በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የተመራው ልዑክ የጉራጌ ሀገረ ስብከትን የልማት ሥራዎች በመጎብኘት ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡
በአዲስ አበባና በጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የተመራና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን ያካተት ልዑክ በጉራጌ ሀገረ ስብከት በአጭር ጊዜ ተሠርተው የተጠናቀቁትን እና በመጠናቀቅ ላይ ያሉትን የልማት ሥራዎችና በቴክኖሎጅ ዘርፍ እየተሠሩ የሚገኙትን የማስፋፊያ ሥራዎችመጎብኘታቸው
ተገልጿል፡፡
ብፁዕነታቸው በሀገረስብከታቸው ከሚያደርጉት
ሐዋርያዊ አገልግሎት፡ አባታዊ አመራርና ቡራኬ ባሻገር በመንበረ ጵጵስናቸው ግቢ ውስጥ በርካታ የልማት ሥራዎችን ማሰራታቸውን የሀገረ ስብከቱ መረጃ ያመላክታል፡፡
ሀገረ ስብከቱን ከዘመኑ ጋር ለማራመድ የሚያበቃ የቴክኖሎጅ ሥራ እና በርካታ ደቀ መዛሙርትን የሚያስተናግድ አዳሪ ትምህርት ቤት እንዲሁም የአካባቢውን ማኅበረሰብ የቤት አሠራር ባሕል ጠብቆ የተሠራ የስብሰባ አዳራሽና በመሠራት ላይ የሚገኝ G+5 የጽ/ቤቱ ሕንጻ ከልማት ሥራዎቹ መካከል ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ በጉብኝቱ ወቅት ለመገንዘብ ተችሏል፡፡
በብፁዕነታቸው አመራር ሰጭነት በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ከፍተኛ ትኩረት ተስጥቶበት እና ብዙ ገንዘብ ወጥቶበት በበጀት ዓመቱ የተጠናቀቀው G+1 ሕንጻ አዳሪ ትምህርት ቤት 60 ደቀ መዛሙርት ተቀብሎ በማሰልጠን ላይ እንደሚገኝ መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡
በጉብኝት መርሐ ግብሩ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅን ጨምሮ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ሰብከት ካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ መ/ሕይወት አባ ወ/ኢየሱስ ሰይፉ፡ የጉራጌ ሀገረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎችና ልዩ ልዩ ሠራተኞች ተገኝተዋል፡፡
በጉራጌ ሀገረ ስብከት እዥ ወረዳ የተሠራውን የቅዱስ ሩፋኤልና አባ ሳሙኤል ገዳም ጸሎተ ቡራኬ በመከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን ሙሉ መረጃውን የምንመለስበት ይሆናል፡፡
ዘጋቢ:-መ/ር ሽፈራው እንደሻው
የመረጃው ምንጭና ፎቶ፡- መልአከ ሕይወት አባ ወልደኢየሱስ ሰይፈ