በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የነበርውን የመልካም አስተዳደር እና የፋይናንስ ችግር ሙሉ በሙሉ ይፈታል በተባለው መዋቅርዊ የአሠራር ለውጥ እና አደረጃጀት ላይ ውይይት በመካሄድ ላይ ነው

0014

ቀደም ብለን በድህረ ገፃችን ስናሰራጭ እንደቆየነው ሀገረ ስብከቱ ከሚያዘያ 2005 ዓ.ም ጀምሮ በአሠራር ለውጥ ውስጥ የቆየ ሲሆን በዚህም መነሻነት ሀገረ ስብከቱ በቃለ ዓዋዲው መሠረት በ7 ወረዳ/ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ተዋቅሮ ለ3 ወራት የሚያገለግል ጊዚያዊ ውስጠ ደንብ ከመዘጋጀቱም በላይ ከሀገረ ስብከቱ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ድረስ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን አዲሱ የሀገረ ስብከቱ መዋቅራዊ የአሠራር ለውጥና አደረጃጀት እጅግ ከፍትኛ ልምድ ባላቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ተዘጋጅቶ ለጥቅምት 2006 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ቀርቦ ከታዬ በኋላ እየተዘጋጀ ካለው ስርዓተ ቤተ ክርስቲያን፤ቃለ ዓዋዲና ዘመኑ ከሚከተለው የአሠራር ሥርዓት በመዘጋጀቱና ለሀገረ ስብከቱ ያለው ጠቃሚነት እጅግ የላቀ መሆኑን ስለታመነበት የሚመለከታቸው አካላት ውውይት አድርገውበት በቋሚ ሲኖዶስ እንዲፀድቅ በተወሰነው መሠረት የመጀመሪያው ዙር ውውይት ህዳር 17 /2006 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በዚሁ ውውይት ላይ የተገኙ ባለሥልጣናትና ተሳታፊዎች ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ፤ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት እና የጅማ ሀገረ ስብከተ ሊቀ ጳጳስ፤ ክቡር ንቡረ ዕድ አባ ዮሐንስ ገ/ሕይወት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ክቡራን የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ኃላፊዎች፤ የክፍል ኃላፊዎች፤የክፍላተ ከተማው የሥራ ኃላፊዎች እና እንዲሁም የጠቅላይ ቤተ ክህነት መምሪያና የድርጅት ኃላፊዎች በተገኙበት ውውይቱ በመካሄድ ላይ ነው ፡፡

ይህ ውውይት እስከ ህዳር 18/2006 የሚቆይ ሲሆን ሁለተኛ እና የሦስተኛው ዙር ውውይት ደግሞ ህዳር 27፤28፤29እና 30/2006 ታህሣሥ 4፤5፤6፤7፤11፤12፤13 እና 14/2006 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በመግቢያ ንግግራቸው የውውይቱን መጀመር በይፋ አብሥረው ባስተላለፉት ቃለ ምዕዳን እና የሥራ መመሪያ በቤተ ክርስቲያን ከላይ እስከ ታች ባለው የሥራ ኃላፊነት ላይም ሆነ በተለያየ የሥራ ዘርፍ የምንገኝ አጠቃላይ ሠራተኞች /አገልጋዮች/ ሁሉ እስከ አሁን ድረስ የቤተ ክርስቲያናችንን ስም ያስጠፋውንና መልካም ስማችንን እያጎደፈ ባለው የመልካም አስተዳደር እጦትና የሥነ ምግባር ጉድለት ከሥር መሠረቱ ነቅለን በማስወገድ ሁላችንም ታማኞች ሆነን ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው፣ ዘመኑን የዋጀ አሠራርን መከተል እንደሚገባን ከገለጹ በኋላ የተቀመጥንበት ወንበር ትልቅ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ በሥራችን ቸልተኛ መሆን የለብንም ብለዋል፡፡

ቅዱስነታቸው አያይዘውም ለአዲሱ አደረጃጀት የለውጥ ሐዋርያነት ግንባር ቀደም ሆነን የቤተ ክርስቲያኒቱን ታሪካዊነት፣ ጥንታዊነትና ሉዐላዊነት አስከብረን የቀደመ ስሟን አስመልሰን ሀብቷንና ንብረቷን በሕጋዊ አሠራር ተቆጣጥረን በአግባቡ በሥራ ላይ ለማዋል ይቻል ዘንድ በየደረጃው ያለን ሁላችንም አገልጋዮች የለውጥ ሰው ለመሆን፣ ለውጡን አምኖ ለመቀበል በአዲሱ የሀገረ ስብከቱ መዋቅራዊ የአሠራር ለውጥና አደረጃጀት ላይ የውውይት መርሃ ግብር መዘጋጀቱ በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን እና በየደረጃው ካሉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መነጋገሩና መወያየቱ እጅግ ጠቃሚ መሆንኑ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በኋላ ቀጥታ ወደ ውውይይቱ የተገባ ሲሆን አዲሱ የሀገረ ስብከቱ መዋቅራዊ የአሠራር ለውጥና አደረጃጀት በዘጋጁ 15 የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆችና ባለሞያዎች ልብን በሚነካ በቤተ ክርስቲኒቱ ቋንቋ አገላለፅ የነበረውን ችግር ነቅሰው ካወጡ በኋላ መፍትሄውን በማስቀመጥ ከ950 ገፅ በላይ ያለው ከሀገረ ስብከት እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ድረስ የሁሉም የሥራ ኃላፊነትና የሥራ መመሪያ ያለው የሀገረ ስብከቱ መዋቅራዊ የአሠራር ለውጥና አደረጃጀት ለውውይት ቀርቦ ከፍተኛ ጉጉት በተሞላበት ሁኔታ በቡድንና በጋራ ውውይይት እየተካሄደበት ይገኛል::መዋቅራዊ ጥናቱ የሰው ሀብት አስተዳደር፣ የሰው ኃይል ልማት፣ የፋይናንስ፣ የኦዲትና ኢንስፔክሽን፤ የዕቅድ፣ ክትትልና ግምገማ፤ የግዥ፣ ሽያጭና ንብረት አስተዳደር፤ ልማትና ምግባረ ሠናይ፤ የቅርስና ቱሪዝም፤ የመንፈሳዊ ፍትሕ፣ የአስተዳደር እና የሥራ ክርክር ጉዳዮች ችሎቶችን የተመለከቱ ፖሊሲዎች፣ መመሪያዎችና ዝርዝር አሠራሮች ይገኙበታል፡፡ይህ መዋቅራዊ የአሠራር ለውጥና አደረጃጀት ሥራ ላይ ሲውል የነበረውን የመልካም አሰተዳደር ችግር ሙሉ ለሙሉ ይቀርፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡በመሆኑም ለዚሁ ታሪካዊና ወደ ቀድሞ ስማችን ለመመለስ በተዘጋጀው መዋቅራዊ የአሠራር ለውጥና አደረጃጀት ላይ አንድ ልብ ሆነን ሀገረ ስብከቱ ለሚያደርገው ሁለንተናዊ የሠራር ለውጥና እድገት በጋር ሆኖ መሥራት የቤተ ክርስቲያን ልጅነታችንን ከመቸውም በላይ የምናረጋግጥበት ወቅት በመሆኑ ሁሉም አቅሙ በሚፈቅደው መልኩ በአንድነት መንፈስ ሊረባረብ ይገባል እንላለን፡፡

{flike}{plusone}