በምዕራብ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአጉስታ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የእሳት ቃጠሎ አደጋ ደረሰ

                            በመ/ር ዘሩ እና በመ/ር ኃይሉ

ማክሰኞ ጥር 14/05/05 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 7.30 ሰዓት ሲሆን መንስኤው ባልታወቀ ምክንያት የእሳት ቃጠሎ ተነስቶ ቤተ ክርስቲያኑ ሙሉ በሙሉ የእሳት ቃጠሎ አደጋ ሊደርስ እንደቻለ ለማወቅ ተችሏል፡፡በዚሁ የእሳት ቃጠሎ እጅግ በጣም የሚያስደንቅ እና የሚያስገርም ተአምር ታይቷል፤4ቱም ፅላቶች ከነመጎናፀፊያቸው አንድም የእሳት አደጋ ሳይነካቸው ሊትርፉ እንደቻሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የፅላቶቹም ስም ፡-

1. በእመቤታችን ስም የተሰየሙ ሁለት ጽላቶች ፤

2. የቅዱስ ዑራኤል ፅላት እና

3. የመጥምቁ የቅዱስ ዮሐንስ ፅላት ናቸዉ

የእሳት ቃጠሎ በደረሰበት ዕለት ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የምዕራብና የደቡብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ ወንድይፍራው የምዕራብ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስከያጅ እና መ/ር ባህሩ ተፈራ የሀገረ ስብከቱ የህግ መምሪያ ኃላፊ በአካል ተገኝተው ማህበረ ካህናቱንና ህዝበ ክርስቲያኑን ያፅናኑ ሲሆን ታቦታቱም ከተቃጠለው ቤተ ክርስቲያን በካህናቱና በህዝበ ክርስቲያኑ በክብር ታጅበው ወደ ቤተልሄም ገብቷል፡፡ በተጨማሪም በአሁኑ ሰዓት ሀገረ ስብከቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የቃጠሎውን መንስኤ በማጣራት ሂደት ላይ ይገኛል፡፡

ሕዝበ ክርስቲያኑም በተለይ ወጣቶቹ ቤተ ክርስቲያኑን በድጋሚ ለመገንባት ከፍተኛ የሆነ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ዝርዝር ሁኔታውን በቀጣይ እየተከታተልን እናቀርባለን፡፡