በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ስም በሐሰተኛ ሰነድ የተጠረጠሩ ግለሰዎች በህግ ቁጥጥር ሥር ዋሉ

640

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ስም ሕገ ወጥ ማህተም፣ የመሥሪያ ቤቱ አርማና የዋና ሥራ አስኪያጁን የስም ቲተር አስመስሎ በመሥራት በሀገረ ስብከቱ ስም በሕገ ወጥ መንገድ ሠራተኞችን የቀጠሩና የተቀጠሩ እንዲሁም በመካከል አቀባባይ የሆኑ ደላሎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ሀገረ ስብከቱም በደረሰው ጥቆማ መሠረት ለፖሊስ ባቀረበው ጥያቄ በዋና ሥራ አስኪያጁ ስምና ፊርማ እንዲሁም በሀገረ ስብከቱ ማኅተም ተመሣስሎ በተሠራ ማኅተም በመጠቀም በርካታ ሰዎችን በሀገረ ስብከቱ ሥር ባሉ ገዳማትና አድባራት በማታለል እንዲቀጠሩ ማድረጋቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በመሆኑም በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ 8 ሰዎች ፤በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ መምሪያ 1 ሰው እና በጉለሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ 4 ሰዎች በምርመራ እየተጣራ ሲሆን የሀገረ ስብከቱ የቀድሞ ዋና ክፍል ኃላፊ የነበሩ የዋና መሥራቤት ሠራተኛን ጨምሮ በገዳማትና አድባራት በልዩ ልዩ ሥራ ተመድበው የሚገኙ ሠራተኞች በደላላነት፣ በዋና ፈጻሚነትና አስፈፃሚነት እንደተሳተፉበት የደረሰው ጥቆማ የሚያስረዳ ሲሆን አንድ ሠራተኛ በተመሣሠለ ደብዳቤ ለመቅጠር ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚከፈል ለማወቅ ተችሏል፡፡
በዚህም መሠረት በቁጥጥር ሥር የዋሉ ተጠርጣሪዎች በሚሰጡት ጥቆማ መሠረት ያልተያዙ ተጠርጣሪዎች መኖራቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
የችግሩን መፈጠር ተከትሎ የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ፤የጉለሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ እና የነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የክትትልና የምርመራ ባለሙያዎች ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን በመያዝ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ እየሠሩ ያሉ መሆናቸውን የሀገረ ስብከቱ የሕግ ባለሙያዎች ገልፀዋል፡፡
የችግሩን መፈጠር ተከትሎ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ከ2007 ዓ.ም መጋቢት ወር ጀምሮ በገዳማትና አድባራት የተመደቡ ሠራተኞችን ማንነትና የቅጥር ሕጋዊነት የማጣራት ሥራ በቅርቡ እንደሚጀምር የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ገልጸዋል፡፡
ተመሳስለው የተጻፉ ደብዳቤዎችም በርካታ ሊሆኑ ስለሚችሉ ሁሉም ገዳማትና አድባራት በሠራተኛ  አቀባበልና አመዳደብ ጥንቃቄ እንዲያደርጉና ከሀገረ ስብከቱ ጋር ተናበው እንዲሠሩ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ጥብቅ መመሪያ መስጠታቸው ይታወሣል፡፡