ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጠቃላይ የሥራ ሂደት ላይ ያላትን ተቋማዊ ሀሳብ እያቀረበች ትገኛለች
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እስከአሁን የሠራቸውን ሥራዎች እና ወደፊት ለመሥራት በዕቅድ በያዛቸው ሥራዎች ዙሪያ ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማትና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኀላፊዎች ጋር ውይይት እያደረገ ይገኛል።
ኮሚሽኑ ዛሬ ኅዳር 23 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ለስብሰባው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የተወከሉት ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የደቡብ ኦሞና አሪ ዞኖች ሊቀ ጳጳስ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚደንት እንዲሁም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።
የምክክር መድረኩን መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ “ይህንን ሀገራዊ ምክክር ውጤታማ ለማድረግ የሃይማኖት ተቋማት ግልጽ ውይይት አስፈላጊ ነው።” በማለት የመድረኩን መነሻ ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ እስከ አሁን ድረስ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያደረገውን ምክክር እና የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራን በመግለጽ የአጀንዳ ልየታ ሥራዎችን በቅርቡ እንደሚያከናውን ገልጿል።
ቤተ ክርስቲያናችን ለኮሚሽኑ ያቀረበቻቸው አጀንዳዎች ትኩረት እንዲሰጣቸው እና ያለምንም መሸራረፍ በአጀንዳነት እንዲያዙና የቤተ ክርስቲያናችንን ተቋማዊ ሕልውና የሚጻረሩ አጀንዳዎችም እንዳይያዙ በብፁዕነታቸው እና በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የሥራ ኃላፊዎች የምክክር ሀሳብ ቀርቧል።
