በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ም/ሥራ አስኪያጅ ተመደበ

d0012

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ከጥቅምት ወር 2005 ዓ.ም በፊት በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ፤ በዋና ሥራ አስኪያጅና በም/ሥራ አስኪያጅ ይመራ ነበር ሆኖም ግን በጥቅምት ወር 2005 ዓ.ም ሀገረ ስብከቱ የተሻለ የሥራ አመራር ሂደትን ሊያመጣ ይችላል በማለት በ4 አህጉረ ስብከት ተከፍሎ እስከ ግንቦት 2005 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ  የዘለቀ ሲሆን ሀገረ ስብከቱ እንደገና ወደ አንድ ሀገረ ስብከት እንዲመለስ ተደርጓል፡፡
ሀገረ ስብከቱ ወደ አንድ ሀገረ ስብከት እንዲመለስ ከተደረገ በኋለም ለረዥም ጊዜ ያለ ምክትል ሥራ አስኪያጅ የቆየ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ከሥራው ውስብስነትና ሊቀ ጳጳስም ያልተመደበለት በመሆኑ ከሥራ አስኪያጁ ጋር በመነጋገር፣ በመወያየት መልካም አስተዳደርን ማስፈን ይቻል ዘንድ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት በቁጥር ል/ጻ 488/420/06 በቀን 20/10/2006 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ  የሀገረ ስብከቱ ም/ሥራ አስኪያጅ ሊሾም ችሏል፡፡
በመሆኑም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ እጅግ ሰፊ ሆኖ በመገኘቱ ቋሚ ሲኖዶስ ሰኔ 20 ቀን 2006 ዓ.ም ባሰተላለፈው ውሳኔ መሠረት መምህር ኃይለማርያም አብርሃ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሆነው እንዲሠሩ የተፈቀደላቸው ሲሆን መምህሩ በተመደቡበት የምክትል ሥራ አስኪያጅነት ተግባር ሙስናን፣ ሕጋዊ ያልሆነ ዝውውርን፣ ቅጥርና ዕድገትን በመከላከል እንዲሁም መልካም አስተዳደርን በማስፈን እንዲሠሩ ከሰኔ 20 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ ተመድበዋል፡፡
መምህር ኃይለ ማርያም አብርሃ ቀደም ሲል በርዕሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን  በድጓ መምህርነት ለብዙ ዓመታት አገልግሎት ከሰጡ በኋላ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ወደ አዲስ አበባ መጥተው በታላላቅ አድባራትና ገዳማት ከድጓ መምህርነታቸው ባሻገር በዋና ፀሐፊነት ሲያገለግሉ የቆዩና በአመራር ብስለታቸው፤ በአስተዋይነታቸውና ነገሮችን በማረጋጋታቸው የሚመሰከርላቸው ታላቅ ሰው መሆናቸው ከተለያዩ ምንጮች ያገኘናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

{flike}{plusone}