በአዲሱ የሀገረ ስብከቱ መዋቅርዊ የአሠራር ለውጥ እና አደረጃጀት ላይ የተለያዩ ጋዜጮችና ማህበራዊ ሚዲያዎች በመዘገብ ላይ ናቸው

pp002

አዲስ አድማስ፣ኢትዮ-ምኅዳር፣ ሰንደቅ ፣ DireTube እና የመሳሰሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች የዘገቡትን እንደሚከተለው ጠቅለል አድርገን ለማቅረብ እንሞክራለን::
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማት፣ አድባራት እና አብያተ ክርስቲያናት ያሉበትን ኹኔታ ተገንዝበው አገልግሎታቸውን የበለጠ በማስፋፋት ወደተሻለ የአገልግሎት ዕድገት የሚሄዱበትን አቅጣጫ ያመላክታል የተባለ የደረጃ መስፈርት ጥናት ረቂቅ ተዘጋጀ፡፡
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የገዳማት፣ አድባራትና አብያተ ክርስቲያናት ደረጃ መስፈርት ሰነዱ÷ በሀገረ ስብከቱ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋሞች ሥር የሰደደውን የመልካም አስተዳደር፣ የፋይናንስ አያያዝና የሰው ኃይል አመዳደብ ችግሮች በወሳኝ መልኩ ለመቅረፍ በቤተ ክርስቲያኒቱ ባለሞያዎች የተካሄደው የአደረጃጀትና አሠራር ጥናት አካል መኾኑ ተገልጧል፡፡
አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ከሚሰጧቸው አገልግሎቶች ጋራ በዕውቀት፣ በክህሎት፣ በሞያና ልምድ የተመጣጠነ የሰው ኃይል ቁጥር የማስገኘት፣ ከአገልግሎቱ ጋራ የተመጣጠነ የአገልጋዮች ክፍያ ሥርዐት የመዘርጋት፣ ከምእመኑ ፍላጎት ጋራ የተመጣጠነ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ስልት የመቀየስና በአጠቃላይም የቤተ ክርስቲያኒቱ ዋናና መሠረታዊ ተልእኮ ከኾነው የስብከተ ወንጌልና ክህነታዊ ተግባራት አንጻር አገልግሎቷን የመምራትና ወደሚፈለገው ደረጃ ከፍ የማድረግ ዓላማ እንዳለው ተጠቅሷል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የደረጃ መስፈርቱ÷ ተዋረዳዊና ጎንዮሻዊ የሞያ ልህቀት ፍኖት/ሰዋስው (career path) ባለውና ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እስከ ሀ/ስብከት በሚዘልቀው መዋቅራዊ አደረጃጀት፣ የሥራ መደብና የሥራ መዘርዝር መሠረት ራሳቸውን በመንፈሳዊ ቅንዓትና በፍትሐዊነት ላይ በተመረኮዘ የመወዳደር ብቃት የሚያሻሽሉበት ኹኔታ ለመፍጠር እንደሚያስችልም ተዘግቧል፡፡
የምዘና መስፈርትና ደረጃ ጥናት ረቂቁ ገዳማቱን፣ አድባራቱንና አብያተ ክርስቲያናቱን በአምስት ደረጃዎች የከፋፈለ ሲኾን አራት ዐበይትና ከሠላሳ በላይ ንኡሳን የምዘና መስፈርቶች ተለይተውበታል፡፡ በዋናነት ለተቀመጡት መስፈርቶች የተሰጣቸው አጠቃላይ ክብደት በሥራቸው ለተካተቱት ንኡሳን መስፈርቶች ተከፋፍሎ በመጨረሻ ከመቶ የሚገኘው ጠቅላላ ድምር ውጤት የአብያተ ክርስቲያናቱን ደረጃ እንደሚወስን ተመልክቷል፡፡
በዚህም መሠረት በቤተ ክርስቲያኒቱ÷ ቅዳሴ፣ ሰዓታትና ጸሎት በዘወትር፣ በሳምንትና በበዓላት የሚፈጸምበት ጊዜ፣ የአብነት ትምህርት ጉባኤያትና የተማሪዎች ብዛት፣ ስብከተ ወንጌል የሚሰጥበት ጊዜ፣ የሰንበት ት/ቤት አገልግሎት ኹኔታ፣ በሙዝየም፣ በጠበልና በቀብር አገልግሎት እየሰጠች ያለችው መንፈሳዊ አገልግሎት 30 ነጥብ ተሰጥቶታል፡፡
