በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የዕቅድ ዝግጅት እና አፈጻጸም እንዲሁም ክትትልና ግምገማን በተመለከተ ሥልጠና ተሰጠ
ዛሬ ታህሳስ 13/2013 ዓ/ም ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባ እና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፥ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊና የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፥ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ስዩማን አካለወልድ ተሰማ ፥ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ስብሐት ሳህሉ፥ የሁለቱ አህጉረ ሰብከቶች የዋና ክፍል ኃላፊዎች እና የየክፍሉ ኃላፊዎች እንዲሁም የሰባቱ ክፍላተ ከተሞች ክፍል ኃላፊዎች በተገኙበት የዕቅድ ዝግጅት እና አፈጻጸም እንዲሁም ክትትልና ግምገማ ያካተተ ሰፋ ያለ ሥልጠና ተሰጥቷል።
ሥልጠናውን የሰጡት መምህር ተስፋ ጥሩነህ የኢትዮ ቴሌኮም ሠራተኛ ሲሆኑ የዕቅድ ዝግጅት፥ አፈጻጸም እንዲሁም የክትትልና ግምገማ ምንነት፥ ዓላማውና ጥቅሙ በደንብ አብራርተዋል።
ከዚህ አያይዘውም ዕቅድ ለአንድ ተቋም ህልውና ለማረጋገጥ እና ከግቡ ለማድረስ፥ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን ለመምራትና ለመወሰን፥ ስራውን በብቃት ለመወጣት እና የድርጅቱ የሥራ አመራር በተቀናጀ መልኩ ለመፈጸም እንዲሁም የተቋሙን ራእይና ተልእኮ በአግባቡ ለማከናወን ዕቅድ ሁነኛ መሳሪያ መሆኑን ገልጸዋል።
በመቀጠልም የዕቅድ ዓይነቶች ከጊዜ አኳያ፥ ከዕቅድ አድማስ አኳያና ከሚሠራው የሥራ ባሕርይ አንጻር፥ የዕቅድ አዘገጃጀት፥ የዕቅድ አላላክ፥ አፀዳደቅ እና ግብረ መልስ አሰጣጥ በሰፊው አብራርተዋል።
በመጨረሻም ከሰልጣኞች ለተነሡት ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ሥልጠናው ተጠናቋል።
በሥልጠናው የተገኙት ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊና የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሥልጠናው በመገኘቴ እጅግ ደስ ብሎኛል፤ ሥልጠናው ለቤተክርስቲያኒቱ በጣም ወሳኝ ነው፤ እኔም ብዙ ቁምነገር ተምሬበታለሁ በዚህ ቀጥሉ ብለዋል።
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባ እና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በቤተክርስቲያኒቱ የሚታቀደው ዕቅድ ሦስት ክፍል ያቀፈ መሆኑን የገለጹ ሲሆን እነሱም የሀገረ ስብከቱ ዋና ክፍል ኃላፊዎች፥ ክፍለ ከተሞች እና አጥቢያዎችን ያካተተ መሆን እንዳለበት አብራርተዋል።
በመጨረሻም ብፁዕነታቸው ለሠልጣኞቹ አባታዊ መልእክትና መዋቅራዊ አደረጃጀትን በተመለከተ መመሪያን በማስተላለፍ ዝግጅቱን በጸሎት ዘግተዋል።
መ/ር ኪደ ዜናዊ የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ
ፎቶ: በዋሲሁን ተሾመ