በልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የኤች.አይቪና ኤድስ መከላከያና መቆጣጣሪያ ፕሮጀክት ከተለያዩ አድባራት ጋር በመተባበር ወንጌል ለልማት በሚል ርዕስ ለካህናትና ለምዕመናን ስልጠና እየተሰጠ ነው

0202

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን እና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር ሲንቀሳቀስ የቆየው የወንጌል ለልማት ፕሮጀክት በኤች . አይቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር፣ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ዙሪያ ከብርጭቆ ማርያምና ከቃሊቲ መካነ ሕይወት ቅዱስ ገብርኤል አብያተ ክርስቲያናት ጋር በመተባበር ለስምንት ቀናት የቆየ የወንጌል ትምህርት መርሐ ግብር ያካሄደ ሲሆን በተጨማሪም ከአድባራትና ገዳማት ለተውጣጡ አጠቃላይ ቁጥራቸው 118 ለሚደርሱ ለአብነት መምህራን፣ለካህናትና ለሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ስልጠና የሰጠ መመሆኑን ምንጮቻችን አረጋግጠዋል፡፡

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለፕሮጀክቱ ስኬት የላቀ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ የሆኑት መምህር አስቻለው ካሴ አብራርተዋል፡፡ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የፕሮጀክት አማካሪ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ፣የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ምክትል ሰብሳቢ፣የሀገረ ስብከቱ ትምህርትና ሥልጠና ክፍልና የሀገረ ስብከቱ የሰንበት ት/ቤቶች ክፍል በአባልነት እንደሚገኙበት አስተባባሪው ገልፀዋል፡፡

እስከ አሁን ድረስ በተሰጠው ትምህርተ ወንጌልና ሥልጠና ከአድባራቱ በሚላከው ሪፖርት የተሻለውጤት መመዝገቡን መ/ር አስቻለው የገለፁልን ሲሆን በተለይም በቃሊቲ መካነ ሕይወት ቅዱስ ገበርኤል ቤተ ክርስቲያን በተደረገው የወንጌል ለልማት ፕሮጀክት ሐዋርያዊ ጉዞ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት፣የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ፣የከንባታ ሐዲያና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ብፁዕ አቡነ ዲሜጥሮስ በኢ.ኦ..ተ.ቤ የአረብ ኤምሬት አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተገኝተው የሰጡት ትምህርተ ወንጌልና አባታዊ ቡራኬ ምዕመናን በሃይማኖታቸው እንዲኮሩና በእምነታቸው እንዲፀኑ ጉልህ አስተዋፅኦ ማድረጉን የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ፀሐይ አባ ኃይለ መለኮት ይሄይስ ገልፀዋል፡፡ በተመሣሣይ ይህ ፕሮጀክት በስኬት እንዲጠናቀቅ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጰጳስ ሊመሰገኑ እንደሚገባቸው የተለያዩ አስተያየት ሰጪዎች ገልፀዋል፡፡

 በመጨረሻም የዝግጅት ክፍላችን የወንጌል ለልማት አገልግሎት የቤተክርስቲያናችን ተቀዳሚ ተልዕኮ እንደመሆኑ መጠን በየደረጃው የሚገኙ የቤተክርስቲያናችን ኃላፊዎችና አገልጋዮች በማንኛውም መንገድ የወንጌል ለልማት ፕሮጀክት መርሐ ግብር ሊጠናር ይገባል እንላለን፡፡

 

{flike}{plusone}