በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ስብከተ ወንጌልን በተመለከተ ሥልጠና እየተሰጠ ይገኛል!!!
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የክፍለ ከተማው አስተዳዳሪዎች፣ ሰባክያነ ወንጌልና የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች ስብከተ ወንጌልን አስመልክቶ እየተሰጠ ያለውን ሥልጠና እየተከታተሉ ይገኛሉ።
ሰልጣኞቹ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን ጨምሮ ክቡር ሊቀ ጉባኤ አባ ተክለሃይማኖት ወልዱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ ዋና ክፍል ኃላፊ፣ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊ/ኅሩያን ዳዊት ታደሰና የክፍለ ከተማው ጽ/ቤት አገልጋዮች በተገኙበት በክፍለ ከተማው ጽ/ቤት አዳራሽ ሥልጠናውን እየተከታተሉ ይገኛሉ ።
በሥልጠናው የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር ሊ/ኅሩያን ዳዊት ታደሰ የእንኳን ደህና መጣችሁ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል።
የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስኪያጅ ሥልጠናው “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው…”(ማቴ.28፥19) በሚል ጌታችን ለቤተ ክርስቲያን የሰጣት ቁልፍ ቃል መነሻነት የተዘጋጀ መሆኑን በመግለጽ የቤተ ክርስቲያን የጀርባ አጥንት የሆነው ስብከተ ወንጌልን ለመተግበር የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።
ክቡር ሊቀ ጉባኤ አባ ተክለሃይማኖት ወልዱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ካህናቲከ ይለብሱ ጽድቀ፣ ወጻድቃኒከ ትፍሥኅተ ይትፌስሑ…፤ ካህናቶችህ ጽድቅን ይልበሱ፥ ቅዱሳንህም ደስ ይበላቸው። (መዝ. 131፥9) ብሎ ቅዱስ ቃሉ እንዳስተማረን ካህናት አገልጋዮች እውነትን ይዛችሁ፣ ጽድቅን ለብሳችሁ እውነተኞችን የምታስከትሉ፣ ጽድቅን ለብሳችሁ ጽድቅን የምታለብሱ፣ ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን በማብሰር፣ የጽድቅ መንገድን በማሳየት ለመንግሥተ ሰመያት የምታዘጋጁ እናንተ ስለሆናችሁ ደስ እያላችሁ ሥልጠናውን በአግባቡ ልትጠቀሙበት ይገባል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ሥልጠናው ላዘጋጀ ለክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ጽ/ቤትም አመስግነዋል።
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴ. 28:19-20) የሚል የቤተ ክርስቲያን ትእዛዝ ለመፈጸም ምእመናን የሚያስተምሩ የሚያበቁ ሰባክያነ ወንጌል መምህራን ዕውቀታቸው እንዲሰፋ፣ በሚገባ ተዘጋጅተው ወንጌልን እንዲያስተምሩ የሚረዳ ሥልጠና መሆኑን ገልጸዋል።
ብፁዕነታቸው የክርስትና ማዕከሉ የምስራች ብሎ ወንጌልን መስበክ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ማወቅና ማሳወቅ፣ እንዲሁም የዲያብሎስን ሥራ ማፍረስ መሆኑን ተናግረዋል።
እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን ሥራ ወንጌልን መስበክና ማስፋፋት እንዲሁም መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ፣ ለመንግሥቱ ተዘጋጁ በማለት የሰው ልጅ ሁሉ ለመንግሥቱ የተዘጋጁ እንዲሆኑ ማድረግ መሆኑን አብራርተው አስተምረዋል።
ብፁዕነታቸው ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ “ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፤ እናንተ ደግሞ ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተ ደግሞ እናወራላችኋለን። ኅብረታችንም ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው” (1ዮሐ. 1፥1-3)። አንዳለው የቤተ ክርስቲያን ዋነኛው ተልእኮ የሰው ልጅ ሁሉ ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ኅብረት እንዲነሮውና መንግሥቱ እንዲወርስ ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ሁሉ ደግሞ በስማበለውና በልማዳዊ ባህል ሳይሆን በደንብ በመዘጋጀት መሆን ስላለበት የዛሬው ሥልጠና ለዚህ ዝግጅት በብዙ መልኩ እንደሚረዳ ገልጸዋል።
ለወጤታማ የወንጌል አገልግሎትም ሰባኪ፣ ተሰባኪና ስብከቱ በሚገባ መስማማት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ሰባኪ፦ ቃሉን ያወቀና በቃሉ በመኖር ራሱን ለወንጌል አገለግሎት ያዘጋጀ፤ ተሰባኪ፦ ቃሉን ለመስማት የተዘጋጀ ልብ ያለው፤ ስብከቱ፦ የምእመናንን መንፈሳዊ ሕይወትን የሚለውጥ፣ የሚያፋቅር፣ ለመንግሥቱ እንዲዘጋጁ የሚያደርግ እውነትና በእውነት የተመሠረተ ስብከት ሲሆን መሆኑን አብራርተው አስተምረዋል።
መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ ዋና ክፍል ኃላፊም ዕድሉን ላገኙት ሠልጣኞች እንኳን ደስ ያላችሁ በማለት “ወንጌልንም ባልሰብክ ወዮልኝ።” (1ቆሮ. 9:16) እንዳለው ቅዱስ ጳውሎስ ያ ወዮታ ለእኛም እንዳይደርሰን ወንጌልን ለመስበክና ለማስፋፋት የተዘጋጀ ሥልጠና መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ በመቀጠልም “የወንጌል አገልግሎትና የወራዙት ሥነ ምግባር ተኮር ለውጥ” የሚል ዳሰሳዊ ጽሑፍ/ጥናታዊ ጽሑፍ የምስካበ ቅዱሳን አባ ኪሮስ ሰባኬ ወንጌል በሆኑት በመ/ሰናያት ዓቢይ መኮንን ቀርቧል።
በጥናታዊ ጽሑፉ ወንጌል ለፍጥረትቱ ሁሉ/ ለሰው ልጆች ሁሉ እንዲሰበክ ከጌታ የተሰጠ የእግዚአብሔር መልእክት መሆኑን በመግለጽ ወንጌል በዕድሜ ክልል ሳይገደብ የሁሉም እንቆቅልሽ የሚፈታ ዋነኛ የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ መሆኑን ተገልጿል።
ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን ለሁሉሞ ሰው በአግባቡ ማዳረስ እንዳለባት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ባይሆንም የዘመኑ ቴክኖሎጂና ፍልስፍና ተጽዕኖ ግምት ውስጥ በማስገባት ወጣቶች በወንጌል ማብቃት እንዳለባት ተገልጿል።
በቀረበው ሥልጠና ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎ ከሠልጣኞች የችግሮቹ መንስኤ ከነመፍትሔው ተዘርዝሮ ቀርቧል።
በመጨረሻም “ወጣቶችን በማብቃትና ችግሮችን በመሠረታዊነት ከመፍታት አንጻር የሰባክያነ ወንጌል ድርሻ” በሚል ርዕስ የችግሮቹ መንስኤዎችና ለችግሮቹ መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ ዘመኑን የዋጁ መሠረታዊ ሓሳቦችን ቀርቧል።
ከሰዓት በፊት የነበረ የሥልጠናው መርሐ ግብርም በዚህ ተጠናቋል።
በመ/ር ኪደ ዜናዊ
ፎቶ በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