በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በመልካም አስተዳደር ላይ የሥራ መመሪያ ተሰጠ

640

ታህሳስ 27 ቀን 2007 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የከንባታ ሐድያና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን ፣የሀገረ ስብከቱ ም/ሥራ አስኪያጅ መ/ር ኃይለ ማርያም አብርሃ፣ የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍልና የክፍል ኃላፊ ሠራተኞች፣ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ም/ሊቃነ መናብርት፣ ፀሐፊዎች እና ቁጥጥሮች የተገኙ ሲሆን ስብሰባው በቅዱስ ፓትርያርኩ በፀሎት ከተከፈተ በኋላ የዕለቱን አጀንዳዎች በክቡር ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን ለጉባኤው ይፋ ተደርጓል፡፡ የስብሰባው አጀንዳዎቸም ፡-
1.    ስለ መልካም አስተዳደር፣
2.    ስለ ፐርሰንት አከፋፈል፣ እና
3.    ስለ ክብረ በዓላት አከባበር በተመለከተ ነበር፡፡
ክቡር ዋና ሥራ አስከያጁ አጀንዳዎቹን በደንብ ካባራሩ በኋላ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ አጀንዳዎቹ አንድ በአንድ በማንሳት እየተመካከሩና እየተረዳዱ መልካም ሥራ መሥራት ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያገለግሉ አገልጋዮች ማለትም የጽ/ቤት እና የቤተ መቅደስ (ካህናት) መካከል ልዩነት መፈጠር የለበትም ካሉ በኋላ ቤተ ክርስቲያን ከላይ ጀምሮ እስከታች ድረስ የአሰራር ሥርዓት ስላለት ህግ እና ሥርዓትን ተከትለን ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ገዳማትና አድባራት ጥሩ ሥራ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው ነገር ግን ከዚህ በላ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ስለሚያስፈልግ ቅዱስ አባታችን በመልካም አስተዳደር ሥራ ላይ መመሪያ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ቅዱስ አባታችን በመካከላችን ተገኝተዋል ብለዋል፡፡በመቀጠልም ቅዱስ አባታችን  በአጀንዳዎቹ ላይ አባታዊ መመሪያ እንዲሰጡባቸው ጋብዘዋል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በተጠቀሱት አጀንዳዎቹ ላይ ጠቅለል ያሉ አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡ በተለይም መልካም አስተዳደርን አስመልክተው በሰጡት ሰፋ ያለ አባታዊ ማብራሪያ በቤተ ክርስቲያችን አስተዳደር ላይ የመልካም አስተዳደር ችግር ባይኖር ኖሮ ጭቅጭቅ፣ ንትርክ እና አድማ (ሰላማዊ ሰልፍ) አይኖርም ነበር ብለዋል፡፡
በመቀጠልም ፍትህ እና ርትዕ በቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር ውስጥ ሊኖር ይገባል፤ እውነት፣ ፍትህና ርትዕ ከቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ካልተገኘ ከወዴት ሊገኝ ይችላል ብለዋል፡፡ እኛ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አብነት ልንሆን ይገባል፡፡ ከቤተ ክርስቲያን የሚሰጠው የሥራ አመራር የግብረ ገብነት፤ የትህትና  እና  የዳኝነት ሊሆን ይገባዋል ፡፡ 
ቤተ ክርስቲያን በምድር ላይ የተሠራች ሰማያዊት ቤት ስለሆነች የተበላሸውን ዓለም ልናስተካክለው ይገባል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደው ይህን የተበላሸውን ዓለም ለማስተካከል እንደመጣ እኛም አሠራራችን ልናስተካክል ይገባል፡፡ ሕግ መንፈሳዊውን እና ዓለማዊውን ሁሉ ስለሚገዛ ለህግ ልንገዛ ይገባል፡፡ በተለይም ደግሞ መንፈሳውያን የሆነው ለሕገ እግዚአብሔር ልንገዛ ይገባል፡፡ አሁን አውቀንና ተረድተን ልንሠራና ልንቀሰቅስ ይገባል ብለዋል፡፡

የሙዳዬ ምፅዋት ገንዘብ አሰባሰብ በተመለከተም በህግና በሥርዓት ሊከናወን ይገባዋል ምክንያቱም ሁሉም በሥርዓት ከተከናወነ ሁሉንም ያስደስታልና  ነው፡፡ በመሆኑም በሕግ የሚከናወን ከሆነ ሰጪውንም ያስደስታል አገልጋች ካህናትም ሆነ ልዩ ልዩ ሠራተኞች በህጋዊ መንገድ ደመወዛቸው እንዲያድግ ወይም እንዲጨመረ ይረዳል፡፡ ስለዚህ የሙዳየ ምፅዋት ገንዘብ በህግና በሥርዓት ተሰብስቦ በአግባቡ ገቢ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ለዚህ ይረዳ ዘንድ ከገዳሙ /ደብሩ/ከካቴድራሉ ልዩ ልዩ ሠራተኞች በተውጣጡ ኮሚቴዎች ሥራው ሊሠራ ይገባል፡፡ በመሆኑም ከጽ/ቤት፣ ከካህናት፣ ከሰበካ ጉባኤ አባላትና ከሰንበት ት/ቤት የተውጣጡ ኮሚቴዎች የሙዳየ ምፅዋቱን የገንዘብ አሰባሰቡና አገባቡ ሊቆጣጠሩ ይገባል ብለዋል፡፡ የሚመረጡ ኮሚቴዎቹም ታማኞችና እውነተኞች ሊሆኑ ይገባቸዋል ፡፡ በዚህ ዓይነት የተሠራ ሥራ ምንም አይነት ሃሜትና አለመተማመን እንዲሁም ጭቅጭቅና ንትርክ ያርቃል ብለዋል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም መጪዎቹ ሁለቱ ዓበይት በዓላት በሰላምና በፍቅር ሃይማኖታዊነቱንና ታሪካዊነቱን መግለፅ በሚችል ሊከበር ይገባል በማለት አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

{flike}{plusone}