ቅዱስ ሲኖዶስ በሀገራችን ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የአቋም መግለጫ ሰጠ
በዓመት ለሁለት ጊዜ ከሚካሄዱት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤያት መካከል አንዱ መደበኛውን የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤተከትሎ የሚደረገው የጥቅምት ምልዓተ ጉባኤ ነው፡፡ይህንን ጉባኤ አስመልክቶም ትናንት ጥቅምት 12 ቀን የመክፈቻ መግለጫውን መስጠቱም ይታወቃል፡፡
በዛሬው ዕለት ደግሞ ማለትም ጥቅምት 13/2012 ዓ/ምሁሉም የምልዓተ ጉባኤው አባላትና በርካታ የሚዲያ ባለሙያዎች በተገኙበት ለመወያያ ከቀረቡት አጀንዳዎች መካከል የሀገርን ጉዳይ ቅድሚያ በመስጠት የሰላም ጥሪ ለማድረግ መገደዱን በመግለጫው አውስቶየቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሀገራዊ ውለታና ስለ ሰላም ያላትን መሻት ካስገነዘበ በኋላ በሀገራችን ኢትዮጵያ ወቅታዊ ተግዳሮቶችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ዙሪያ ለሁሉም ባለድርሻ አካላትና ለመላው ኢትዮጵያውያን ከክፉ ነገር ራቅ ሰላምን ፈልጋት /መዝ.33፡12/ በሚል ርእስየሰላም ጥሪ አቀረበ፡፡
በመግለጫው ላይ የተላለፈው የሰላም ጥሪ በአሁኑ ወቅት ላለው ሀገራዊ ቀውስ ከማባበስ ይልቅ ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጡ ለሚገባቸው የማኅበራዊ ሚዲያና የመገናኛ ብዙኃን ድርጅቶች፤ የፖለቲካ ተንታኞችና አክቲቪስቶች፤ ለሀገር ተረካቢ ወጣቶች፤ የፍትሕና የጸጥታ አካለት እንዲሁም በሀገሪቱ ውስጥ ለሚገኙ የእምነት ተቋማትና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው ፡፡
በመጨረሻም ሰላም የሰላም አለቃ እግዚአብሔር ስለሆነ ከእርሱ የሆነውን ሰላም ለሀገራችን እንዲሰጠን መላው ሕዝባችን የሦስት ቀናት ጸሎትና ምህላ እንዲያደርግ በማለት ለተከታታይ ሦስት ቀናት መንፈሳዊ አዋጅ አውጇል፡፡
ሙሉውን የምልዓተ ጉባኤው መግለጫ ከታች ስለተያያዘ ታነቡት ዘንድ ተጋብዛችኋል፡፡
በሀገረ ስብከቱ ሚዲያ ክፍል
የሀገራችንን ወቅታዊ ጉዳይ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተላለፈ የሰላም ጥሪ፤
ተገሐሥ እምዕኲይ ወግበር ሠናየከክፉ ነገር ራቅ ሰላምን ፈልጋት መዝ.33፡12
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሥራቿና አምላኳ የሰላም አባትና አለቃ የሆነው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደመሆኑ በጸሎቷና በአገልግሎቷ ስለ ሀገር ሰላም፣ ስለ ሕዝቦቿና ስለ መላው ዓለም ሰላም ዘወትር ወደአምላኳ ስታማጽንና ስትማልድ የኖረች ያለችና ወደፊትም የምትኖር የሀገር ባለውለታና የሁሉም እናት መሆኗ ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጂ በሀገራችን በተለያዩ ክልሎች ልዩ ልዩ ምክንያቶች የአማራና የቅማንት፣ የሱማሌና የአፋር፣ የአማራና የትግራይ የኦሮሞና የአማራ የጉምዝና የአማራ የሲዳሞና የወላይታ በሚል ብሔርና ሃይማኖትን እንዲሁም ቋንቋን መሠረት ያደረገ በኢትዮጵያ ሀገራችን እንኳንስ ሊደረጉ ይቅርና ሊታሰቡ የማይገባቸው መጠነ ሰፊ ግጭቶች በመከሰታቸው የሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ በርካታ ንብረት ወድሟል፣ ዜጎች ከቀያቸው አለአግባብ እየተፈናቀሉ ለከፋ እንግልትና እርዛት ተዳርገዋል፡፡