ከሙዳየ ምጽዋት፣ ከልማትና ከአገልግሎት የሚገኘው የገቢ ኹኔታ 27 ነጥብ፣ በትምህርት ቤቶች፣ በሙዓለ ሕፃናት፣ በጤናና በአረጋውያን መጦርያ የልማት ተቋማትና የምግባረ ሠናይ ሥራዎች 23 ነጥብ፣ በአጥቢያው በሰበካ ጉባኤ የተመዘገቡ ምእመናንን ብዛት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ይዞታ ሕጋዊነት፣ ስፋትና የምሥረታ ዘመን ያካተተው ሌሎች ሀብታትና ታሪክ መስፈርት 20 ነጥብ ክብደት እንደተሰጣቸው በጥናቱ ተብራርቷል፡፡
በዚህም መሠረት ከ85 – 100 ያሉት አብያተ ክርስቲያናት ደረጃ አንድ፣ ከ70 – 84.99 ያሉት ደረጃ ሁለት፣ ከ55 – 69.99 ያሉት ደረጃ ሦስት፣ ከ40 – 54.99 ያሉት ደረጃ አራት ሲባሉ ከተተከሉ እስከ ሁለት ዓመትና ከዚያም በታች የኾኑ አዲስ አጥብያ አብያተ ክርስቲያናት ለብቻቸው በአምስተኛ ደረጃ ላይ ተለይተዋል፡፡

በየደረጃ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት የተለያየ መዋቅር፣ የተለያየ የሰው ኃይል ምደባ/በቁጥርና በሞያ/ እንዲሁም የደመወዝ ስኬል የሚኖራቸው ሲኾን ይህም በየሁለት ዓመቱ በሚካሄድ ክለሳና አብያተ ክርስቲያናቱ ዐቅደው በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት ዕድገታቸው በቀጣይ የምዘና መስፈርት እየተረጋገጠ እንደሚሻሻል ከቀረበው ጥናት ለመረዳት ተችሏል፡፡
እንደየሥራው ስፋት የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል ተፈላጊውን የትምህርት፣ የሥራ ልምድና የክሂሎት ዝግጅት ባገናዘበ አኳኋን ለየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ በሚሠራው የሰው ኃይል ትመና ሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም የሚያስችላቸው የክፍያ ሥርዐት ተዘርግቷል፡፡  በሀ/ስብከቱ የሚገኙ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ትኩረት አግኝተው ተተኪዎችን ማፍራት ይችሉ ዘንድ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡
በሰው ኃይል ትመናው ገዳማቱና አድባራቱ ካላቸው መንፈሳዊ አገልግሎትና የልማት እንቅስቃሴ አንጻር የሚበቃቸው ያህል አገልጋይ ያገኛሉ፡፡ ቀሪው የሰው ኃይል በፋይናንስ ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያው እንዲሁም በልማት ሥራዎችና ምግባረ ሠናይ ተግባራት ፖሊሲና መመሪያው መሠረት÷ አብያተ ክርስቲያኒቱ ዓመታዊ በጀታቸውን ከመጠባበቂያቸው ጋራ ከያዙ በኋላ ቀሪ ከኾነው ገንዘብ ከሚመድቡት 60 በመቶ የልማት ፈንድ በሚከፍቷቸው የልማት ተቋማት የተለያዩ የክህሎት ሥልጠናዎችን በመስጠት የሚሠማራበት ሥርዐት እንደሚኖር ታውቋል፡፡
ከዚህም አኳያ ከፍተኛ የሰው ኃይል ክምችት በየአጥቢያው መኖሩ እሙን ቢኾንም አጥቢያዎች በልማት በየጊዜው ከሚፈጥሩት አቅምና በዚህም በሚስፋፉት የአገልግሎትና ምርት ተቋማት በሒደት የሚደላደል እንጂ የሚፈናቀል አገልጋይ እንደማይኖር ተገልጦአል፡፡

c003

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን÷ ከአድልዎና ሙስና የጸዳ፣ ሥርዐተ እምነትዋን የሚጠብቅ፣ መንፈሳዊ ዕሴቶችዋን የሚያንጸባርቅ፣ ሞያዊ ብቃትን ማዕከል ያደረገ፣ ዘመኑን የዋጀና የተቀላጠፈ አሠራር እንዲኖራት ያስችላል የተባለ ሁለገብ የማሠልጠኛ ማዕከል ለመገንባት የፕሮጀክት ጥናቱን አጠናቅቃ ማዘጋጀቷ ተገልጿል፡፡
