በብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስ ወቅዱስ ጳውሎስ እና ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ለደብሩ ማኅበረ ካህናት የሚሰጠውን የሦስት ወራት ሥልጠናን አስመልክቶ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተከናወነ

በብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስና ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ለደብሩ ማኅበረ ካህናት የሚሰጠውን የሦስት ወራት ሥልጠናን አስመልክቶ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተከናወነ።
በመርሐ ግብሩ ላይ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ሊቀ ሊቃውንት አባ ጥዑመ ልሳን አዳነ የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ፣ ሊቀ ብርሃናት አድማስ አበራ የደብሩ አስተዳዳሪ፣ አሰልጣኝ መምህራን እንዲሁም የስልጠናው ተሳታፊዎች የደብሩ ሊቃውንትና ካህናት አገልጋዮች ተገኝተዋል።
መርሐ ግብር በጸሎተ ወንጌል የተጀመረ ሲሆን መርሐ ግብሩን ያስተዋወቁት የደብሩ ሰባኬ ወንጌል የሆኑት መጋቤ ሐዲስ ኤፍሬም ተስፋ በደብሩ ይስተዋል የነበረውን ሁኔታ አስታውሰው ክቡር የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በዛሬው ዕለት ሊያጣሩን ሳይሆን ሊያጠሩን በመምጣታቸው ማኅበረ ካህናቱ እንደተደሰተ ገልጸዋል።
የደብሩ አስተዳዳሪ ሊቀ ብርሃናት አድማስ አበራ ከተመደቡበት ጀምሮ በደብሩ ለወገኔ_ይጠቅማል በሚል የተፈጠሩ ችግሮችኔ ከሰበካ ጉባኤው ጋር በመሆን የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወኑ መሆናቸውን ያስታወሱ ሲሆን ከነዚህም አለመግባባቶች እንዲፈቱ የሰላምና ዕርቅ ኮሚቴ በማወቀር ለሰበካ ጉባኤውና ለማኅበረ ካህናቱ አደራውንና የጣለበትን ቤተ ክርስቲያናዊ ሐላፊነትን ጠብቆ እንዲያገለግል ሥልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።
በመሆኑም ይህ ዛሬ በክብሩ ሥራ አስኪያጁ የተከፈተው ሥልጠና የደብሩ ማኅበረ ካህናት አንድነትን የሚጠብቅና የተሰጣቸውን ሰማያዊ አደራ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያናዊ ተልዕኮ ሳይዘነጉ እንዲያገለግሉ ለማስታወስ የታሰበና ለውጡም በብዙ ናፍቆት የሚጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል።
አክለውም ሥልጠናው ለሦስት ተከታታይ ወራት በሳምንት ሁለት ቀናት ረቡዕና አርብ የሚሰጥ ሲሆን በዐራት የቤተ ክርስቲያናችን ተቋማት መምህራን ትምህርተ ኖሎት ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ቤተ ክርስቲያናዊ አስተዳደር በሚሉ ርእሶች ሥልጠናው ይሰጣል ብለዋል።
የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ሊቀ ሊቃውንት አባ ጥዑመ ልሳን አዳነ በበኩላቸው
ስለካህናት ሹመት፣ ሐላፊነት፣ተልእኮ፣ ዕውቀትና ሕይወት፣ የሚያስቀጣውንና የሚያሸልመውን ቤተ ክርስቲያን አደራ ምንነት ያብራሩ ሲሆን ይህ ሥልጠና ለማወቅና ለመተግበር እንደሚረዳ ጠቁመዋል።
የሦስት ወራቱ ሥልጠና መጋቤ ሐዲስ ስቡሕ አዳምጤ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ መምህር፣ ዶ/ር ቀሲስ መዝገቡ ካሳ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሊቀ ሊቃውንት ዮሴፍ ደሳለኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት ጉባኤ አባል የሚሰጥ ሲሆን የትውውቅና ስለሥልጠናው ሐሳብ አስተያየት ሰጥተዋል።
የማጠቃለያ መልእከትና መምሪያ ያስተላለፉት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንግሤ የሀገረ ስብከቱን አቅጣጫ በመከትል በፍጥነት ይህን ሥልጠና የደብሩ አስተዳዳርና ሰበካ ጉባኤ እንዲሁም ማኅበረ ካህናት ምስጋና ይገባል ብለዋል።
ቀጥለውም በመጽሐፈ መነኮሳት የሚገኘውን “በአንድ እጂህን እየሰበሰብክ በሌላኛው እጅህ አትበትን” በሚል ቃል መነሻነት ስለሥልጠና ምንነት፤ ከሥልጠናው የሚጠበቅውን ተጨባጭ ተግባር እንዲሁም አሁናዊ የቤተ ክርስቲያናችን ተግዳሮቶችን መረዳትና የአገልጋዮች ዝግጁነት የሚሉ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ትምህርትና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ለነገዋ ብቻ ሳይሆን ለአሁና ቤተ ክርስቲያናችን ህልውና በመንፈሳዊ መሠረትነት በትጋትና በጥንቃቄ መገልገል እንደሚገባ የጠቆሙት ክቡር ሥራ አርኪያጁ ጽድቃችን የተበተነበትኔ አርአያነታቸን የየተናቀበት፣ የፍቅር አጥተን የሰበሰብነው የአገልለግሎት በረከት በከንቱ የራስ ውዳድነት አማካኝነት ሳይጠቅመን እየበተነ ነው ብለዋል።
አክለውም ከምድር በላይ ሰማያዊ ሥልጣን የተሰጠውን የክህነት አገልግሎትን በመንደርና በጎጥ በማውረድ ሀብተ መንፈስ ቅዱስን በከንቱ እየበተነው ስለምንገኝ ወደ እውነተኛው የአገልግሎት ሕይውት እንመለስ ለዚህም ይህን ሥልጠና እንደምክንያትነት እንጠቀመው ብለዋል።
በመጨረሻም መልካም ሥልጠና እንዲሆን ተመኝተው በሥልጠናው የደብሩ ካህናት ሁሉም እንዲሳተፉ አሳስበዋል።
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በዊንጌት አካባቢ የሚገኘው የብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስ ወቅዱስ ጳወሎስ ቤተ ክርስቲያን እቴጌ መነን ስዕለታቸው ደርሶላቸው ከባዕድ ሀገር ሲመለሱ በእሳቸው አማካኝነት በ1933 ዓ/ም እንደተመሠረተ ታሪክ ያስረዳል።