እስከአሁን ድረስ በግጭቶች እየደረሱ ካሉት የሰው ሕይወት ጥፋትና የንብረት ውድመት ልንማር ባለመቻላችን በያዝነው ሳምንት ችግሩ ቀጥሎ በአዲስ አበባ፣ በኦሮምያ ክልልና በሌሎችም ክልሎች እየተሰከተ ያለው ግጭት እጅግ አሳሳቢ ከመሆኑም በላይ ጊዜ የማይሰጥና ሁሉም ኢትዮጵያውያን በአንድነትና በሕብረት ችግሩን ካልቀረፍነው መጠነ ሰፊ ጉዳትን የሚያስከትል ከመሆኑም በላይ በሀገራችን ያሉ ጅምር የልማትና የእድገት ጉዞዎችን በመግታት ሀገሪቱን ለከፍተኛ ጥፋትና ድህነት የሚዳርግ እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ በመሆኑ ዓመታዊ ስብሰባውን በማካሄድ ላይ የሚገኘው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ስለ ሀገር ሰላም ቅድሚያ በመስጠትና ከሌሎች የመወያያ አጀንዳዎች በማስቀደም በጉዳዩ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ተከታዩን አስቸኳይ የአቋም መግለጫና የሰላም ጥሪ አስተላልፏል፡፡
1.ማንኛውም የተለየ ሐሳብና አመለካከት ያለው ወገን ቢኖር ሐሳቡን በሰለጠነና በሰከነ መንገድ ሀገራዊ አንድነትን ማእከል ባደረገ ሁኔታ በክብ ጠረጴዛ በመወያየት ችግሮቹ እንዲፈቱና የአሠራር ግድፈቶች ካሉም እንዲታረሙ እንዲደረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፣
2.የሀገር ተረካቢ የሆናችሁ መላው የኢትዮጵያ ወጣቶች ሀገራችሁ ኢትዮጵያ ከዛሬ ይልቅ ነገ በእናንተ ተተኪነትና በምታከናውኑት የማይተካ የላቀ አስተዋጽኦ ወደላቀ የእድገት ደረጃ ደርሳ እናንተም ሆናችሁ መላው ወገናችሁ ተጠቃሚ የሚሆንባት የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባትና እውን ለማድረግ የሀገሪቱ ሙሉ ተስፋ በእናንተ በወጣት ልጆቻችን ትከሻ ላይ የተጣለ መሆኑ ይታወቃል፤ በመሆኑም በወቅታዊና ሚዛናዊ ባልሆነ አንዳንድ ከሕግ ማዕቀፍ የወጡ አካሄዶችን በሰከነ አእምሮ ትኩረት በመመልከት ሀገራችን ኢትዮጵያን ከጥፋትና ካልተገባ ግጭት ትታደጓት ዘንድ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከአደራ ጋር በአጽንኦት ለእናንተ ለልጆቿ ጥሪዋን ታስተላልፋለች፡፡
3.በሀገራችን ኢትዮጵያ የተፈጠረውን የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ተከትሎ ለሀገራችሁ የሚሆን ልዩ ልዩ አማራጭ ሐሳቦችን በማመንጨት ሕጋዊ እውቅና አግኝታችሁ በመንቀሳቀስ ላይ የምትገኙ ሁላችሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ ፖሊሲ ቀርጻችሁና ያመናችሁበትን ርዕዮተ ዓለም አቅዳችሁ የምትንቀሳቀሱት ሀገራችሁ ኢትዮጵያ ወደተሻለ የእድገት ደረጃ እንድትደርስ የበኩላችሁን ድርሻ ለመወጣት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ከዚህ አንጻር በየጊዜው ዘር፣ ብሔርና ሃይማኖትን መሠረት አድርገው እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችን ከጅምሩ በአንድነት ማስቆም ካልተቻለ ነገ የምትረከቧትና የምታስተዳድሯት ሀገር ልትኖር ስለማትችል በቅድሚያ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ሳይገድባችሁ ለሀገር ሰላምና አንድነት በሕብረት ዘብ በመቆም የበኩላችሁን ኃላፊነት ትወጡ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