በአዲስ አበባ ዙሪያ ካሉት የኦሮሚያ ወረዳዎች በአንዱ ለመገንባት ጥናቱ ተጠናቅቆ እንደቀረበ ለተገለጸውና ብር 292,260,281 ያህል በጀት የተያዘለት ለዚህ ሁለገብ የሥልጠና ማዕከል ግንባታ ፕሮጀክት ተፈጻሚነት፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጋራ መነጋገራቸውንም የሀ/ስብከቱ ምንጮች ለኢትዮ ምኅዳር ዝግጅት ክፍል አስታውቀዋል፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ ባለሞያዎች ተጠንቶ ሰሞኑን ለውይይት የቀረበው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የመዋቅር፣ የአደረጃጀትና የአሠራር ጥናት ሰነድ ረቂቅ አካል የኾነው ሁለገብ የማሠልጠኛ ማእከል ፕሮጀክቱ÷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀድሞ የነበራትን መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦ አጠናክራ ለመቀጠል ትችል ዘንድ ዘመኑን የዋጀና የተቀላጠፈ አሠራር እንዲኖራት የማድረግ አጠቃላይ ዓላማ ይዞ የተነሣ ነው፡፡
ለጥናቱ በተደረገው የኹኔታዎች ዳሰሳ÷ ስብከተ ወንጌልንና ትምህርተ ወንጌልን ከማጠናከርና ከማስፋፋት ይልቅ በደጋፊ ተግባራት ላይ ማተኮር፣ የአገልጋዮች የሥራ ትጋት መቀነስና ተነሣሽነት ማጣት፣ ምእመናን ሓላፊነት ለመውሰድ ያለመቻል፣ የቤተ ክርስቲያን ችግር በዓለማዊ ፍ/ቤት መታየቱ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ክብረ ነክና የአገልግሎት ጊዜን አባክኗል ተብሏል፡፡

በዳሰሳው ግኝቶች÷ ጥፋተኞች ያለአንዳች ተጠያቂነት በሹመትና በዝውውር መታለፍ፣ በሰበካ ጉባኤያትና በአስተዳደር ሠራተኞች፣ በካህናትና ምእመናን መካከል አለመግባባቶች መፈጠር የመሳሰሉ የመዋቅር፣ አደረጃጀትና አሠራር እንዲሁም ሥነ ምግባራዊ ችግሮች፤ የቅጥር፣ ዝውውር፣ ሹመት፣ ዕድገትና ጥቅማጥቅም ጋራ የተገናኙ የሰው ኃይል አስተዳደር ችግሮች መኖራቸው ታውቋል፡፡
ከፋይናንስና ቁጥጥር ድክመቶች ጋራ በተያያዙ ብልሹ አሠራሮች ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረት አላግባብ መባከናቸው በዋናነት የተለዩ ሲኾኑ ችግሮቹን÷ የጥናቱ አካል በኾነውና የቤተ ክርስቲያኒቱን ዕሴቶች ያንጸባርቃል በተባለው የአገልጋዮች ማስተዳደርያ ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ ከመፍታት ባሻገር በሥልጠናና የሰው ሀብት ልማት ፖሊሲውና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያው መሠረት በአገልጋዮች አመለካከት፣ ክህሎትና ዕውቀት ላይ አተኩሮ በሚሠራበት የሁለገብ ማዕከሉ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎችም ለመቅረፍ መታሰቡ ተመልክቷል፡፡
በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ምእመናንና በብዙ መቶ ሺሕ የሚታሰቡ ካህናት ያሏት ቤተ ክርስቲያኒቱ፣ ዘመኑን የዋጀና ሁለ አቀፍ የኾነ የሥልጠና ማዕከል በመገንባት በመንፈሳዊና ማኅበራዊ ተቋሞቿ መልካም አስተዳደርን፣ ምቹና ቀልጣፋ አሠራርን ማስፈኗ ለአገር ዕድገትና ልማት እጅግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት በፕሮጀክቱ ዝርዝር ዓላማዎች ላይ ተገልጧል፡፡
