በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ መመሪያ ሰጭነት ተገንብቶ የተጠናቀቀው የአዳሪ ትምህርት ቤት ደቀ መዛሙርትን ተቀበለ

በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ መመሪያ ሰጭነት በጉራጌ አህጉረ ስብከት ተገንብቶ የተጠናቀቀው የአዳሪ ትምህርት ቤት ደቀ መዛሙርትን ተቀበለ።
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ለደቀመዛሙርቱ “የእንኳን ደህና መጣችሁ” መልእክት አስተላልፈውላቸዋል።
ብፁዕነታቸው የትምህርት ቤቱ መገንባት ዋናው ዓላማ ካህናትን በማሰልጠን ምእመናንን በመንፈሳዊ ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ እንደሆነ አውስተዋል።
አያይዘውም ካህናቱ በትምህርት ቆይታቸው የሚሰጣቸውን ሥልጠናዎች በአግባቡ በመውሰድ መንፈሳዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አጽንዖት ሰጥተው ገልጸዋል።
ካህናት የእግዚአብሔርን ቃል ለምእመናን የሚመግቡ እንመሆናቸው መጠን እራሳቸውን በሥልጠናዎች ለማጠናከር እንደዚህ ያሉ ትምህርት ቤቶች ለቤተክርስቲያኒቱ በብዛት ሊገነቡ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።
ተገንብቶ የተጠናቀቀው ሕንጻ G+1 ሲሆን ለመማር ማስተማር ምቹ መሆኑም ተገልጿል።
በዛሬው ዕለት ትምህርት ቤቱ የተቀበላቸው ካህናት በቁጥር 60 መሆናቸውም ተጠቅሷል።
ካህናቱ በትምህርት ቤቱ የሶስት ወራት ሥልጠና እንደሚወስዱ ተገልጿል።
በሶስት ወራት የሥልጠና ጊዜ ውስጥ የተለያዩ የቤተክርስቲያኒቱን መንፈሳዊ ትምህርት እንደሚወስዱም ተጠቅሷል።
መንፈሳዊ ትምህርት ቤቱ የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ተልዕኮ ለማስፈጸም የራሱ ድርሻ እንዳለውም ተገልጿል።
በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ እንደተገነባው እንደ ዝዋይ የካህናት ማሰልጠኛ ተቋም ብዙ መንፈሳዊ ጥቅሞችንም ለቤተክርስቲያኒቱ እንደሚሰጥ ይጠበቃል ።
ዘጋቢ መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