በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ሥር ለሚገኙት የአድባራትና ገዳማት የስብከተ ወንጌል ኃላፊዎች ለሁለት ቀናት ሲሰጥ የቆየው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ባማረ መልኩ ተጠናቀቀ

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ ዋና ክፍል አዘጋጅነት በትናንትናው ዕለት የተጀመረው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና መርሐ-ግብር በዛሬው ዕለትም ቀጥሎ የዋለ ሲሆን በመጀመሪያ በነበረው መርሐ -ግብር “ዘመኑን ማወቅ /ግሎባላይዜሽን/ ” በሚል ርዕስ በመ/መ ሳሙኤል እሸቱ ተሰጥቷል።
መምህሩ ስለ ስብከተ ወንጌል ምንነት በሰፊው ያነሱ ሲሆን ስብከተ ወንጌል የወንጌሉን የምሥራች ቃል ማብሰሪያ ብቸኛው መንገድ መሆኑን ገልጸው በጌታችን በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኝ የኃጢአት ሥርየትና የዘለዓለም ሕይወት የሚታወጅበት መንገድ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተው አብራርተዋል።
አያይዘውም የስብከተ ወንጌል ዋናው ዓላማ የጠፋን መፈለግ፣ያላመነውን ማሳመን፣ፍቅርን መስበክና የእግዚአብሔርን መንግሥት ማስፋፋት እንደሆነ በሰፊው ጠቅሰው የመልእክተኛው አጠቃላይ ዝግጁነት ለተቀበለው መልእክት ታማኝ መሆን፣ የመልእክቱን ክቡርነት መረዳት፣ የላከውን ማንነትና የላከበትን ዓላማ ማወቅ እንዳለበት ገልጸዋል።
በሌላ መልኩ መምህሩ በዘመናችን በስብከተ ወንጌል ዙሪያ እየተስተዋሉ ያሉትን ተግዳሮቶቾ በሰፊው የጠቀሱ ሲሆን ያለውን ክፍፍል፣ድህረ ዘመናዊነት ያመጣውን ጫና፣ እንዲሁም በተለያዩ መንገዶች እየተከሰቱ ያሉትን መከራዎችና ፈተናዎች አብራርተው የመፍትሔ አቅጣጫዎችንም ጠቅሰዋል፤ ከተሳታፊዎች ለተነሣላቸው ጥያቄዎችም መልስ ሰጥተዋል።
በሁለተኛ በነበረው መርሐ-ግብር “የቤተክርስቲያን ተግዳሮትና መፍትሔ” በሚል ርዕስ በመ/ር ዳንኤል ሰይፈ የግንዛቤ ማስጨበጫ የተሰጠ ሲሆን ዘመነ ሐዋርያትንና ዘመነ ሰማእታትን አካተው በየዘመኑ የነበሩትን የቤተክርስቲያን ተግዳሮቶችን ጠቅሰዋል።
አክለውም የቤተክርስቲያንን ዓላማ በማወቅና በመረዳት ዘመኑን የሚዋጅ፣የሚያይ፣የሚያነብና የሚዳስስ አገልጋይ በመሆን፣አገልጋይነትን አምኖ በመቀበል፣ አርዓያ በመሆን፣ በጸሎት ሕይወት በመበርታትና ተግቶ በማገልገል የመፍትሔ አካል መሆን እንደሚገባ ትኩረት ሰጥተው አብራርተዋል።
በመርሐ -ግብሩ ላይ በአርቃቂ ኮሚቴ ባለ አስራ ሁለት ነጥብ የጋራ አቋም መግለጫ ተነቧል።
መርሐ -ግብሩን የመሩት የሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ ዋና ክፍል ኃላፊ መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ ለብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ፣ለክቡር ዋናው ሥራ አሰኪያጁ መ/ር አካለወልድ ተሰማ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ለሰጡት መምህራን፣ለክፍላተ ከተማ የስብከተ ወንጌል ኃላፊዎችና ለሚዲያ ክፍል አባላት ምስጋና አቅርበው ለአድባራቱና ገዳማቱ የስብከተ ወንጌል ኃላፊዎች መመሪያዎችን አስተላልፈዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናውን በተመለከተ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ያለፈውን የአገልግሎታችንን ሕይወት በመፈተሽ ጠንካራው ጎናችንን የምናስቀጠልበት፣ ደካማው ጎናችንን የምናርምበትና ለመጪው ጊዜ የተሻለ አገልግሎት የምናገለግልበትን እውቀትና ልምድ ያገኘንበት መርሐ -ግብር ነው በማለት አብራርተዋል። አያይዘውም ሀገረ ስብከቱ ቅድሚያ ለስብከተ ወንጌል እንደሚሰጥ ገልጸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናው እንዲዘጋጅ ላደረጉት ለሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ ዋና ክፍል ኃላፊ ለመልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ ያላቸውን አድናቆት አቅርበው በጸሎት ጉባኤውን ዘግተዋል።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ መ/ር ዋሲሁን ተሾመ