ፕሮጀክቱ የሥልጠና ማዕከል ብቻ ሳይኾን ወላጆቻቸውን በኤች.አይ.ቪ እና በተለያየ ምክንያት ያጡ ጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናትን በማሰባሰብ ተንከባክቦ በሥነ ምግባር የማሳደግ፣ ከቀለም ትምህርታቸው ጎን ሞያዊ ክሂሎታቸውን በማዳበር ራሳቸውን ችለው ሥራ ፈጣሪ እንዲኾኑ በማስቻል ብቁ ዜጋ የማድረግ፤ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን አረጋውያንና አካል ጉዳተኞችን በማሰባሰብ ኑሯቸውን የማሻሻል ዝርዝር ዓላማዎች እንዳሉትም ተዘግቧል፡፡
እንደዚሁም በሀገረ ስብከቱ ሥር ያሉ  ገዳማትና  አድባራት የካሽ ሬጅስተር ማሽንን ለገቢ መሰብሰቢያነት ለመጠቀም የሚያስችላቸው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑ ተገልጿል፡፡
ዘመኑን ያልዋጀውንና ጥራት የጎደለውን፣ ለሙስናና ብክነት የተጋለጠውን የቤተ ክርስቲያኒቱን የፋይናንስ አሠራርና ቁጥጥር ችግር ግልጽነት፣ ወጥነት፣ ተቀባይነትና ተጠያቂነት ባለው የፋይናንስ አያያዝ ሥርዐት ለመቅረፍና ለማድረቅ ያስችላል፤ በሚል በቀረበው የሀገረ ስብከቱ የሒሳብ አያያዝ ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ ረቂቅ ላይ እንደተጠቀሰው÷ በማንኛውም መንገድ የተሰበሰበ ገቢ ገንዘብ ሕጋዊ የገቢ መሰብሰቢያ ደረሰኝ ወዲያውኑ ሊቆረጥለት የሚገባ ሲኾን ይህም በዋናነት በካሽ ሬጅስትር ማሽን እንደሚከናወን ተመልክቷል፡፡
የሀ/ስብከቱ አብያተ ክርስቲያናት የካሽ ሬጅስተር ማሽን ተጠቃሚ መኾናቸው በገቢ ሒሳብ አሠራርና ቁጥጥር እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመከላከል ያስችላል፡፡ በጥናቱ ላይ በመነሻነት ከተዘረዘሩት ችግሮች ለመረዳት እንደሚቻለው በዕለት ገቢዎችና ደረሰኝ አጠቃቀም ረገድ፡- የቤተ ክርስቲያኒቱን የገንዘብ ገቢ ሰነዶች በሕገ ወጥ መንገድ አሳትሞ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም ለግል ገንዘብ ይሰበሰባል፤ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የተከለከለ ደረሰኝ ጥቅም ላይ የሚውልበት አጋጣሚ ታይቷል፤ ከደረሰኙ በበራሪው/ለከፋዩ ከሚሰጠው/ የተለየ መጠን በቀሪው ላይ መጻፍና የግል ጥቅምን ማካበት ይዘወተራል፤ በዘወትርና በክብረ በዓላት በርካታ ገንዘብ ገቢ ቢኾንም በዕለቱ ወደ ባንክ ያለማስገባት ኹኔታ አለ፤ ምእመናን ለሚከፍሉትና ለሚሰጡት ገንዘብ ከመተማመን አንጻር ደረሰኝ የመቀበል ልማድ የለሌላቸው መኾኑን እንደክፍተት በመጠቀም ለቤተ ክርስቲያን የመጣው ገንዘብ ‹‹በየመንገዱ እየተንጠባጠበ ወፎች የሚለቃቅሙት ይበዛል፤›› በሥራ ላይ ያልዋሉ የገንዘብ ገቢና ወጪ ሰነዶች (ሞዴላሞዴሎች ሴሪ ንምራ ቁጥር) መሠረታዊ ችግር ተጠንቶ መፍትሔ አልተሰጠም፡፡

በንግሥ፣ በወርኃዊ በዓላትና በዕለተ ሰንበት በሙዳየ ምጽዋት ሳይኾን በተዘረጋ ጨርቅ ላይ የሚሰበሰብ ገንዘብ መኖሩን የሚጠቅሰው ጥናቱ÷ በዚህ መልክ የተሰበሰበው ገንዘብ ሀ/ስብከቱ በታኅሣሥ፣ 2003 ዓ.ም. ባስተላለፈው የገንዘብ ቆጠራ፣ የንብረት አመዘጋገብና አጠባበቅ የሥራ መመሪያ መሠረት የምእመናንና ካህናት ሰበካ ጉባኤ ተወካዮች በሙሉ በተገኙበት ቆጠራ የማይካሄድበትና በተወሰነ መልኩም ሙሉ ገንዘቡ ገቢ የማይደረግበት ኹኔታ በመኖሩ አሠራሩ ለብኩንነት፣ ሐሜትና አሉባልታ መጋለጡን ገልጧል፡፡

