በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመልካም አስተዳደር አተገባበር
በአንድ መሥሪያ ቤት /ድርጅት/ ውስጥ ከሚያስፈልጉ ቁልፍ ጉዳዮቸ መካከል ቀዳሚ ሊባል የሚችለው መልካም አስተዳደር እንደሆነ የማህበረሰብ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ በእንዚህ መሁራን ምልከታ መሠረት በአገልጋይና ተገልጋይ መካከል በመተማመን ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ሊፈጠር የሚችለው መሥስሪያ ቤቱ /ድርጅቱ/ አስተማማኝ የመልካም አስተዳደር ሁኔታን መገንባት ሲችል ብቻ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በተለይም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ያለው የሰው ኃይል እጅግ ብዙ ስለሆነ ሥራ እና ሠራተኛን ለማገናኘት እና አመርቂ ሥራ ለመሥራት መልካም አስተዳደር የግድ አስፈላጊ ነው፡፡
በዚህ መሠረት መልካም አስተዳደር የሚገለጽባቸው ሁኔታዎች በርካታ ናቸው፡፡ ለአብነት የሕግ የበላይነት፣ ተጠያቂነት፣ፍትሐዊትና ግልጽነት ዋና ዋናዎቹ የመልካም አስተዳደር መገለጫዎች ናቸው፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች የሚገለጹበት መልካም አስተዳደር በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ዘላቂ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ያስችላል፡፡
መልካም አስተዳደር በሰፈነበት መሥሪያ ቤት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የተረጋገጠ በመሆኑ የተገልጋዮች ቅሬታ በእጅጉ ይቀንሳል፡፡ የዚህ አይነቱ አሥተዳደር የሠራተኞችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ የሚያረጋግጥ በመሆኑ የሚወጠኑ የቤተ ከርስቲያኒቱ የልማትም ሆነ ሌሎች ሃይማኖታዊ ፋይዳ ያላቸው መርሐ ግብሮች በጊዜው ሕዝባዊ መሠረትን ይጎናጸፋሉ፡፡
በዚህም በሀገረ ስብከቱ ያሉ ሠራተኞች፣ ካህናትና ልዩልዩ ሠራተኞች ከሀገረ ስብከቱ የሚጠብቋቸው የተለያዩ አገልግሎቶችን በሚፈልጉት ጥራት፣ ፍጥነትና ብቃት ይፈጠራል፡፡ የዚህ አይነቱ ሁናታ በሀገረ ስብከቱ ኃላፊዎችና በአጥቢተያው ሠራተኞች መካከል ጠንካራ መተማማን እንዲኖር ያደርጋል፡፡
ጠንካራ መተማመን ደግሞ የቤተ ክርስቲናችን እድገትና ብልጽግና እውን እንዲሆን ያደርጋል፡፡
ለመሆኑ መልካም አስተዳደር ለምን ያስፈልጋል?
