በሩሲያ ውስጥ ካሉ ግዙፍ የብዙኃን መገናኛ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የ”ጋዝፕሮም” ሚዲያ ልዑካን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅትን ጎበኙ
የ”ጋዝፕሮም” ሚዲያ ልዑካን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ስርጭት ድርጅት ዘመናዊ የቴሌቭዥን ስቱዲዮን ጨምሮ በድርጅቱ ቅጽረ ግቢ ውስጥ የሚከናወነውን የፕሮዳክሽን የሥራ ሂደትና የአስተዳደር ቢሮችዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡የ”ጋዝፕሮም” ሚዲያ ልዑካን በጉብኝታቸው ሩሲያ ከአፍሪካ በተለይም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጋር ያላትን ግንኙንት ይበልጥ ማጠናከር እንደምትፈልግ የገለጹ ሲሆን ልዑካኑ የቤተክርስቲያኗን ሚዲያ መጎብኘቱም ለዚህ መሻት አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የ”ጋዝፕሮም” ሚዲያ ልዑካንን ተቀብለው ያስጎበኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ስርጭት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ቀሲስ ዶ/ር አካለወልድ ተሠማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እና የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ለረጅም ዘመናት የቆየው ወዳጅነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ስርጭት ድርጅትም የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ገዳማትንና ታላላቅ ካቴድራሎችን ለኢትዮጵያዊያን ለማስተዋወቅ አይነተኛ ሥፍራ መሆኑን ለልዑካኑ ገልጸውላቸዋል።
ከቀሲስ ዶ/ር አካለወልድ ተሠማ የጋዝፕሮም ሚዲያ ባለሞያዎች ሥልጠና መስጠት በሚችሉበትን፣ መንገድ በተጨማሪም የቴክኖሎጂ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ዙርያ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡
የ”ጋዝፕሮም” ሚዲያ ልዑካን በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት ጋር በመተባበር የሁለቱን ሀገራት አብያተ ክርስቲያናት እና ህዝቦች ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ የሚያቀራርቡ ተከታታይ ድራማዎችንና ዘጋቢ ፊልሞችን ፤ ለመሥራት ማቀዳቸውን ጠቁመዋል፡፡
እነዚህ የፕሮዳክሽን ሥራዎች ታዲያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች ከ”ጋዝፕሮም” ሚዲያ አቻዎቻቸው ጋር በጋራ እንዲሠሩ ዕድል የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል።
በተመሳሳይ በሁለቱ መገናኛ ብዙኃኖች መካከል የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር የሥልጠናና የልምድ ልውውጥ እድሎችም ለባለሞያዎቹ እንደሚመቻች ልዑካኑ በዚሁ ጉብኝታቸው አረጋግጠዋል።
የ”ጋዝፕሮም” ሚዲያ ልዑካን በጉብኝታቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባቶችና ምእመናን ለሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ያላቸውን ቤተሰባዊነት ለማስተዋል በመቻላቸውም መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/