c001

በንግሥ በዓላት ወቅት ጥላ ዘቅዝቀው የሚለምኑ ሰዎች ኹሉም ስለማይታወቁ የተኣማኒነት ችግር አለ፡፡ በስእለትና በሙዳየ ምጽዋት በውጭ ምንዛሬ የሚገቡ የውጭ ሀገር ገንዘቦች በመመሪያው መሠረት በዕለቱ የባንክ ምንዛሬ ወደ ብር እየተቀየሩ በተገቢው መንገድ ገቢ አለመኾናቸው፣ በምትኩ ቅያሬው ወጥነት ያለውና ለብኩንነት የተጋለጠ እንደኾነም ተዘግቧል፡፡
በቃለ ዐዋዲ ድንጋጌው የተመለከተውንና በዝርዝር የሥራ መመሪያ የተላለፈውን የገቢ አሰባሰብ በተሻለ አሠራር ያጠናክራል የተባለው በፖሊሲና መመሪያ ረቂቁ የሒሳብ ሰነዶች አያያዝ፣ ምዝገባና አወጋገድ መሠረት÷ ለሒሳብ ሥራ የሚያገለግሉ ደረሰኞችና ቫውቸሮች የዋና ተጠቃሚውን ተቋም ስም ይዘው በሀገረ ስብከቱ ምስጢራዊ ኮድ ይዘው ይታተማሉ፤ የማሳተም ሓላፊነቱም የሀገረ ስብከቱ የፋይናንስና በጀት ዋና ክፍል ሲኾን ይህም በዋና ሥራ አስኪያጁ ፈቃጅነት የሚከናወን ይኾናል፡፡
በማንኛውም መንገድ የተሰበሰበ ገቢ ሕጋዊ የገንዘብ መሰብሰቢያ ደረሰኝ ወዲያውኑ ሊቆረጥለት ይገባል፤ ይህም በዋናነት በካሽ ሬጅስተር ማሽን ተፈጻሚ ይኾናል፤ የገንዘብ መሰብሰቢያ ደረሰኝ ከገንዘብ ሰብሳቢ ውጭ መያዝና መጠቀም አይቻልም፡፡ ማንኛውም የገንዘብ ስጦታ በገንዘብ ያዡ በኩል መሰጠት ይኖርበታል፤ ስጦታው እንደተበረከተም ወዲያውኑ የገንዘብ መቀበያ ደረሰኝ ሊቆረጥለት ይገባል፡፡ በዐይነት የሚሰጥ ስጦታ በግዥ፣ ሽያጭና ንብረት አስተዳደር ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ መሠረት በተተመነለት ዋጋ ይመዘገባል፡፡
ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ውጭ በሙዳየ ምጽዋት ሣጥን ገንዘብ መሰብሰብ አይቻልም፤ ቋሚ ሙዳየ ምጽዋት በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን የሚቀመጥበት ቦታ ተጠንቶ በሰበካ ጉባኤው መጽድቅ አለበት፤ ለቆጠራ ካልኾነ በቀር ከተቀመጠበት ማንቀሳቀስ አይቻልም፤ በትከሻና ተይዘው የሚዞሩ ሙዳየ ምጽዋት ሣጥኖች ሙሉ መረጃ ተመዝግቦ ይያዛል፡፡ የሙዳየ ምጽዋት ቆጠራ በሚካሄድበት ወቅት ሣጥኖቹ ከመከፈታቸው በፊት ሁሉም ቆጣሪዎች የቁልፍ ካዝናውና የቁልፍ ሣጥኖች፣ የሣጥኖቹን ብዛትና እሽጋቸው አለመከፈቱን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፤ የተቆጠረ ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ወዲያውኑ ካልተቻለ ከሌላ ገንዘብ ጋራ ሳይቀላቀል በበነጋው ወደ ባንክ አካውንት መግባት አለበት፤ ዣንጥላን፣ ምንጣፍንና የመሳሰሉትን በመጠቀም ገንዘብ መሰብሰብ ፈጽሞ የተከለከለ ይኾናል፡፡
