በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥር በሚገኘው በደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የአዲሰ አበባ እና የጉራጌ አህጉር ስብከት ሊቀ ጳጳሰ ብፁእ አቡነ መልከጼዴቅ የተጠናቀቁ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ

በጉብኝቱም ወቅት የሀገረ ስብከቱ የሕዝብ ግንኝነት ኃላፊ ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ታደሰ፣ የክፍለ ከተማው ቤተ ከህነት ዋና ሥራአሰኪያጅ መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃን፣ የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ አሚን ለይኩን አበጀ እና የደብሩ የሰበካ ጉባኤ አባላት፡ የደብሩ አገልጋይ ካህናት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ታህሣስ 10 /2013 ዓ/ም የሥራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡

የደብሩ አሰተዳደሪ መልአከ አሚን ለይኩን አበጀ “የደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሰ/ጉ/ጽ/ቤት እና ማኅበረ-ካህናቱ ለልማት ባላቸው ከፍተኛ ተነሳሽነት በዛሬ ዕለት የጎበኛችሁትን ለማኅበራዊ እና መንፈሳዊ አገልግሎት የሚውልና ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚሰጠውን የልማት ሥራ ለማጠናቀቅ ተችሏል ብለዋል፡፡

አያይዘውም ደብሩ ከዚህ በፊት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ነበሩበት ፣በአሁን ስአት ግን በደብሩ ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት አባላት፣ በአስተዳደር ሠራተኞች፣ በደብሩ ማኅበረ ካህናት እና በሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች እንዲሁም በአካባቢው ምዕመናን ቀና አንድነታዊ ትብብር ሰፊ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በመሰጠቱ የነበረው ችግር ተወግዶ በተሻለ የልማት እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል::

በመጨረሻም በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት በፁዕነታቸው በተመለከቱት ዘርፈ ብዙ ልማት መደሰታቸውን በመግለፅ ቤተ-ክርስቲያን በወንጌል የሰውን አእምሮ ማልማት ከቻለች ቁሳዊ ልማት በራሱ ጊዜ ይመጣል ብለዋል፡፡

ቀጥለውም ለዚህ ለጎበኘነው የደብሩ ልማት ገንዘባችሁን፣ ዕውቀታችሁን እንዲሁም ጊዜያችሁን እና ጸሎታችሁን በማስተባበር ትልቁን ድርሻ የተወጣችሁት የደብሩ የሰበካ ጉባኤ አባላት፣ የአስተዳደር ሠራተኞች፣ የደብሩ ማኅበረ ካህናት እና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች እንዲሁም የአካባቢው ምዕመናን ልትመሰገኑ ይገባል ብለዋል፡፡

በቀጣይ ጊዜም የጀመራችሁትን ይህንን በጎ ሥራ ቀጥሉበት፣ ልትሰሯቸው ካቀዳችኀቸው ዕቅዶች መካከል ግን ለስብከት ወንጌል መስፋፋት ትልቁን በጀት፣ ጊዜ እና ትኩረት ትሰጡ ዘንድ በጥብቅ አሳስባለሁ በማለት አባታዊ መመሪያ አሰተላልፈዋል፡፡

አዘጋጅ፦ መ/ር ደምስ አየለ
አርታኢ፦ መ/ር ሽፈራው እንደሻው
ፎቶ፡-መ/ር ዋሲሁን ተሾመ