በባለሙያዎች ተዘጋጅቶ የቀረበው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመዋቅር ጥናት ረቂቅ ሰነድ ውይይት በጥሩ ሁኔታ ተጠናቀቀ

2538

ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጀምሮ እስከ አድባራት እና ገዳማት ድረስ አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ በባለሙያዎች ተዘጋጅቶ በእስላይድ ሲቀርብ የሰነበተው የመዋቅር ረቂቅ ጥናት ውይይት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ስር በሚገኙ ክ/ከተሞች፤ ገዳማት እና አድባራት ተወካዮች ውይይት ሲደረግ ቆይቶ ዛሬ ታህሳስ 14 ቀን 2006 ዓ.ም በጥሩ ውጤት ተጠናቅቋል፡፡
ከ169 አድባራት እና ገዳማት በተውጣጡ የውይይት ተሳታፊዎች አጠቃላይ ብዛታቸው ከ2700 በላይ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡
መዋቅራዊና የአሠራር መመሪያ ጥናት ረቂቅ ሰነዱ 13 ጥራዞች ያሉት ሲሆን በአጠቃላይ እስከ 1,000 የሚደርስ ገፅ አለው ፡፡
በ2ቱም ቀናቶች ውይይት ከተካሄደባቸው ረቂቅ ሰነዶች መካከል፡-
1. አጠቃላይ ስለ መዋቅራዊና የአሠራር መመሪያ ጥናት ረቂቅ ሰነድ
2. ስለ አዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ደረጃ አሰጣጥ ረቂቅ ሰነድ
3. በሰው ኃብት አስተዳደር ረቂቅ ሰነድ
4. በፋይናንስ መመሪያ ረቂቅ ሰነድ
5. በግዥና ንብረት አስተዳደር መመሪያ ረቂቅ ሰነድ
6. በልማት መመሪያ ረቂቅ ሰነድ
7. በዕቅድና ሪፖርት መመሪያ ረቂቅ ሰነድ
8. በቁጥጥር መመሪያ ረቂቅ ሰነድ እና
9. የሥልጠና መመሪያ ረቂቅ ሰነድ ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የመዋቅር ረቂቅ ጥናት አቅራቢዎች፡- 
1ኛ. ዲ/ን ስንታየሁ ደምሴ ( BA – Accounting,MSc- Information Science )
2ኛ. ቀ/ሲስ ሶሎሞን አለነ( BA – management, MA Marketing management )
3ኛ. ዲ/ን ንጋቱ ባልቻ( BA – Accounting, MBA  )
4ኛ. ዲ/ን ተመስገን ወርቁ (BA – Accounting ,MSc Accounting and finance, PhD Candidate (Ctilbing University Holand) ተማሪ)
5ኛ. ካሣ አወቀ (BA – management, MBA)
6ኛ. አማረ በፈቃዱ( BA – management )
7ኛ. እስጢፋኖስ ታፈሰ (BA – management, BA-accounting, MBA Student)
8ኛ. ዳግማዊት ኃይሌ ( BA – Accounting, MBA)  
9ኛ. ዲ/ን አንዱዓለም ኃይሉ (BA – Economics ,MA Economics)
10ኛ. ቀሲስ ሶሎሞን በቀለ(መ/ር) (BA –Theology)
11ኛ. መስፍን ጥላሁን (BA – Economics, MA Economics)
12ኛ. መ/ስ ሳህሉ የማታ (LLB – Law )
13ኛ. ቀሲስ መንግሥቱ ጐበዜ (BA History, MA Archeology)
14ኛ. ተስፋዬ ቢሆነኝ(BA – Business Education, MA marketing )
15ኛ. ታደሰ አሰፋ (BA- Management ,MBA ,CIMA student, Theology students )
ሲሆኑ ውይይቱን በሊቀ መንበርነት የመሩት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት እና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሲሆኑ የመዋቅር ረቂቅ ጥናት ሰነዱ ከ14 ቀናት ያላነሰ የውይይት መርሐ ግብር ተደርጐበታል፡፡
ውይይቱ 96% ውጤታማ አንደነበር የጥናት አቅራቢ ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ታደሰ አሰፋ አብራርተዋል፡፡ የአዲስ አበባ አድባራት እና ገዳማትን የመልካም አስተዳደር ችግር ሙሉ በሙሉ ይፈታል ተብሎ በባለሙያዎች ተዘጋጅቶ ለውይይት የቀረበው የመዋቅር ረቂቅ ጥናት ሰነድ ቁጥራቸው ዘጠኝ በሚደርሱ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት እንደገና ሊገመገም እንደሚችል ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ አስታውቀዋል፡፡ በሊቃውንቱ ከተገመገመና ይሁንታን ካገኘ በኋላ በሥራ ላይ እንደሚውል ብፁዕነታቸው አክለው አብራርተዋል፡፡ ከመጀመሪያ ጀምሮ የመዋቅር ረቂቅ ጥናቱን ውይይት የመሩት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በየዕለቱ ከስብሰባው መጀመሪያ በፊት ቀድመው በመገኘት ለረቂቅ ጥናት ውይይት ስኬት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡
ይህ መዋቅራዊና የአሠራር መመሪያ ጥናት ረቂቅ ሰነድ በገንዘብ ቢሠራ ኖሮ ከ2,000,000 ብር በላይ የገንዘብ ወጪ ይጠይቅ የነበረ ከመሆኑም በላይ በቤተ ክርስቲያኒቱ ቋንቋ አገላለፅ መዘጋጀቱና እንዲሁም የነበረውን ወቅታዊ የሀገረ ስብከቱ የመልካም አስተዳደር ችግር በግልፅ ያሳየ እና ሙሉ መፍትሄውን በዝርዝር ያስቀመጠ በዓይነቱ ልዬ የሆነ ጥናት ነው፡፡
ለቤተ ክርስቲያኒቱ ብሎም ለሁሉም አህጉረ ስብከት ሞዴል የሚሆን ሥራ በመሆኑ ለአጥኝ ቡድን አባላት ክፍተኛ የሆነ ምስጋና ይገባቸዋል ፤ቀሪ ዘመናቸውን እግዚአብሔር አምላክ በደስታና በጤና እንዲያኖራቸው/እንዲጠብቃቸውና በመጨረሻም በማያልፈው የመንግስተ ሰማያት ወራሾች እንዲሆኑ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር እንደምታስባቸው የቤተ ክርስቲያን አባቶች ገልጿል፡፡

{flike}{plusone}