ቅዱስ ሲኖዶስ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ

ቅዱስ ሲኖዶስ ጥቅምት16 ቀን 2013 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ በነበረው ጉባኤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በታላቁ የሓዳሴው ግድብ ዙሪያ በሰጡት ግጭት ቀስቃሽ ንግግር ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ፡፡

መግለጫው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የቀረበ ሲሆን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሥራው ተጀምሮ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱ ከዚያም በላይ ከሦስት ወራት በፊት በግድቡ የመጀመሪያ ሙሌት ተደርጎ ለሕዝባችን የብስራት ድምጽ መሰማቱ ኢትዮጵያውያንን ያስደሰተ ጉዳይ መሆኑ፣ ከሦስት ዓመታት በኋላም የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደሚደርስ ተስፋ የተጣለበት መሆኑም ከመግለጫው ተደምጧል፡፡

ይሁን እንጂ ሕዝባችን በዚህ ተስፋ ውስጥ በገንዘቡም፣ በጉልበቱም፣ በሙያውም የበኩሉን ድጋፍ እየተረባረበ ባለበት ወቅት ጥቅምት 13 ቀን 2013 ዓ.ም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በሀገራችን ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ግድባችንን አስመልክቶ ሀገራትን ወደ ግጭትና አለመግባባት ውስጥ የሚከት የጥፋት መልዕክት ማስተላለፋቸው ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመታዊ ጉባኤው ላይ እንዳለ በሐዘን የተመለከተውና አጥብቆ የሚቃወመው እንደሆነ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

ታሪክ እንደሚያስታውሰን ሀገራችን ኢትዮጵያ በዘመናት ውስጥ ተከብራ የኖረችውና ለመላው ጥቁር ሕዝብ ምሳሌ የሆነችው ሀገሪቱ ሀገረ እግዚአብሔር፣ ሕዝቡ ሕዝበ እግዚአብሔር በመሆኑና በዚህም የሰውና የእግዚአብሔር አንድነት ሀገራችን በእግዚአብሔር ተጠብቃ የኖረች ሀገር መሆኗም ተብራርቷል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ በመከባበርና በአንድነት መንፈስ እየተረዳዱ የሚኖሩባት፣ እንግዳ በመቀበልና ቤት ያፈራውን ተካፍሎ በመኖር የሕዝባችን ልዩ መታወቂያ መሆኑም ተደምጧል፡፡

ከኃያላኑ መሪዎችም ሆነ ሌሎች ሀገራችንን በሩቅ ሆነው ከሚጎመጇት አካላት እየተጎሰመ ያለው የጥፋት ጥሪ ኢትዮጵያውያን እንደትናንት አባቶቻችን በአንድነት በመከባበር፣ በመመካከር፣ በመደማመጥም ጭምር መቆም ከቻልን ከአቅማችን በላይ የሚሆን ነገር እንደሌለ ከእኛ ይልቅ የሀገራችንን እድገት የማይፈልጉ ከእኛ ይልቅ የበለጠ ይገነዘቡታል፣ያውቁታል ተብሏል፡፡

በመጨረሻም በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣በሀገር የመምሪያ ኃላፊነት ለተሰጣቸው የፌዴራልና የክልል መሪዎች፣ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ሁሉም ኢትዮጵያዊ የትኛውንም የግልና የቡድን አመለካከት ወደ ጎን በመተው አንድነትን በማጠናከር የኢትዮጵያን ሕልውና ማስቀጠል እንደሚገባ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

መ/ር ወንድምአገኝ ደጀኔ የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