4.ለመንግሥታችሁና ለሕዝባችሁ ሙያዊ ትንታኔን መሠረት ያደረገ አማራጭ ሐሳቦችን በግብዓትነት በማበርከት የሀገራችንን እድገትና የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ወደተሻለ ደረጃ እንዲደርስ የበኩላችሁን አስተዋጽኦ ለማበርከት በማሰብ ልዩ ልዩ ጽሑፎችንና ዘገባዎችን በመገናኛ በዙኃንና በማህበራዊ ሚዲያ የምታቀርቡና የምታስተላልፉ የፖለቲካ ተንታኞችና አክቲቪስቶች ከስሜት፣ ከብሔር፣ ከቋንቋና ከሃይማኖት ልዩነት በጸዳ ሁኔታ እናት ሀገራችሁን ማዕከል በማድረግ ለተሻለ ሰላምና አንድነት የበኩላችሁን ድርሻ ከማበርከት ባለፈ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩና አንዳንድ ያልተገቡ ትርክቶችን አላግባብ ከማሰራጨት በመቆጠብ ሀገራዊ ግዴታችሁን እንድትወጡ እናሳስባለን፤
5.የመንግሥትም ሆነ የግል የመገናኛ ብዙኃን ድርጅቶች ከተቋቋማችሁበት መሠረታዊ ተልዕኮና ዓላማ አንጻር በተቻለ አቅም ዘርን፣ ቀለምን፣ ብሔርንና ሃይማኖትን መሠረት ካደረጉ የትንኮሳ ቃላቶች በመራቅና ሚዛናዊ የሆኑ መረጃዎችን ለሕዝባችን በማድረስ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት የበኩላችሁን ኃላፊነት እንድትወጡ አደራ እንላለን፤
6.የማህበራዊ ሚዲያ መሠረታዊ ዓላማው ዜጎች በእውነታ ላይ የተመሠረቱ ወቅታዊ መረጃዎችን በተሻለ ፍጥነት እንዲያገኙ ታስቦ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ግን በሀገራችን ኢትዮጵያ እየታየ ያለው እውነታ ከዚህ በተለየ መልኩ ሕዝብን ከሕዝብ፣ ብሔርን ከብሔር፣ ጎሳን ከጎሳ ሃይማኖትን ከሃይማኖት የሚያጋጩና ከእውነት የራቁ ግጭት ቀስቃሽ ሐሰተኛ መረጃዎችን በማሠራጨት ሀገራችን ኢትዮጵያ የቆየ የአብሮነትና የአንድነት ባሕሏን በሚያጎድፍ መልኩ ላልተገባ ዓላማ እየዋለ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፤ ከዚህ አንጻር ዛሬ በሌሎች ላይ የሚደርሰው የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ነገ በየአንዳንዱ ቤት ሲያንኳኳ ሁሉም የጉዳቱ ሰለባ እንደሚሆን በመረዳት በተቻለ አቅም የማህበራዊ ሚዲያውን ለሀገራዊ ሰላምና አንድነት በመጠቀም ሁሉም የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚው ሕዝባችን የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ እንጠይቃለን፤
7.ሀገር በእውቀት እና በተሻለ ሐሳብ የምታድግና የምትመራ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ከዚህ አንጻር የሀገራችን ምሁራን ያላቸው ድርሻ በቀላሉ ሊገመት የማይችል ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን አንዳንድ ምሁራን የሚያስተላልፏቸው የኢትዮጵያን ታሪክ መሠረት ያላደረጉ ትርክቶች ለሀገራችን የግጭትና ያለመግባባት መንስኤ ሲሆኑ ይስተዋላሉ፡፡ በመሆኑም የሀገራችን ምሁራን በተቻለ አቅም ከልዩነትና ከግጭት ይልቅ ለሀገራዊ አንድነት እና ሰላም ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፤
8.በየደረጃው ያላችሁ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች መላው ሕዝባችን ትመሩትና ታስተዳድሩት ዘንድ የሰጣችሁን ይሁንታና ሀገራዊ ኃላፊነት ከግምት ውስጥ ባስገባና በታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነት ስሜት በተቻለ መጠን ግጭቶችና አገመግባባቶች ከመከሰታቸው በፊት ልዩ ልዩ የውይይት መድረኮችን ለመላው ሕዝባችሁ በማዘጋጀት እና በውይይት መድረኩ የሚገኙትን ግብአት የእቅዳችሁ አካል አድርጋችሁ በመተግበር ኃላፊነታችሁን ከቀድሞው በተሻለና በላቀ ሁኔታ በመፈጸም ለሀገራችን ሰላምና አንድነት እድገትና ብልጽግና የድርሻችሁን እንድትወጡ እንጠይቃለን፤
