“በሥራ ለተተረጎመ ቦታ በቃል ብዙ ማውራት አስፈላጊ አይደለም “…ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ
የአዲስ አበባና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ በርእሰ አድባራት እንጦጦ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን በበጀተ ዓመቱ የተሠሩ የልማት ሥራዎችንና የንጉሡን ቤተ መንግሥትና የቤተ ክርስቲያኑን ውስጣዊ ክፍል ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ የተደረገውን ዕድሳት በመረቁበት ወቅት ያስተላለፉት መልእክት ነው፡፡
ብፁዕነታቸው በገዳሙ የሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት አስተባባሪነት በደብሩ ካህናትና በበጎ አድራጊ ኦርቶዶክሳውያን የጋራ ትብብር ተሠርተው የተጠናቀቁ የልማት ሥራዎችን፡ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቀውን የቤተ ክርስቲያኑን ውስጣዊ ክፍሎችና የቤተ መንግሥቱን የዕድሳት ሥራ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡
የቡራኬና ጉብኝት መርሐ ግብር መጠናቀቁን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር ርእሰ አድባራት እንጦጦ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን በደገኛው ንጉሥ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከተመሠረቱ ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ መሆኗን አብራርተዋል፡፡
በአጭር ጊዜ ውስጥ በዚህ ጥንታዊና ታሪካዊ ቤተ ክርስቲያን ከተሠሩ የልማት ሥራዎች ባሻገር የንጉሡን ቤተ መንግሥትና የገዳሙን ውስጣዊ ክፍል ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ የተደረገው ዕድሳት በእጅጉ እንዳስደሰታቸው ገልጸው፡ በሥራ ለተተረጎመ ቦታ በቃል ብዙ ማውራት አስፈላጊ አይደለም ብለዋል፡፡
የቦታውን ታሪካዊነት ሲያስረዱም ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥታቸውን ከዚሁ ሥፍራ መሥርተው የዛሬይቱን የኢትዮጵያ ርእሰ መዲና ቁልቁል በማየት አዲስ አበባ የሚል ስያሜ የሰጡበት ቦታ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
አክለውም እዚህ ያለውን ከፍተኛ ቅዝቃዜ ተቋቁማችሁ ታሪካዊውን ሥፍራ እየጠበቃችሁ የምታገለግሉ አገልጋዮች እና አገልግሎቱን የምትደግፉ ሕዝበ ክርስቲያን በእጅጉ እናከብራችኀለን፡ በማለት አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም ደብሩ በጥናት ላይ የተመሠረተ ጥያቄ ካቀረበ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሚቻለው ሁሉ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የታሪክ ምልክትና መነሻ የሆነውን ታሪካዊ ቤተ ክርስቲያንም በመጠበቅና በመንከባከብ ረገድ ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ የበኩሉን እንዲወጣም አባታዊ ጥሪና መመሪያ አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡-መ/ር ሽፈራው እንደሻው
ፎቶ፡-በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