“በሀገራችንም ሆነ በዓለም ላይ ሰላም እንዲሰፍን ሁላችንም በአንድ መንፈስ ሆነን በእግዚአብሔር ፊት በጾምና በጸሎት ልንተጋ ይገባል” … ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ

የአዲስ አበባና የጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የ2014 ዓ.ም የዐቢይ ጾም መግቢያን አስመልክተው ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን አባታዊ መልእክት አስተላለፉ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በቀኖና ከወሰነቻቸው አጽዋማት መካከል አንዱ የዐቢይ ጾም መሆኑን ብፁዕነታቸው ገልጸዋል።

ዐቢይ የሚለው ቃል ትርጉሙ ትልቅ ማለት ሲሆን የጾሙን ታላቅነት ይገልጻል ሲሉ ተናግረዋል።

አያይዘውም ዐቢይ ጾም የተባለበት ምክንያት ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለጾመውና ለተከታታይ ስምንት ሳምንታት ሳይቋረጥ የሚጾም ስለሆነ ነው ብለዋል።

በእያንዳንዱ ሳምንት ውስጥ ያሉት እሑዶች የየራሳቸው የሆነ ስያሜ፣ ትርጉምና ልዩ ምሥጢር እንዳላቸውም አብራርተዋል።

ጾም ማለት ከምግብና ከመጠጥ ለተወሰኑ ሰዓታት መቆጠብ ብቻ  ሳይሆን አንደበትም ከሀሜት፣ እጅም የሌላውን ከመውሰድ፣ እግርም ወደ ክፉ ከመሄድ፣ ኅሊናም መጥፎውን ከማሰብ፣ ዓይንም የሚያሰናክሉ ነገሮችን ከማየት፣ ጆሮም የማይጠቅመውን የዚህን ዓለም ነገር ከመስማት ሊቆጠቡ ይገባል ሲሉ አጽንዖት ሰጥተው ገልጸዋል።

በትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ 58 ላይ ስለ ጾም የተጠቀሰውን የእግዚአብሔርን ሃሳብ አንስተው እግዚአብሔር የማይፈልገውን ጾም ሳይሆን እግዚአብሔር የሚፈልገውን ጾም መጾም እንዳለብን አውስተዋል።

እግዚአብሔር የማይፈልገው ጾም በተጠቀሰው  ምዕራፍ ላይ  “እነሆ፥ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ፣ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ፣ እነሆ ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ” ተብሎ መጠቀሱን አንስተዋል።

እነዚህን ነገሮች ከሕይወታችን በማስወገድና በማስተካከል ትክክለኛውንና እግዚአብሔር የሚፈልገውን ጾም ልንጾም እንደሚገባ አብራርተዋል።
  
አክለውም እግዚአብሔር የሚፈልገው ጾም በዚሁ ምዕራፍ ላይ  “የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ፥ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፥ የተገፉትንስ አርነት ትሰድዱ ዘንድ፥ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን? እንጀራህንስ ለተራበ ትቈርስ ዘንድ፥ ስደተኞቹን ድሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፥ የተራቈተውንስ ብታይ ታለብሰው ዘንድ፥ ከሥጋ ዘምድህ እንዳትሸሽግ አይደለምን? ” ተብሎ መጠቀሱን ገልጸዋል።

በመጨረሻም በአሁን ጊዜ በዓለም ላይ የሰላምና የፍቅር እጦት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ መምጣቱ  ለሁሉም ሰው አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን አያይዘው ጠቅሰዋል።

“በሀገራችንም ሆነ በዓለም ላይ ሰላም እንዲሰፍን ሁላችንም በአንድ መንፈስ ሆነን በእግዚአብሔር ፊት በጾምና ጸሎት ልንተጋ ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።

በተሰጠን ጸጋ ሌሎችን በማገዝና በመርዳት፣
የተራቡትን በመመገብ፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስ፣ የተጨነቁትን በመምከር፣
የታሰሩትን በመጠየቅ፣ስለ ሀገራችንም ሆነ ስለ ዓለም ሰላም አብዝተን በመጸለይ፣ በመጾምና ንስሐ በመግባት ልናሳልፍ ይገባል ሲሉ አባታዊ ምክራቸውን አስተላልፈዋል።

በመ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ

ለተጨማሪ መረጃ የሀገረ ስብከቱ ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ይጎብኙ:-

  1. ድረ-ገጽ:- www.addisababa.eotc.org.et
  2. ፌስ ቡክ ገጽ:- አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት/Addis Ababa Diocese
  3. ቴሌግራም ቻናል:- t.me/AddisAbabaDiocese
  4. ትዊተር :-www.Twitter.com/AddisDiocese