በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የጥምቀት በዓል ዓላማውን በጠበቁ መልኩ በሰላም መከበሩን የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ገለጹ

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የጥምቀት በዓል ዓላማውን በጠበቁ መልኩ በሰላም መከበሩን የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ገለጹ።
ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያችን በየዓመቱ በዓደባባይ ከምታከብራቸው በዓላት መካከል አንድ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት ነው።
በዓሉ በዚህ ዓመት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በ250 አብያተ ክርስቲያናት በ66 አብሕርተ ጥምቀት የተከበረ ሲሆን በካህናት ምስጋና በሰንበት ተማሪዎች ሽብሻቦና ዝማሬ ያለምንም ችግር ደምቆ ውሏል ብለዋል የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጂ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ገልጸዋል።
ዋና ሥራ አስኪያጁ አክለውም በዓሉን በሥርዓትና በወጥነት ለማክበር ይቻል ዘንድ ከወጣው የውጫና የመግቢያ ሰዓት አኳያም ከ12 ገዳማትና አድባራት ውጭ ሁሉም በሰዓቱ የተመለሱ ሲሆን ተናቦና ተግባብቶ የማስፈጸም ትግበራው እጅግ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።
ቀጥለውም በዓሉ በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ያለምንም የጸጥታ ችግር በላቀ መንፈሳዊነትና ልብን ባሳረፍ ኦርቶዶክሳዊነት ተከብሯል ብለዋል።
በዚህ በዓል ከሀገረ ስብከቱ ጀምሮ እስከ አጥቢያ የላው መዋቅር ተገነዛዝቦ አገልገሎቱን ያከናወነ መሆኑን የተጠቆሙት ዋና ሥራ አስኪያጁ ከመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች፣ የጸጥታ አካላት፣የጤና ተቋም እንዲሁም ማኅበረ ካህናቱ፣ ሰንበተ ተማሪዎች፣ የየአካባቢው ወጣቶች፣ ምዕመናንና ምዕመናት ላደረጉት መልካም ተግባርና ታዛዥ መንፈሳዊነት በእጅጉ ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።
በመጨረሻም የዛሬውን የጥምቀት በዓል በልዩ ኦርቶዶክሳዊ ሥርዓትና መናበብ እንደተከበረ ሁሉ በነገው ዕለት የሚከበረውን የቃና ዘገሊላ በዓልና ከዚያ በኋላ ለሚገቡ ታቦታትም መሠረታዊ መዳረሻ ዓላማውን በጠበቀ መልኩ በታዛዥነትና የበዓሉን በረከት በማሰብ እንዲከበር አሳስበዋል።
“ጥምቀት ለድኅነት ለሕይወት ዘለዓለም”

©የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