በየትኛውም የአስተዳደር እርከን ተገልጋይ የሚያገኘው አገልግሎት ይኖራል አገልግሎት ማግኘቱ ብቻ ሳይሆን አገልገሎቱን ያገኘበት መንገድ ግልጽና አርኪ ሊሆንለት ያስፈልጋል፡፡ ይህ የመልካም አስተዳደር ሂደት ጥራትና ብቃት ነው አገልጋዩን ከተገልጋዩ ጋር ማግባባት ላይ የሚያደርሳቸው፡፡ የማይቻለውን አይቻልም ማለት መልካም አስተዳደርን የሚያጠፋ አይደለም፡፡ የማይቻልበትን ሕግና ደንብ ጠቅሶ ወይም ያለውን አሠራር አብራርቶ ማሰናበት የመልካም አስተዳደር አንዱ ክፍል ነው፡፡ ሁሉም ተገልጋይ የጠየቀውን አገልግሎት ማግኘት የማይቻልባቸው አያሌ ምክንያቶች አሉ፡፡
በተቃራኒው የሚቻለውን በተቻለ ፍጥነት መሥራትና ተገልጋዩን ማርካት ያስፈልጋል የሚጠበቅበትን አሟልቶ ግዴታውን ተወጥቶ የሚቀርብ ጠያቂ ዛሬ ነገ ቆይ በኋላ ሊባል አይገባም ይህን ከተባለ መልካም አስተዳደር አፈር ድሜ በላች ማለት ብቻ አይደለም፡፡ እባክህን ቶሎ ጨርስልኝ የሚል ልምምጥ እንዲያቀርብና ከበር ወጥቶ መብትን በመስኮት ለመግዛት ብሎም ዘመድና ወዳጅ እንዲፈልግ ግድ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህ በተራው ሙስናን ያስከትላል፡፡
ማግኔት ብረትን እንዲስብ ነገሮችም ይሳሳባሉ፤ ችግር ችግርን ይስባል የመልካም አስዳደር እጦት ሙስናን ያስከትላል፡፡ ሙስና የሀገር ውድቅትን የህዝብ ድህነትን ያመጣል የታሰበው እድገተና ብልጽግና እንዳልታበ የተሰራው ሥራም ምንም እናዳልተሠራ ያስቆጥራል፡፡ የመልካም አስተዳደር መስፈን በበኩሉ አያሌ ነገሮች ይስባል መልካም አስተዳደር ሲሰፍን ሥራ ና ሠራተኛ ይግናኛሉ፡፡ ሰላም የጋራ አላማና ግብ ይሆናል፡፡ በአንድ ጊዜም ባይሆን በሂደት ካቀድነው ግባችን መድርሳችን አይቀርም፡፡
ባንድ ወቅት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በቤት ክርስቲያኗ ያለውን ዘርፍ ብዙ ችግር ከዘርዘሩ በኋላ ለመፍትሔው እንነሣ ማለታቸው ይታወቃል፡፡
በዚህ መሠረት ቅዱስነታቸው የቤተ ክርስቲያኗ የመጨረሻው አመራር ሰጭ ከመሆናቸውም በተጨማሪ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ልዩ ሀገረ ስብከታቸው ሰለሆነ ለሀገረ ሰብከቱ መፍትሔ ያመጣል ብለው ያሰቡትን ተግባራዊ በማደርጋቸው ከሁለት ወራት በፊት በትምህርት ዝግጀታቸውና ባላቸው የሥራ ልምድ ሀገረ ስብከቱን ከገባበት ብልሹ አሠራር ያወጡታል ተብሎ የታመንባቸውን ሊቀ ማእምራን የማነብርሃን ዘመንፈ ቅዱስን የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብርን ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አድርገው በመደመደባቸው በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር ያሉ የገዳማትና አድባራት አስተዳደራዎች፣ ጸሐፊዎች፣ ሰባክያነ ወንጌልና መምህራን/ ካህናት ከወዲሁ ነበር ለዋና ሥራ አስኪያጁ እና የምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ ያላቸውን ድጋፍ ልብሰ ተክህኖ በመልበስ በሀገረ ሰብከቱ የመሰብሰቢያ አዳራሻ በመገኘት የገለጡት፡፡
