በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለሚ ኩራ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ሥር ለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የሥራ ኃላፊዎች ሥልጠና ተሰጠ

ሀገር አቀፍ ሥልጠና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለሚ ኩራ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ሥር ለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የሥራ ኃላፊዎች ሥልጠና ተሰጠ ።
በሥልጠና መርሐ ግብር ላይ መልአከ ሰላም ዶ/ር አባ ቃለ ጽድቅ ሙሉጌታ የመንበረ ፓትርያርክ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ሐላፊና የዕለቱ አሰልጣኝ፣ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫነ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የመገናኛ ብዙኃን ሒሳብና በጀት ሐላፊ፣ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ እግዚአብሔር ታደለ የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ የተገኙ ሲሆን የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት የሥራ ኃላፊዎች፣ የየአድባራቱ አስተዳዳሪዎች ፣ የሰበካ ጉባዔ ም/ሊቃነ መናብርት ፣ ዋና ጸሐፊዎች፣ ሒሳብ ሹሞች ፣ ተቆጣጣሪዎች ፣ የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊዎች የሰ/ት/ቤት ተወካዮች ተሳትፈውበታል።
የለሚ ኩራ ክ/ከተማ ዋና ሥራ አሥኪያጅ ክቡር መ/ም ቆሞስ አባ ገ/እግዚአብሔር ታደለ ለሥልጠናው የእንኳን ደህና መጣችሁና የመክፈቻ መልክት ያስተላላፉ ሲሆን ስለ ሥልጠና አስፈላጊነትም አበራርተዋል፡፡
በሥልጠናው የሰበካ ጉባኤ አደረጃጀት እና የቃለ ዓዋዲ አፈጻጸም በክቡር መ/ሰላም ቆሞስ አባ ቃለጽድቅ (ዶ/ር) እንዲሁም የሪፖርት አቀራረብ በክቡር ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫነ አማካኝነት ተሰጥቷል፡፡ በመቀጠልም ሥልጠናውን መሠረት በማድረግ ሰልጣኞች ሀሳብ አስተያየትና ጥያቄ ቀርበው በአሰልጣኞቹ ተገቢው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሥልጠናው በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መመሪያ ሰጪነት በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ተዘጋጅቶ በሁሉም ክፍላተ ከተሞች መሰጠቱ መዋቅራዊ አንድነቱን ከማጠናከሩ ባሻገር ተናቦና በእኩል የመረዳት ዓላማ መሠረትነት ሕያውን አገልግሎት ለማከናወን በእጅጉ ጠቃሚና አስፈላጊ ነው በማለት ገልጸዋል፡፡
አክለውም በዚህ ዘመን ዘመኑን የዋጀ ሥልጠና ያስፈልገናል ምክንያቱም ዘመኑ አዳዲስ ቴክኖሎጂ እየተፈጠሩበት ያለ ዘመን በመሆኑ እኛም ዘመኑ የፈጠረውን ቴክኖሎጅ ተጠቀምን ለሰማያዊው አገልግሎት ልንገለገልበት ይገባል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በሀገረ ስብከቱ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት እስከአሁን ድረስ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተወስነው የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ሲሠሩ የቆዩና አሁንም እየሠሩ መሆናቸው የሚያስመሠግን መሆኑን አውስተው የአድባራት የጽ/ቤት የሥራ ኃላፊዎች ራሳችሁን በትምህርት ና ሥልጠና በማሻሻል ትውልዱን የሚመጠን አገልግሎት መስጠት ይኖርባችኋል በማለት አሳስበዋል፡፡
ከክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ክቡር መምሕረት ቆሞስ አባ ገ/እግዚአብሔር ታደለን ጋር በመሆን የውስጥ የልማት ሥራዎቻችን እንዳሉ ሆነው በክፍለ ከተማው የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የውጭ ዕይታቸውን በማስፋት ከመንግሥት ቦታ በመጠየቅ በጋራ ሆነው የልማት ሥራዎችን ቢሠሩ ውጤታማ እንደሚሆኑና ከራሳቸውም አልፈዉ የገጠሪቷ ቤተ ክርስቲያንን ሊረዱ እንደሚችሉ ለሰልጣኞቹ አስገንዝበዋል፡፡
የለሚ ኩራ ክ/ከ/ቤ/ጽ/ቤት ዋና ሥራ አሰኪያጅ ክቡር መ/ም ቆሞስ አባ ገ/እግዚአብሔር ታደለ በበኩላቸው የዛሬው ሥልጠና እጅግ የሚያስደስት፣ ዘመኑን የዋጀ ፣ እኛን ኃላፊዎችን የሚያበረታታና የሚያነቃቃ ኃላፊነታችንንም በተገቢው ሁኔታ እንድንፈጽም የሚያበቃ ሥልጠና መሆኑን ተረድተናል ብለዋል፡፡ ስለዚህ ሁላችንም የተሰጠንን ኃላፊነት በተገቢው ሁኔታ በመፈጸም ሥልጠናውን ተግባራዊ ማድረግ ይገባናል በማለት አሳስበዋል፡፡