በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሰባቱም ክፍላተ ከተሞች ሲካሄድ የነበረው የ39ኛው የሰበካ ጉባኤ ስልጠና በዛሬው ዕለት ተጠናቀቀ!!!
መጋቢት 21/2013 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ እና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ዋና ክፍል አዘጋጅነትና በሰባቱ ክፍላተ ከተሞች አስተባባሪነት በሁሉም ክፍላተ ከተሞቹ ለሰባት ቀናት ሲካሄድ የነበረው ስልጠና በዛሬው ዕለት ተጠናቋል፡፡
በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ የሚገኘውን የCovid-19 በሽታ ለመግታት የወጣውን መመሪያ መሠረት በማድረግ በክፍለ ከተማው ሥር የሚገኙ የገዳማትና አድባራት የሥራ ኃላፊዎች ብቻ በተገኙበት በነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አስተባባሪነት በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ስልጠናው ተካሂዷል፡፡
የስልጠና መርሐ ግብሩ ከተጠናቀቀ በኀላ በተደረገው ውይይትና ምክክር ስልጠናው የፈጠረው ግንዛቤና መነቃቃትና መልካም ቢሆንም ተመሳሳይ ስልጠና በተመሳሳይ ሰዎች በሁሉም ክፍላተ ከተሞች መቅረቡ አሰልች ከመሆኑም በላይ ለሌሎች ምሁራን ዕድል የነፈገ መሆኑን ገልጸው ወደፊት በሚደረገው ስልጠና ግን እንደዚህ ዓይነቱ አካሄድ እንዳይደገም የስልጠናው ተሳታፊዎች በጥብቅ አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻም የሀገረ ስብከቱ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ዋና ክፍል ኃላፊ መ/ብ ሳሙኤል ደምሴ ለተከታታይ ሰባት ቀናት የሰጠው ስልጠና ለሀገረ ስብከታችን ብሎም ለቤተ ክርስቲያናችን ስኬት ነው፡ ወደፊትም የሰጣችሁንን ገንቢ ሐሳቦች እንደግብዓት ተጠቅመን የተሻለ ነገር ይዘን እንቀርባለን ሲሉ የነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ መ/ም ዘካርያስ ሐዲስ ደግሞ የስልጠና መርሐግብሩን በማዘጋጀትም ይሁን በማሰልጠን አስተዋጽኦ ላደረጉት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡እንደ ክፍለ ከተማ ለሚደረገው ስልጠናም የተሰጠውን አስተያየት ተግባራዊ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል፡፡
ዘጋቢ መ/ር ሽፈራው እንደሻው
ፎቶ መ/ር ዋሲሁንተሾመ