በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአራዳ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ባለፈው የአገልግሎት ዓመት የተሻለ የሥራ አፈጻጸም ላሳዩ ገዳማትና አድባራት የምስጋና መርሐ ግብር አከናወነ

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአራዳ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የ ፳፻፲፯ ዓ.ም የበጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትና የምስጋናና መርሐ ግብር አከናወነ።
መርሐ ግብሩ የተዘጋጀው በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ሲሆን ፳፻፲፯ በጀት ዓመት የሥራ ሪፖርት በመጋቤ ሠናይት የቻለው የአራዳ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሪፖርት ቀርቧል።
በሪፖርቱ በክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ሥር የተሰሩ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች በዝርዝር ተዳሷል።ከዚህም በተጨማሪ በአብነት ትምህርትና በስብከተ ወንጌል ፣በበጎ አድራጎት፣በሰው ኃይልና ቁጥጥር፣ በሠራተኛና አሠሪ መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በመፍታት ረገድ ክፍለ ከተማው ያስመዘገበውን አመርቂ ውጤት አቅርቧል ።
የአራዳ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት በስሩ ፳ የሚደርሱ አድባራትና ገዳማት የያዘ ሲሆን በበጀት ዓመቱ የየአብያተ ክርስቲያናቱ የገቢ ሁኔታም በዝርዝር የቀረበበት ነበር፡፤
ከዚህም በተጨማሪ ክፍለ ከተማው የገጠሙትን ተግዳሮቶችም ለሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ለብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ያስረዱ ሲሆን በዋናነት የክፍለ ከተማው ጽ/ቤት በግለሰብ ኪራይ ሥር መሆኑ ፣የክፍለ ከተማው ወርኃዊ የሥራ ማስኬጂያ አነስተኛ መሆን ከተጠቀሱት ተግዳሮቶች መካከል ይገኙበታል፡፡ለዚህም ብፁዕነታቸው የመፍትሄ ሀሳብና አባታዊ መመሪያም ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም በክፍለ ከተማው ሥር ለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትና ለብፁዕነታቸው የሰርተፍኬትና የምስጋና መርሐ ግብር ተከውኗል፡፡
ኅዳር ፪ ቀን በተዘጋጀው በዚህ መርሐ ግብር ላይ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና የሀድያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፤ መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ መጋቤ ሠናያት የቻለው የአራዳ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የክፍለ ከተማው አድባራትና ገዳማት ሓላፊዎች በየደረጃው ተገኝተዋል፡፡

የዘገባው EOTC Tv ነው።