በሰሜን አሜሪካ ለኢትዮጵያውያን ምእመናን ቦታ ገዝተው፣ ቤተክርስቲያን አሳድሰው አስረከቡ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በሰሜን አሜሪካ በዩታ ግዛት ለኢትዮጵያውያን ምእመናን ቦታ ገዝተው፣ ቤተክርስቲያን አሳድሰው ያስረከቡትን የኋላኛው ቀን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ልዑካንን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ፡፡
ቅዱስነታቸው ልዑካኑን “ወደ ኢትዮጵያ፣ወደ መንበረ ፓትርያርክ እንኳን ደህና መጣችሁ” በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
የቤተክርስቲያኑ መሪ ቫስባንድ እንደተናገሩት “ቅዱስነትዎን በማግኘታችን፣ ቅዱስነትዎ ስለአደረጉልን አቀባበል ምስጋና እናቀርባለን፡፡ በሰሜን አሜሪካ በዩታ ግዛት ኢትዮጵያውን ኦርቶዶክሳውያን ይኖራሉ፡፡ ለእነዚህ ኦርቶዶክሳውያን እግዚአብሔርን የሚያመልኩበት ቦታ ሰጥተን ቤተክርስቲያን አሳድሰን አስረክበናል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን እየተገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ወደፊትም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጋር በትምህርት፣በሰላምና በወጣቶች ላይ በትብብር እንሠራለን፡፡” ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ቅዱስነታቸው እንደተናገሩት “በሰሜን አሜሪካ በዩታ ስቴት(ግዛት) ለትዮጵያውያን እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑበት ቦታ በመስጠታችሁ እናመሰግናለን” ብለዋል፡፡ ቅዱስነታቸው አክለውም “በወቅቱም ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ልከናቸው ቦታውን አይተው፣ ባርከው ቤተክርስቲያን የሠሩትንም አመስግነዋል፡፡ እናንተም በጥሩ ሁኔታ ተቀብላችሁ ስላስተናገዳችኋቸው በድጋሚ እናመሰግናለን፡፡ ወደፊትም ግንኙነታችን አጠናክረን እንቀጥላለን” ሲሉ አነባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
EOTC TV
