በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ጽ/ቤት የፍቅር ማዕድ መርሐ ግብር ተካሄደ
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ጽ/ቤት የሥራ ኃላፊዎች መጪውን የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን ጾመ ፍልሰታ ምክንያት በማድረግ የፍቅር ማዕድ መርሐ ግብር አካሄዱ።
የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሰ ፍቅር ለሰው ልጆች ከእግዚአብሔር የተሰጠ ልዩ ስጦታ መሆኑን በአጋፔ ማዕድ መርሐ ግብሩ ላይ አብራርተዋል።
አብሮ በጋራ የፍቅር ማዕድ መቋደስ መተሳሰብን፣ መረዳዳትን፣ መተዛዘንንና የአብሮነት ስሜትን ያሳድጋልም ብለዋል።
ፍቅር የቤተክርስቲያን መታወቂያዋና መገለጫዋ ስለሆነ ሁላችንም እርስ በእርስ በመዋደድና አብሮ በመብላትና በመጠጣት በመካከላችን ያለውን ፍቅር መግለጽ አለብን ሲሉ አብራርተዋል።
ፍቅር በሠራተኞች ዘንድ ለሥራ መነሣሣትን፣ ጠንክሮ መሥራትንና መነቃቃትን ይፈጥራል ብለዋል።
በሠራተኞች ዘንድ የጸሎትና ወንጌል የመማማር መርሐ ግብርም እንዳለ አውስተዋል።
ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ የጽ/ቤቱ ቢሮዎች ደሳሳ ቢሆኑም በሠራተኞች መካከል ያለው ፍቅር ግን እጅግ የሚያስደስት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በቅርብ ጊዜ ውስጥ የክፍለ ከተማውን ቤተክህነት የሚመጥን የሕንጻ ሥራ እንደሚጀምርም ጠቁመዋል።
መጪው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የጾመ ፍልሰታ ሱባኤም መልካም እንዲሆን ምኞታቸውን ገልጸዋል።
የክፍለ ከተማው ቤተክህነት የትምህርትና ማሰልጠኛ ዋና ክፍል ኃላፊ መ/ኃ አባ ተክለሃይማኖት ገ/ኢየሱስ 5000 ብር ከራሳቸው ኪስ አውጥተው የፍቅር ማዕድ መርሐ ግብሩ እንዲዘጋጅ ላደረጉት አስተዋጽኦ ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ አድንቀዋል።
የክፍለ ከተማው ሠራተኞች በዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሰ አመራር ደስተኛ እንደሆኑ ጠቅሰዋል።
ከዚህ በፊት በሳምንት ውስጥ ጥቂት ጊዜ ብቻ ለሥራ እንደሚገቡ ጠቅሰው ነገር ግን በአሁን ጊዜ በሳምንቱ የሥራ ቀናት በሙሉ እንደሚገቡና ሥራቸውንም በፍቅር እንደሚሠሩ አውስተዋል።
ዘጋቢ፦ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ
ፎቶ ፦መ/ር ዋሲሁን ተሾመ