በቦሌና ለሚኩራ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥር በአራብሳ አካባቢ የሚገኙ ፲፭ አድባራት የባሕረ ጥምቀት ቦታ በተመለከተ ያሏቸውን አቤቱታዎች ለሀገረ ስብከቱ አቀረቡ
በቦሌና ለሚኩራ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥር የሚገኙ ፲፭ አድባራት የባሕረ ጥምቀት ቦታ በተመለከተ ያሏቸውን አቤቱታዎች ለሀገረ ስብከቱ አቀረቡ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና ትውፊት መሠረት በዐደባባይ ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ የጥምቀት በዓል ነው።
የበዓሉ አከባበር ሥርዓት ታቦታቱን ከቤተ ክርስቲያን ወደ ተከተረ ባሕረ ጥምቀት ቦታ በመውሰድ በልዩ ሥርዓትና ድምቀት ይከበራል ።
ይሁንና የባሕረ ጥምተቀ ቦታ ይዞታ ሕጋዊነትና በመቋሚነት ከማክበር አኳያ በተለያዩ ቦታዎች በየዓመቱ ችግሮች እንደሚከሰቱ ይታወቃል።
በዚሁ መነሻነት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በቦሌና ለሚኮራ ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሥር በአራብሳ አካባቢ የሚገኙ ፲፭ አብያተ ክርስቲያናት የጥምቀት ማክበሪያ ቦታ ጉዳይ ላይ በየዓመቱ እያጋጠማቸው ያሉትን ችግሮች በትናትናው ዕለት በነበረው ውይይት ለሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቅርበዋል።
በውይይት መርሐ ግብር የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፤ የሀገረ ስብከቱ የዕቅድና ልማት ዋና ክፍል ሐላፊ መምህር ኃይሉ ጸጋው ፣ የቦሌና ለሚኩራ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃን ፣የአድባራቱ አስተዳዳሪዎችና የሥራ ሐላፊዎች ተገኝተውበታል።
የውይይቱ መነሻ
1. የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ቦታዎች በየዓመቱ እርግጠኛ ካለመሆን አልፎ የዘርፈ ብዙ ችግሮች መንስኢዎች መሆናቸውን ፤
2.የጥምቀት በዓልን ስናከብርባቸው የነበሩ የባሕረ ጥምቀት ቦታዎች ከአድባራቱ ተነጥቀው ለሌሎች አብያተ እምነት ተላልፈው መሰጠታቸው፤
3.በዓመታት ስናከብርባቸው ለነበሩ ቦታዎችን ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫን አለማግኘት እንዲሁም
4.በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ በየዓመቱ በዓሉ የሚከብርባቸው ጊዜያዊ ቦታዎች በተለያዩ ምክንያቶች መለዋወጥና የዘላቂነት ችግር ተግዳሮቶች ማጋጠማቸውን በዝርዝር አቅርበዋል።
የአድባራቱ አስዳዳሪዎች የባሕረ ጥምቀት ቦታዎችን ከጊዜዊነት ወደ ዘለቄታዊነት በማስከበሩ ረገድ የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃን ድርሻቸውን እንደተወጡም አክለው ገልጸዋል።
ሥራ አስኪያጁም አድባራቱ ባሕረ ጥምቀት ቦታዎች ጉዳይ ላይ እያከናወኑት ያሉትን መልካም ተግባር በእጅጉ አድንቀው መንግሥት ለሚቀርቡለት ጥያቄዎች አፋጣኝ መልስ እየሰጠ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
አክለውም በቀጣይ ከሀገረ ስብከቱ ጀምሮ የመንግሥት አካላትን በመነጋገር መፍትሒ እንዲያገኝ እንደሚሠሩም ተናግዋል።
ከዚሁ ጋር በየአድባራቱ የሚመጡትን ጥያቄዎች አግባብነታቸውን በመከተል ለሚመለከታቸው አካላት ደብዳቤ መጻፋቸውን የሀገረ ስብከቱ የዕቅድና ልማት ዋና ክፍል ሐላፊ መምህር ኃይሉ ጸጋው አስረድተዋል።
በመሆኑም የችግሩ ግዝፈትና ተዘውታሪነት ምክንያት ጥያቄውን መፍትሒ እንዲያገኝ ለማድረግ ይቻል ዘንድ በሀገረ ስብከቱ በኩል ከፍተኛ ክትትልና ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልገው በውይይቱ ተጠቁሟል።
የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ በበኩላቸው በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ የጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎችን በጊዜያዊነት መገልገሉ እንዳለ ሆኖ ሕጋዊ ይዞታ እንዲኖራቸው ከፍተኛ ጥረቶችን እያደረጉ ለሚገኙ የክፍለ ከተማዎ የሥራ ሐላፊዎችና የአድባራቱ አስተዳዳሪዎችና ሠራተኞች ምስጋና አቅርበዋል።
ዋና ሥራ አስኪያጁ አክለውም የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ቦታዎችን በተመለከተ የሚነሱ ችግሮች በርካታ መሆናቸውን አስታውሰው ከይዞታ ጋር የተያያዘውን ጥያቄ በዘለቂታዊ መልኩ ለመፍታት ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በየጊዜው ውይይት እንደሚደረጉም አስተውሰዋል።
በቀጣይም በተነሱ ዋና ዋና ጥያቄዎች መነሻነት ሀገረ ስብከቱ ጉዳዩን በጥብቅ ከመከታታል ባለፈ ለተፈጻሚነቱ በቁርጠኝነት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሠራም አብራርተዋል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከከተማ አስተዳዳሩ ጋር ሀገር ጠቀም በሆኑ ቤተ ክርስቲያንና የጋራ ጉዳዮች ላይ በቅርበትና በትብብር እየሠራ እንደሚገኝ ተቁመው በቀጣይም የአቤቱታ የቀረበበትን ባሕረ ጥምቀት ቦታዎች ጉዳይ በተመለከተም ከከተማ አስተዳዳሩ ጀምሮ ባሉ የተዋረድ መዋቅሮች ጋር በመነጋገር መፍትሔ ለማሰጠት እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
በመጨረሻም ለዐደባባይ በዓላት በክብርት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የሚመራው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በገንዘብ በመደገፍ ጭምር ለቅድስት ቤተ ክርስቲያንና ለአማኙ ህዝበ ክርስቲያን ያለውን አክብሮት በየዓመቱ በተግባር እየገለፀ መምጣቱን ዋና ሥራ አሥኪያጁ ገልፀው ከፊታችን የሚጠብቁንን የጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎችንና የአምልኮ ሥፍራ ጥያቄአችንን በውይይትና በትብብር መንፈስ እንደሚፈታ ለአቤቱታ አቅራቢዎች አብራርተዋል።
©የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