ቅዱሱን ወንጌል በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ መምህራንን ማብቃት እንደሚገባ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ ገለጹ

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ ዋና ክፍል በ2018 ዓ.ም የዐብይ ጾምን አስመልክቶ የጋራ የምክክር ጉባኤና በቅርቡ የዋና ክፍሉ ኃላፊ ሆነው ለተመደቡት ለበኩረ ትጉኅን ደመላሽ ቶጋ የእንኳን ደና መጡ መርሐ ግብር ተካሔዷል።
ዐብይን ጾም በተናበበና መዋቅራዊ በሆነ መልኩ የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን ለማጠናከር እንደታሰበና አገልግሎቱ ምን መመሰል እንዳለበት ውይይትና ምክክር ተደርጎበታል።
የዐቢይ ጾም ጉባኤን አስመልክቶ ከቅድስት እስከ ሆሳዕና ባሉት ሳምንታት የሚካሄድ ሲሆን ስምንቱንም ክፍላተ ከተሞች ያካተተ እንደሚሆንና የዘንድሮው ጉባኤም በ56 ገዳማት ና አድባራት በ140 መምህራን ጉባኤዎችን ለማገልገል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን የአዲስ አበባ ሰባክያን ኅብረት ሰብሳቢ በኩረ ትጉኅን ፋንቱ ገላው (ዶ/ር) ገልፀዋል።
በተጨማሪም በሆሳዕና ሳምንት በስምንቱ ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ከተመደቡት ውጪ በፍቃደኝነት ጉባኤ የሚያደርጉ ገዳማትና አድባራት እንደሚጨመሩበትና በመርሐ ግብሩ ላይ ሆሳዕናን ለሆሳዕና በሚል ለሆሳዕና መንፈሳዊ ከፍተኛ ትምህርት ቤት የገቢ ማሰባሰቢያና የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት እንደታሰበ ገልፀዋል።
መጋቢ ሐዲስ ንጉሡ ዓለሙ በበኩላቸው የኅብረቱን የሚዲያ ተደራሽነትን በተጠናከረ መልኩ ለመቀጠል እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን አብራርተዋል። ከዚሁ ጋር የኅብረቱ አባላት ለሆኑ አገልጋዮች ሁሉ መታወቂያን ለማዘጋጀት ይቻል ዘንድ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ “ወንጌል የሁሉም ነገር መክፈቻ ቁልፍ ነው”ሲሉ ተናግረዋል ።
ለሰባክያኑም ወርቅ የሆነውን፣ ፣ወደ አንድነት የሚያመጣውን የሚያፋቅረውን ንፁሕ የሆነውን ወንጌል እንዲዘሩ መልእክት አስተላልፈዋል።
በተጨማሪም ቅዱሱን ወንጌል በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ተደራሽ ለማድረግ መምህራን ማብቃት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በትረ ትጉኅን ደምመላሽ ቶጋ በዐብይ ጾም ወቅት የሚሰብኩ ሰባክያን ከግጻዌና ከስንክሳር ጋር የተያያዘ ዝግጅት አድርገው ትምህርተ ወንጌልን እንዲያስተምሩ መልእክት አስተላልፈዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይም መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ በኩረ ትጉኀን ደመላሽ ቶጋ የሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ ዋና ክፍል ሐላፊ፣ በኩረ ትጉኀን ፋንታ ገላው (ዶ/ር) የሰባክያነ ወንጌል ኅብረት ዋና ሰብሳቢ፣ የገዳማትና አድባራት መምህራነ ወንጌል ተገኝተዋል።