የሀገረ ስብከቱ የመዋቅርና አደረጃጀት ሰነድ አካል የኾነው የሒሳብ አያያዝ ፖሊሲና ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ ጥናት ረቂቅ እንደሚያትተው÷ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት፣ የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች፣ የልማትና በጎ አድራጎት ተቋማት፣ ደረጃ አንድ እና ሁለት የኾኑ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በኮምፒዩተር የታገዘ የሒሳብ አያያዝ ዘዴን/ሥርዐት እንዲከተሉ ይደረጋል፡፡ የሒሳብ አያያዝ ዘዴውም የሁለትዮሽ የሒሳብ አያያዝ ዘዴ(Double entry system) ሲኾን በአክሩዋል ቤዝስ ከሚጠቀሙት ከልማት ተቋማት በስተቀር የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና በሥሩ ያሉ ሌሎች ተቋማት በጥሬ ገንዘብ ላይ የተመሠረተ፣ ገቢንና ተከፋይን በታሳቢነት በሚያስላው የሒሳብ አያያዝ ዘዴ(Modified cash bases) እንዲከተሉ ለማድረግ መታቀዱ ተገልጦአል፡፡ በኮምፒዩተር የሚታገዘው የሒሳብ አያያዝ ሶፍትዌርም በሀገረ ስብከቱ ተመርጦ የተዘጋጀው እንደሚኾን ታውቋል፡፡
የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዕውቀትና ዘመናዊው የፋይናንስ ሞያ በጥምረት ሥራ ላይ ለሚውልበት ለዚህ አሠራር ተፈጻሚነት÷ ከሀገረ ስብከቱ፣ ከክፍለ ከተማ ጽ/ቤቶችና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ተመርጠው ለተውጣጡና ለሚመለከታቸው የሒሳብና የቁጥጥር ሓላፊዎችና ሠራተኞች ሥልጠና እንደሚሰጥ የተጠቆመ ሲኾን የሀገረ ስብከቱ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ዶኩመንቴሽን ዋና ክፍል በማእከል ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠረው የመሠረተ – ቴክኖሎጂው ዝርጋታ በሚተገበርባቸው ተቋማትና አብያተ ክርስቲያናትም በግልጽ የፕሮጀክት አሠራር እንደሚፈጸም ተገልጧል፡፡
ዘመናዊው የፋይናንስ አሠራር በሀገረ ስብከቱ ተቋማትና አብያተ ክርስቲያናት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲኾንም በተጭበረበሩ ደረሰኞችና በማይታወቁ የገንዘብ አሰባሰቦች የግል ጥቅምን ማካበት በመከላከል ለክትትልና ቁጥጥር አመች ለማድረግ እንደሚያበቃ ተመልክቷል፡፡ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት፣ በልማትና በጎ አድራጎት ተቋማቱ እንዲሁም በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ የሚዘጋጁ የፋይናንስ ሪፖርቶች ግልጽነት፣ ወቅታዊነትና ተኣማኒነት/ተቀባይነት እንዲኖራቸው ለማድረግ፣ ሀገረ ስብከቱ በሚሰበሰበው የኻያ በመቶ ፈሰስና ከአብያተ ክርስቲያናቱ በቅጽ ተሞልቶ በሚላከው ሒሳብ መካከል በየዓመቱ የሚያጋጥመውን ልዩነት ለማስወገድ እንደሚያስችል ተገልጧል፡፡
ይህም በሒደት ከፍተኛ የሀብት ክምችት የሚገኝበት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በፋይናንስ አሠራሩና መልካም አስተዳደሩ የሁሉም አህጉረ ስብከት ሞዴል በመኾን ቤተ ክርስቲያኒቱ በመንበረ ፓትርያርክ ደረጃ ማእከላዊ የፋይናንስና በጀት አስተዳደር ይኖራት ዘንድ መሠረት ለመጣል፣ የካህናቷን ኑሮ በማሳደግና በማሻሻል ሐዋርያ ተልእኮዋን ለማጠናከር ከፍተኛ አቅም የምትፈጥርበት መሠረት ለመጣል እንደሚያስችላት ታምኖበታል፡፡ይህም አገሪቱ እያከናወነችው  ላለው የመሠረተ ልማት እንቅስቃሴ ሀገረ ስብከቱ ከፍተኛ የሆነ  ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

{flike}{plusone}