“በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ አንደራደርም” …ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ
ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበትን ዕለት በማስመልከት ዛሬ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብሰባ አዳራሽ በተዘጋጀ የእንኳን አደረሰዎ መርሐ ግብር ላይ የተገኙት ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ስለ መስቀል አደባባይ ጉዳይ ያስተላለፉት አጭር መልክት ነው።
የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በዚሁ ጉዳይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰፊ ሥራ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል ።
የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደትን በማስመልከት የእንኳን አደረሰዎ መርሐ ግብሩን ያዘጋጀው የየካ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽህፈት ቤት በሥሩ ካሉት ገዳማትና አድባራት ጋር በመተባበር ነው።
በመርሐ ግብሩ ላይ ለብፁዕነታቸው የመስቀል እና የአርዌ በትር ስጦታም ተበርክቶላቸዋል።
በክፍለ ከተማው የተሰሩ የልማትና የሰላም ሥራዎች በየካ ክፍለ ከተማ ሥራ አስኪያጅ በመልአከ ሰላም ግርማ አሰፋ ሪፖርት ቀርቧል።
እንደመልአከ ሰላም ገለጻ ቤተ ክርስቲያን ከመንግሥት አካላት ጋር በቅርበት መሥራቷ ተጨባጭ ለውጥ እንዳመጣ ጠቅሰው ለዚህም በየካ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በኩል ለልደት በዓል በየካ ክፍለ ከተማ ሥር ላሉት ገዳማትና አድባራት ለጾም መፍቻ የሚሆን አንዳንድ በግ ስጦታ መሰጠቱን ጠቅሰዋል።
በእንኳን አደረሰዎ መርሐ ግብሩ ላይ የሲኤምሲ ደብረ ጽባህ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን መምህራን ወረብ ያቀረቡ ሲሆን ቅኔም የዝግጅቱ አካል ነበር።
ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅን ጨምሮ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር ሊቀ ጉባኤ ቆሞስ አባ ተክለሃይማኖት ወልዱ: የሀገረ ስብከቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ጥበብ ምናሴ ወልደ ሃና :የሀገረ ስብከቱ የዋና ዋና ክፍል ኃላፊዎችና ሠራተኞች: የየክፍላተ ከተማው የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች እና የመንግሥት ባለ ሥልጣናት በመርሐ ግብሩ ተገኝተዋል።
በተክለሃይማኖት አዳነ ጋዜጠኛ
ለተጨማሪ መረጃ የሀገረ ስብከቱን ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ይጎብኙ፣ like እና Join በማድረግ ይቀላቀሉ፣ ለሌሎችም ሼር ያድርጉ!!!
- ድረ-ገጽ:- www.addisababa.eotc.org.et
- ፌስ ቡክ ገጽ:- አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት/Addis Ababa Diocese
- ተሌ ግራም ቻናል:- t.me/AddisAbabaDiocese