሁፍ ያቀረቡት መልአከ መዊዕ ቀሲስ ሳሙኤል እሽቱ ሲሆኑ ሁለተኛውን ያቀረቡት ደግሞ መልአከ ሰላም ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻ ናቸው፡፡
በዳሰሳዊ ጥናታቸውም አሁን ባለንበት የእኛ ዘመን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ስላሉባት ወቅታዊ ተግዳሮቶችና እየከፈለችው ስላለው ከባድ መስዋእትነት ካብራሩ በኋላ ከዚህ ሁሉ ችግርና ፈተና ሊያወጣትና ሊታደጋት የሚችለው የእግዚአብሔር መለከታዊ ሐሳብ ቅዱስ ወንጌሉ መሆኑንም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ የእነዚህ ችግሮች ምንጭ ከውጭ ባሉት አጽራረ ቤተ ክርስቲያን ተጽዕኖ እና በራሷ አገልጋዮች የሥነ ምግባር ጥሰትና ኃላፊነት የጎደለው እንቅስቃሴ የመነጨ መሆኑን በሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በተለይም ደግሞ ከመንግሥት ሥራ አስፈጻሚ አካላት በኩል በተለያዩ መንገዶችና ስልታዊ አቅጣጫዎች እየደረሰባት ያለው ጫና ከምንጊዜውም በላይ አሳሳቢ መሆኑን አሳይተዋል፡፡ ለታዳሚዎቹም እነዚህን ተጽዕኖዎች ምን ያክል እንደተገነዘቡትና የቤተ ክርስቲያንን ሕልውና እየተገዳደረ እንዳለ አስረድተዋል፡፡
በመጨረሻም በቀረቡት ዳሰሳዊ ጽሁፎች መነሻነት በአሁኑ ስአት ቤ/ክያን እየገጠማት ያለው ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ጫናዎች ምንድናቸው? የቤተ ክርስቲያናችን የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ ምን ዓይነት መንገድ ይከተል? ይህንን ሀገራዊ ለውጥ ለማምጣት የእኛ ድርሻ ምን ይሁን? የሚሉ ሦስት ዋና ዋና የመወያያ ሐሳቦች /ነጥቦች/ ለታዳሚዎች ቀርበዋል፡፡
የሰብሰባው ተሳታፊዎችም በተነሡት ነጥቦች መነሻነት በርካታ ሐሳባቸውን የሰነዝሩ ከመሆናቸውም በላይ ቤተ ክርስቲያናችን አሁን ላለችበት ወቅታዊ ተግዳሮት በውጭ ካለው ችግር ይልቅ በውስጥ ያሉት ብልሹ አሠራሮችና የመልካም አስተዳደር ዕጦት፤ ሀላፊነት የጎደላቸው አገልጋዮች የሚፈጥሩት ወከባ፤ ፍትሕ አልባ የሥራ ቅጥር፤ ዕድገትና ዝውውር እንዲሁም የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ቸልተኝነት የታየበት አካሄድና ወቅቱን ያላገናዘቡ ውሳኔዎች፤ ጸብ አጫሪና የክርስቶስን ብሎም የቤተ ክርስቲያንን ስምና ዝና የሚያጎድፉ ፅሁፎች በየዘመኑ በስርዋጽ መልኩ ከመግባታቸውም ባሻገር በጊዜው አለመታረማቸው ለዚህ ሁሉ ግድፈት መነሻ ምክንያቶች መሆናቸውን ቁጭት በተሞላው ንግግራቸው ድምጻቸውን አሰምተዋል፡፡
በሌላ መልኩም ቤ/ክያን ከፖለቲካ ጋር ያላት ጥብቅ ጋብቻ ከራሷ ሰማያዊ ዓላማ ይልቅ ወደ ምድራዊ ምልከታ እንድትመለስ ከማድረጉም በላይ የስብከተ ወንጌሉን አገልግሎት ከመዘንጋቷ የተነሣ ከመንፈሳዊ ዓለም ወጥታ ምድራዊ ሀብትን ወደ መሰብስብና ማከበት መግባቷን ገልጸዋል፡፡ ከዚህም በማያያዝ ከፍተኛውን ሀላፊነት የተሸከመው ቅዱስ ሲኖዶስም አንቀላፍቷል ብለው ይነቃ ዘንድም የንቁ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በዕለቱ ስብሰባውን ሲመሩት ከነበሩት ብጹዓን አባቶች መካከል ብጹፅ አቡነ ማቲዎስ የዳሰሳዊ ጥናት አቅራቢዎቹንና የታዳሚዎቹን ሐሳብ በመቀበልና በመደገፍ እናንተን የቤተ-ክርስቲያንችንን ልጆች በዚህ መንፈስ ስንመለከት የኩራት መንፈስ ይሰማናል፤ የነገራችሁንንም ሐሳቦች ተቀብለናል ነገር ግን ስብሰባችን የአሽዋ ጭብጦ እንዳይሆን አሳስበው የውስጥ ችግሮቻችንን በሂደት እንቀርፋለን ወቅታዊውን የውጭ ችግር ግን እንደ ኢያሱ ሠራዊት በአንድ መንፈስ ሆነን ልንታጋለው ይገባል ሲሉ የቅዱስ ፓትርያሪኩ ረዳት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ደግሞ ሥራ የጀመርነው ገና ዛሬ ነው በማለት ለጉዳዩ አጽንዖት መስጠታቸውን አመላክተዋል የተሰነዘረውን ሐሳብ ወደ ሲኖዶስ እንደሚያደርሱም ቃል ገብተዋል፡፡
ጠቅለል ባለ መልኩ የቤተ- ክርስቲያናችንን ችግሮች ስንመለከት በዳሰሳዊ ጥናቱም ሆነ በተሳታፊዎች ከተገለጸው በላይ መሆኑን የሁላችን ኅሊና የሚቀበለው ሐቅ ነው፡፡ ማለትም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በውጭና በውስጥ ባሉ ኀሊና ቢሶችና ጊዜያዊ ጥቅመኞች በእጅጉ እየታወከች ትገኛለችና፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ በውጭ ካለው ተፅእኖ ይልቅ የበረታውና የከፋው በውስጥ ያለው ግራ ዘመም አስተሳሰብና ጎጠኝነት፤ያለ እውቀትና መስፈርት የሚደረግ የሥራ ምድባና ዝውውር፤ ለቅዱስ ቃሉ ያለው ቦታ በእጅጉ ከመውረዱ የተነሣ ከዋናው አገልግሎት ይልቅ በድጋፍ ሰጭ ሥራዎች ላይ መጠመድ፤ ራዕይ አልባ ትውልድ በየዘመኑ በቤተ ክርስቲያን መሰግሰግ፤ ወደ ሀላፊነት የሚመጣበት መንገድ ትምህርትና እውቀት እንዲሁም ልምድ ሳይሆን እንደ ፌደሬሽን ምክር ቤት ኮታዊ አሠራርን መከተል፤ ከእግዚአብሔር ፍርድና ተግሳጽ ይልቅ የሰዎችን ተግሳጽና ፍርድ መፍራት፤ ከእግዚአብሔር ክብር ይልቅ የራስን ዝና፤ ስምና ማዕረግ ማስቀደም፤ ወጣቱን የተማረ የሰው ኃይል ጡረታ ያወጣ አሠራር መዘርጋትና መማር መረገም እስኪመስል ድረስ የተማረውን የሰው ኃይል ያገለለ እንቅስቃሴ ማድረግ ሲሆኑ፤
በጥቅሉ ስንታዘብ ግን መንፈስ ቅዱስን ያገለለና ሥጋዊ አሠራርንና ሀብትን ያስቀደመ ክፉና ምትሐታዊ አካሄድ ውስጥ መግባታችን ለዚህ ሁሉ አዙሪት ያዳረገን መሆኑን ልብ ያለውና የቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪ ሁሉ ሊገነዘበው የተገባ እውነት ነው፡፡
ከእነዚህ ውስጣዊ የቤተ ክርስቲያን ችግሮች በተጨማሪ ደግሞ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀገራዊ ውለታና ያበረከተችውን አስተዋጽኦ የዘነጉ የውጭ ኃይሎች በቤተ-ክርስቲያን በተፈጠሩ አንዳንድ ክስተቶችን በመጠቀም ለፖለቲካ ፍጆታ የሚያውሉና በሌሎች ሃይማኖቶች የተፅእኖ ክልል ውስጥ እንድትወድቅ የሚፈልጉ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን መኖራቸውም የሚዘነጋ ጉዳይ አይደለም፡፡ ለዚህም ምስክር ለማቆም ብዙም ድካም የሚጠይቅ ሳይሆን አሁን ያለውን ወቅታዊ ችግር መገንዘቡ ከበቂ በላይ ነው፡፡
ለእነዚህ ሁሉ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች እየተሰባሰቡ መወያየቱና መመካከሩ መልካም ቢሆንም ከጊዜያዊ እሳት ማጥፋት መርሐ ግብር ተለይቶ የሚታይ አይደለም፡፡ በየዘመናቱ የሚነሡና ሊነሡ የሚችሉ ችግሮችን በዘለቄታዊነት መፍታት የምንችለው ግን የእግዚአብሔርን መንፈስ ያስቀደመ አሠራር ዘርግተንና የውሰጥ ችግራችንን በአስቸኳይ ተነጋገርን በመፍታት ወደ ቀደመ ክብራችን በመመለስና ውስጣዊ አንድነታችንን ስናጠንክር ብቻ ነው፡፡
በሀገረ ስብከቱ ሚዲያ ክፍል