9.በየደረጃው ያላችሁ የፀጥታና የፍትሕ አካላት ሁሉ በተለያዩ ቦታዎች ግጭቶችና አለመግባባቶች ከመከሰታቸው በፊት ቅድመ መከላከልን መሠረት ያደረገ የፀጥታ ሥራን በመተግበር እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችንና የሰው ሕይወት መጥፋትን እንዲሁም የንብረት ውድመትን በመከላከል የተጣለባችሁን ኃላፊነት እንድትወጡ እናሳስባለን፤
10.መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! እስከአሁን ድረስ የኢትዮጵያን ሰላም በማይወዱ አካላት የሚከሰቱ ልዩ ልዩ አፍራሽና ግጭት ቀስቃሽ አጀንዳዎችን ወደጎን በመተውና በአርቆ አሳቢነትና በሀገር ባለቤትነት መጠነ ሰፊ ትዕግስት የተሞላበት ሀገራዊ አንድነትና ሕብረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ላበረከታችሁት የማይተካ ሚናና ታሪክ የማይረሳው ውለታ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም እያመሰገነ እንደአሁን ቀደሙ ሁሉ ለሀገራችን ሰላምና አንድነት ዘር፣ ብሔርና ሃይማኖት ሳይለያያችሁ እጅ ለእጅ በመያያዝ የበኩላችሁን የማይተካ ድርሻ እንድትወጡ የአደራ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፤
11.በሀገራችን ኢትዮጵያ የምትገኙ የሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ሀገራችን ኢትዮጵያ በሃይማኖት ብዝሃነትና ተቻችሎና ተከባብሮ በመኖር አስደናቂ ባሕሏ ሌሎች ሀገራት የሚቀኑባትና በአርአያነትም የሚጠቅሷት ሀገር መሆኗ ይታወቃል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ይህን አኩሪና አርአያ የሆነ ታሪኳን በሚያደበዝዝ ሁኔታ ሃይማኖትና ብሔርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች እየተበራከቱ በመሆናቸው ዜጎች ያለምንም መሸማቀቅና ተጽእኖ እምነታቸውን ለማምለክና ለማስመለክ የማይችሉበት የስጋት አደጋ እየተጋረጠ ከመሆኑ አንጻር ሁሉም ቤተ እምነቶች ለሀገራዊ አንድነትና ለእምነት ነጻነት በአንድነትና በሕብረት ለመላው ሕዝባችን የሰላም ጥሪ በማስተላለፍና ዘወትር በየአስተምህሮአችን ለሕዝባችን የሰላምን ጥሪ ተደራሽ በማድረግ ሀገራዊ ኃላፊነታችንን እንወጣ ዘንድ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
12.በመጨረሻም ያለ ሀገር ሰላምና አንድነት እንዲሁም ፍቅርና እድገት መኖር ስለማይቻል መላው ሕዝባችን እንደየእምነቱና ሃይማኖቱ ሥርዓት ከዛሬ ጥቅምት 13 ቀን 2012ዓ.ም. ጀምሮ ለ3 ቀን ያህል በጾም፣ በጸሎትና በሐዘን ስለ ሀገር ሰላም በአንድነት ጥሪውን ለፈጣሪውና ለአምላኩ ያቀርብ ዘንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጸሎትና ምህላ እንዲደረግ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም ጥሪውን አስተላልፏል፡፡ መንፈሳዊ አዋጁንም አውጇል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!ጥቅምት 13 ቀን 2012 ዓ.ምአዲስ አበባ – ኢትዮጵያ