በምሥራቀ ፀሐይ ቅ/ገብርኤል፣ ቅ/አርሴማ ወአቡነ አዳም ቤተ ክርስቲያን የሰማዕቷ የቅድስት አርሴማ ዓመታዊ ክብረ በዓል በድምቀት ተከብሮ ዋለ።
በምሥራቀ ፀሐይ ቅ/ገብርኤል፣ ቅ/አርሴማ ወአቡነ አዳም ቤተ ክርስቲያን የሰማዕቷ የቅድስት አርሴማ ቅዳሴ ቤቷ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና እጅግ በርካታ ምእመናን በተገኙበት በድምቀት ተከብሮ ውሏል።
በበዓሉ በሊቃውንት “ሃሌ ሉያ ቤተ ክርስቲያን፡ መስቀለ ክርስቶስ መሠረታ…፣ በደብሩ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራንም “እንተ ተሐንጸት በእደ ካህናት፡ ወተቀደሰት ቤተ ክርስቲያን በአፈ ጳጳሳት” የሚል ያሬዳዊ ዝማሬ ተዘምሯል።
በዕለቱ መ/መንክራት ግርማ ወንድሙ ትምህርት ሰጥተዋል። መ/መንክራት ግርማ “አንድ ሰው ወደ እርሱ ቀረበና ተንበርክኮ። ጌታ ሆይ፥ ልጄን ማርልኝ፥ በጨረቃ እየተነሣበት ክፉኛ ይሣቀያልና አለው” (ማቴ 17:14) በሚል መነሻነት ሰፋ ያለ ትምህርት ሰጥተዋል።
በመጀመሪያ ደረጃ አባት የልጁን ችግር ለይቶ በማጥናት፣ ክፉ መንፈሱ እንዴት እንደሚያደርገው፣ ወዴት እንደሚጥለው ጠንቅቆ በማወቅና የችግሩን መፍትሔ በማን አንደሚቀረፍ ተረድቶ ወደ መድኃኒቱ በመሄድ መንበርከኩን ገልጸዋል።
መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስም “ወደ እኔ አምጡት” በማለት ጋኔኑን ገሥጾ በማስወጣቱና ብላቴናው መፈወሱን በመግልጽ ሁላችን ስለ ሁሉም ነገር ወደ እርሱ ቀርበን መንበርከክና መጸለይ እንዳለብን አስተምረዋል።
በበዐሉ የተገኙት መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፈ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊም፦ “ምስክሮቼ ድንቆች ናቸው” በሚል መነሻነት ሰማዕት ማለት ምስክር ማለት ነው፤ ቅድስት አርሴማ የክርስቶስ ምስክር ናት፤ በዛሬ ዕለት በዚህ ስፍራ የተገኘንም የዚህ በረከት ተካፋዮች ስለ ሆን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
አዲሱ የምሥራቀ ፀሐይ ቅ/ገብርኤል፣ ቅ/አርሴማ ወአቡነ አዳም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ሆነው የተመደቡና ታኅሣስ 3 ቀን 2014 ዓ.ም ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው መ/ጽዮን ቆሞስ አባ እስጢፋኖስ ይርጋ በቦታው ለተገኙት ሁሉ እንኳን በሰላም አደረስን በማለት በዐሉ የፍቅር፣ የሰላምና በረከት የምንካፈልበት ይሁንልን ብለዋል ።
መልአከ ጽዮን ቆሞስ አባ እስጢፋኖስ ይርጋ ከዚህ በፊት በቀበና ምሥራቀ ፀሐይ መድኃኔዓለም ካቴድራል በአስተዳዳሪነት ሲያገለግሉ የቆዩት ሲሆን በቤተ ክርስቲያኑ ቆይታቸው በአጭር ጊዜ ብዙ የሚያሥመሰግን የወንጌልና የመሠረተ ልማት ሥራዎች መሥራታቸውን ይታወቃል።
በምሥራቀ ፀሐይ መድኃኔዓለም ካቴድራል ሳሉ ከሠሩዋቸው ስኬታማ ሥራዎች መካከልም፦ ደብሩ ወደ ካቴድራልነት ማሳደጋቸው፣ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ያልነበረው የሱቆች ቦታ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲሰጠው ማድረጋቸው፣ የቅጽረ ቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያም በንስሓ ልጃቸው ከ1,200,000 ወጪ በማውጣት የቴራዞ ንጣፍ ሥራ እንዲሠራ ማድረጋቸውና በንስሓ ልጃቸው ከ1,300,000 በላይ ወጪ የሥዕል ሥራ ተሠርቶ በካቴድራሉ ማስለጠፋቸውን ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ መሆናቸውን ይታወሳል።
አሁንም በቀበና ምሥራቀ ፀሐይ መድኃኔዓለም ካቴድራል የሠሩዋቸው ብዙ አሰደናቂ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ስኬቱ በምሥራቀ ፀሐይ ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አጠናክረው ይቀጥሉበታል ተብሎ ስለ ታመነባቸው ወደዚህ ታላቅ ደብር እንዲዘዋወሩ መደረጉን ተገልጻል።
መ/መንክራት ግርማ ወንድሙና መ/ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስም መ/ጽዮን አባ እስጢፋኖስ ይርጋ የወንጌልና የልማት አርበኛ መሆናቸውን በህዝቡ ፊት ሲመሰክሩ ተሰምተዋል።
መልአከ ጽዮን አባ እስጢፋኖስ ይርጋም ቅድሚያ ለወንጌል በመስጠት በወር ሁለት ጊዜ ጉባኤ እያደረግን የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን አጠናክረን በማስቀጠል ከሚመለከታቸው አካላት እየተመካከርን በትጋትና በንቃት ቤተ ክርስቲያናችን እናገለግላለን ሲሉ ወንጌሉንና ልማቱን አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ በህዝቡ ፊት ቃል ገብተዋል።
ደብሩ በአሁን ሰዓት በጣም ግዙፍ የሆነ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን እየገነባ መሆኑን ለመመልከት የቻልን ሲሆን በዛሬው ዕለት በተደረገው የበረከት አስተዋጽኦ መ/መንክራት ግርማ ወንድሙ አማንያን አስተባብረው መንበሮቹን አሠራለሁ ብለው ቃል ሲገቡ
እያንዳንዱን 45ሺህ ከሚፈጅ የ15 በሮቹ ደግሞ የ12ን በር ወጪ እንሸፍናለን ያሉ የበረከቱ ተካፋይ አማንያን መገኘታቸውን ለመመልከት ችለናል። የተቀሩትም በሌሎች አማንያን እንደሚሸፈኑ ተስፋ ተጥሎባቸዋል።
በበዓሉ ብዙ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና እንደ ሰማይ ከዋክብት ደምቀው የሚታዩ እጅግ በርካታ የተዋሕዶ ልጆች ምእመናንና ምእመናት ተገኝተዋል።
ዘገባ በመ/ር ኪደ ዜናዊ
ፎቶ በመ/ር ዋሲሁን ተሾመ