ሊቀ ማእምራን የማነብርሃን ዘመንፈስ ቅዱስ እና ምክትላቸው መጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብርም የመጀመርያ ሥራቸው ያደረጉት የተመረጡ ሰዎች እየተጠሩ ከመግባት ውጪ ለቤተ ክርስቲያኗ ሊቃውንትና ካህናት ዝግ የነበረውን የሀገረ ስብከቱ የግቢ በር ክፍት ማድረግ ነበር፡፡
አሁን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በር ክፍት ስለሆነ ለማንኛው ባለጉዳይ ወደ ፈለገው ቢሮ ገብቶ ጉዳዩን ማስፈጸም ከባድ አይደለም፡፡
በዚህ መሠረት ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አያሌ የለውጥ ሥራዎች የተሰሩ ሲሆን ከነዚህ አበይት ክንውኖች መካከል የተወሰኑት ለአብነት ተጠቃሾች ናቸው፡፡
አንደኛ፡- በሀገረ ስብከቱ ሥር ሰዶ በነበረው ብልሹ አሠራር ምክንያት ከሥራና ከደመወዝ ታግደው ሲሰቃዩ የነበሩ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ገብተው ችግራቸውን ለሚመለከተው ክፍል ነግረው መፍትሔ እንዳያገኙ በር ተዝግቶባቸው ይፍትሐ ያለህ በማለት ያነቡት የግፍ ዕንባ መታበሰ አለበት በማለት ዋና ሥራ አስኪያጅና ምክትላቸው ከሀገረ ስብከቱ የክፍል ኃላፊዎች ጋር በመመካከር ወደ ሥራና ደመወዝቸው እንዲመለሱ በመደረጉ አሁን በሀገረ ስብከቱ ከሥራና ከደመወዝ ታገደኩ የሚል ባለጉዳይ ማግኘት ከማይቻልበት ደርሰናል ምክንያቱም ችግሩ ተወግዶአልና ነው፡፡
ሁለተኛ፡- በሀገረ ስብከቱ ሥር ባሉ አድባራት እና ገዳማት በሙዳየ ምፅዋት ላይ ይደረጋል ተብሎ የሚገመተውን ሰጋት ለማስቀረት ብሎም ሥራን ለማቀላጠፍና ጊዜንም በአግባቡ ለመጠቀም ሀገረ ስብከቱ ለአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሙዳየ ምፅዋት በምን ዓይነት ሁኔታ መቆጠር እንዳለበት ከውሳኔ ላይ በመድረሱ ከዚህ የሚከተለውን ደብዳቤ አስተላልፎ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር የሚገኙ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትም ሀገረ ስብከቱ ያስተላለፈው ውሳኔ የቤተክርስቲያንዋን ንብረት ከብክነት ይጠብቃል ብለው ስላመኑበት ተግባራዊ በመደረጉ አሁን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር ያሉ ገዳማት፣አድባራት እና ካቴድራሎች በዚህ መሠረት እየተጠቀሙ እና ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ሀገረ ስብከቱ ለአጥቢያ አቢያተ ክርስቲያናት ያስተላለፈው ሰርኩላር ደብዳቤ ከዚህ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ጉዳዩ፡- የሙዳየ ምፅዋት ገንዘብ አቆጣጠር የስዕለት ንብረት ዋጋ አገማመትን ይመለከታል
ቤተክርስቲያናችን ከምዕመናን በሙዳየ ምፅዋት ሣጥን የሚገባውን ገንዘብና ንብረት አቆጣጠር ለማሻሻልና ከዚህ ጋር በተያያዘ በቤተክርስቲያናችን ቅሬታ እየፈጠሩ ያሉ አሠራሮችን ለመቅረፍና ግልፅነትን ለማስፈን አስፈላጊ የሆኑ አሠራሮችን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ የሙዳየ ምፅዋት ገንዘብ አቆጣጠርን መሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የሚከተሉት መመሪያዎች ተግባራዊ እንዲደረጉ መመሪያ መስጠት አስፈላጓል፡፡
ስለዚህ፡-
1ኛ.የሙዳየ ምፅዋት ገንዘብ በበዓላት ከሀገረ ስብከቱ ተወካዮች በተጨማሪ የደብሩ (የካቴድራሉ) ቄስ ገበዝ፣የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ፣ የሰበካ ጉባኤ የምዕመናን ተወካዮችና በአቅራቢያው የሚገኝ የንግድ ባንክ ባለሙያዎች በተገኙበት እንዲቆጠር፣ በአዘቦት ደግሞ ከሀገረ ስብከቱ ተወካዮች በስተቀር የተጠቀሱት በጠቅላላ በተገኙበት እንዲቆጠር፣
2ኛ.የሰበካ ጉባኤ ም/ሊቀመንበር በቆጠራ ላይ የማይገኙበት በቂ ምክንያት ካለ ይህን በጽሑፍ ለሰ/ገ/ጽ/ቤቱ እንዲገልፁና ሌላ የሰ/ጉባኤ ተወካይ እንዲወክሉ እንዲደረግ፣
3ኛ.የሰ/ጉ/ጽ/ቤቱ በአቅራቢያው የሚገኝ የኢትዮጰያ ንግድ ባንክ ቅርጫፍ ከቆጠራ ቀናት አስቀድሞ በማሣወቅ የገንዘብ መቁጠሪያ ማሽን የያዙ ባለሙያዎች እንዲገኙ እና ቆጠራው ሲጠናቀቅ የንግድ ባንክ ሠራተኞች በሰበካ ጉባኤው ሂሳብ ቁጥር ገንዘቡን ገቢ አድርገውና ስሊፕ ሰጥተው ተረክበው እንዲወስዱ እንዲደረግ፣
4ኛ.የተሰጠውን መመሪያ አተገባበር ለመከታተል እንዲቻል የቆጠራ አፈፃፀምን የሚገልፅ ሪፖርት ገንዘቡ የገባበትን የባንክ ስሊፕ እና በገቢ የተመዘገበበትን ሞዴል 64 (ኮፒ) ቅጂ ለሀገረ ስብከቱ ሂሳብና በጀት ዋና ክፍል ገንዘቡ በተቆጠረ በ24 ሰዓታት ውስጥ የሰበካ ጉባኤው ሂሳብ ሹም እንዲያቀርቡ፣
5ኛ.በቆጣራ የተገኘው ገንዘብ በዋና ፀሐፊው፣ በአስተዳዳሪው፣ በገንዘብ ያዥ፣ በሂሳብ ሹም፣ በተቆጣጣሪ፣ በሰበካ ጉባኤ ም/ሊቀመንበሩ፣ በደብሩ (ካቴድራሉ) ቄስ ገበዝ እና በስብከተወንጌል ክፍል ኃላፊው እንዲሁም በሀገረ ስብከቱ ተወካዮች ተፈርሞ አንድ ቅጂ በመሸኛ ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት እንዲቀርብ እንዲደረግ፣
6ኛ.በቆጠራው የተከፈቱ ቋሚና ተንቀሳቃሽ የሙዳየ ምፅዋት ሣጥኖች ብዛት፣ የተገኘው ገንዘብ እና የኮሚሽን ክፍያ እና ሌሎች ቅንስናሾች በቃለ ጉባኤው በግልፅ እንዲሰፍሩ ይህም የሰበካ ጉባኤው ዋና ጸሐፊ በኃላፊነት እንዲፈፅሙ፣
7ኛ.በገንዘብ ቆጣራ የሚሣተፉ ካህናት በዕለቱ የተቆጠረውን ገንዘብ የመመዝገብ ማስታወሻ የመያዝና የመጨረሻ ድምር ውጤት የማወቅ መብት እንዲጠበቅላቸው ሆኖ አሠራሩ በግልፅነት መርህ እንዲመራ እያስገነዘብን መመሪያው ተጥሶ ቢገኝ በአስፈፃሚነት የተመደቡ ኃላፊዎችን ተጠያቂ የሚያደርግ መሆኑን በጥብቅ እናስታውቃለን፡፡
ከመንፈሳዊ ሰላምታ ጋር
ይህ ሁሉ ያለመልካም አስተዳደር የሚታሰብ አልነበረም፤ ነገር ግን አሁን በሀገረ ስብከቱ ያለው ሁኔታይህን የመሰለ መልካም ሥራ ለመስራት አመቺ በመሆኑ መልካም ጅምር ስለሆነ ለቅድስት ቤተክርስቲያን ሁለንተናዊ ሰላም እና እድገት የሚያስብ እና የሚሰራ ማንኛውም ሰው የተለየ የግል ጉዳይ ከሌላው በስተቀር ለተፈጻሚነቱ የበኩሉን አስተዋጽዖ ከማድረግ ወደኋላ እንደማይል እምነታችን ጽኑ ነው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር፡፡
{flike}{plusone}